Sunday, 21 February 2021 17:15

‘ተራችንን’ ጥበቃ...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

   "ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ለዚህ ‘መካከለኛ ገቢ’ ለሚባለው ነገር ተራ ይዘን አልነበረም እንዴ! (ወይስ የያዝን መስሎን ነው!) አሀ...ልከ ነዋ...እንደውም ብዙ ነገሮች ላይ “ሀገሪቱ መካከለኛ ገቢ ስትደርስ ይሳካል...” ምናምን የሚባል ነገር ተለምዶ ነበር፡፡ ግን አሁን መካከለኛ ገቢ፣ ‘መካከለኛ ህልም፣” ነገር ሆነች መሰለኝ!"
    
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ተረኛ ነኝና እንዳትሸበሪ
ስለይሽ አዝናለሁ አልማዝ ደህና እደሪ-
የምትል አሪፍ ዘፈን ነበረች...ያኔ ብዙ አልማዞች በነበሩ ጊዜ ማለት ነው፡፡
እናማ... አለ አይደል.... ምን መሰላችሁ...ተራ እየጠበቅን ነው፡፡ ይኸው ስንት ዘመናችን... ተራ ጥበቃ ላይ ሆነን፡፡ አንዳንዴ ተራ ውስጥ ለመግባታችን እንኳን እርግጠኞች ሳንሆን ተራ እንጠብቃለን፣ ወይም ተራ እየጠበቅን ያለን ይመስለናል፡፡ ታዲያላችሁ በርዬው ላይ ስንደርስ “እሰይ ስለቴ ሰመረ!” ብለን ሳናበቃ እጢዬዋ ዱብ! የጥበቃ ሠራተኛ ሆዬ ይጠይቃል፤ የሆነች ብጣሽ ወረቀት ቢጤ ይዟል፡፡
“ስም?”
“ተራዬ ደረሰ”
ሊስቱን አየት ያደርግና... ምን ቢል ጥሩ ነው... “በዛ ስም የተያዘ ተራ የለም”
“እንዴ ትናንትና በስልክ ደውዬ አስመዝግቤ ነበር እኮ!”
“እዚህ ላይ ስምህ የለም”
“እባክህ በደንብ እይልኝ”
“ሥራችንን እንሥራበት፣ በሩን ልቀቀው፤ ተረኛ!”
ብግን ብላችሁ በሩን ብቻ ሳይሆን አካባቢውን ለቃችሁ ትሄዳላችሁ፡፡ እድሜ ለአንጻራዊነት አሁንም ወለሏ ላይ ካለው ህብረተሰብ ብዙ እርቃ ያልሄደችው ዳግም!
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ተራ ጥበቃ ክፋት የለውም። አንዳንዶቻችን እንደምናስበው የቅሽምና፣ የኋላ ቀርነት ነገር አይደለም... በህግና በስርአት የመመራት የዘመናዊነት መንገድ እንጂ!
እኔ የምለው... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ይሄ ‘ዘመናዊነት’ የሚሉት ነገር ግራ እያጋባን ነው፡፡ ልከ ነዋ... መለኪያው ተምታታብና! ‘ድሮ፣ ድሮ’ ጠጉርዬውን እንደ ኤልቪስ ፕሪስሊ መሃል ላይ  የከፈለ ሰው፣ በቃ፣ ምን አለፋችሁ ዘመናዊነት የሚከፋፈል ቢሆን ኖሮ፣ በ‘ትርፍነት’ የያዘውን ሁሉ ያከፋፍል ነበር! እናላችሁ... እንደውም አረማመዱ ሁሉ እንደ ኤልቪስ ይሆናል...ኤልቪስ እንዴት እንደሚራመድ አይቶት አያውቅም እንጂ! እናላችሁ... ወደዚያኛው ዘመን ‘ዘመናዊነት’ ኩዋንተም ቅብጥርስዮ ምናምን የሚባሉ ነገሮች ስለሌሉት ቀለል ያለ ነው፡፡
ፓሪሞድ ለብሳለች፣ ሹራብ ደርባለች
ጸጉሯን ተተኩሳ በፎርም ሰዓት አድርጋለች
አያችሁልኝ አይደል! ዘመናዊነትን ለመለየት ከዚህ በላይ ምን ያስፈልጋል? እሷዬ ፓሪሞድ ከለበሰች፣ ሹራብ ከደረበች፣ ጸጉሯን ከተተኮሰችና ሰዓት ካደረገች፣ ማን ምን የቆረጠው ነው፣  ከዘመናዊነት ዙፋኑዋ ላይ የሚያወርዳት!?
“ስማ ያቺ እንትናን አይተሀታል?”
“አላየኋትም፣ በጣም ረጅም ጊዜ ሆኖኛል”
“እኔ እሁድ እለት ሰርግ ላይ አላገኛት መሰለህ! ብታያት አታውቃትም፡፡ ሌለ ሰው ነው የሆነችው፡፡"
“አገባች እንዳትለኝ!”
“በቃ የድሮ ነገር ላይለቅህ ነው! የዛሬ አስር ዓመት፣ ከአስር ወር፣ ከአስር ቀን የተለየሀትን ሴት አገባች፣ አላገባች ምን ይመለከትሀል!”
“ወደ ጉዳይህ፡፡ እና አገኘሃት፣ ምን ይጠበስ!”
“አትናደዳ!”
አሀ... ለምን አይናደድም! እንደውም ወዳጅ፤ “አንድ ጊዜ ተናደድና ይውጣልህ" እንደማለት ጭራሽ “አትናደዳ!” ብሎ ነገር! ለምንስ ‘ክሬዜ’ ምናምን አይሆንም! ሜዳ ላይ አስጥታው አይደል እንዴ የሄደችው! እንደውም ደምፕ አደረገችው ማለት ምን ማለት እንደሆነ የተረዳው ያኔ ነው። የምር ግን... እንዲሁ ‘ቻዎ፣ ቻዎ’ መባባል አሪፍ ነገር ነው፡፡ ደህና ሁኝ ልበልሽ በእንባ እየታጠብኩኝ ማለትም አንድ ነገር ነው።  ሜዳ ላይ ማስጣት ግን አሪፍ አይደለም፡፡
“እሺ፣ አሁን ለምንድነው የእሷን ስም ያነሳህልኝ?”
“አንተ እንዴት ዘመናዊ እንደሆነች ብታያት አታምንም፡፡ እዚህ የምናውቃት ሳትሆን እኮ ከአሜሪካ ምናምን ዱብ ያለች ነው የምትመስለው!”
“ዘመናዊነቷን በምን አወቅህ?”
“ፓሪሞድ ለብሳለቻ!” (ቂ...ቂ...ቂ....)
አሪፍ አይደል፡፡ ‘ሁዋሳፕ’ ማለት አያስፈልግ! ኦ.ኤም.ጂ. ማለት አያስፈልግ! ፓሪሞድን የመሰለ ተቃውሞ ሊቀርብበት የማይችል የዘመናዊነት ሚዛን እያለ፡፡ ዛሬ ፓሪሞዱ ቀርቶብን እንደው ‘የአስተሳሰብ ዘመናዊነት’ የሚባል ነገር ካለ፣  በሻይ ማንኪያም ቢሆን ይከፋፈለንማ!
እናላችሁ... በየስፍራው፣ በየመስኩ ስርአት እየጎደለበት ብቻ ሳይሆን “ህግ የሚባል ነገር የለም፣” የሚል አዋጅ የወጣ በሚመስልበት በአሁኑ ጊዜ፣ ባሉበት በስርአት ተሰልፎ ተራን መጠበቅ ዘመናዊነት ነው፡፡
ግን እንደዛ እያደረግን ነው ወይ? በስርአት እየተሰለፍን ተራችንን እየጠበቅን ነው? የታክሲ ጥበቃን እዩልኝማ! አሁን፣ አሁን እኮ ሰልፉ የትና የት እንደደረሰ እያዩ፣ ዘሎ ሰልፍ ሰብሮ መገባት እየተለመደ ነው። እንደ ቀድሞው ቢሆን... አለ አይደል... “ምን የዘንድሮ ጎረምሳ ሰው አያከብሩ፣ ለራሳቸውም ክብር የላቸው ...ምናምን ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ልጄ ጉርምስና የ‘ኤጅ’ ጉዳይ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ጸጉርዬዋ ‘ሁዋይት’ ሆነች፣ ‘ብላክ’ ሆነች...ለውጥ የለውም፡፡ ‘ሰቨንቲን’ ደርሶ እንትን፣ እንትን የአካል ክፍሎች ‘ጠጉር’ ነገር እየሞካከረው ያለውም፣ ‘ሰቨንቲ ዋኗን ላፍ አድርጎ እንትንና እንትን የአካል ክፍሎች ‘ጠጉርዬው’ እየሳሳበት ያለውም... ሰልፍ ደርምሶ ነው የሚገባው... ያውም ዓይኑን በጨው አጥቦ! አብዛኛው ሰዋችን ደግሞ አሁን፣ አሁን ንትርክና ጭቅጨቅ እየሰለቸው ነው መሰለኝ ዝም ብሎ ይታዘባል አንጂ “ውጣ!” “አስወጣው!” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡
እናላችሁ... አንዳንድ ቦታዎች ራሳቸው የታክሲ ተራ አስጠባቂዎች እንኳን ሁሉን መብት እኩል ሊያስከብሩ ይቅርና ራሳቸው ‘ዘመድ ሲጠቅሙ’ ነው የሚታየው፡፡ ሰልፉ ተጠምዝዞና ተጠማዞ የትናየት ደርሶ እያለ ወይ የሠፈር ልጅ ሲመጣ፣ ወይ ደግሞ ተራ አስከባሪው፣ በአራድኛው ዲክሺነሪ፣ ‘ጆፌ የጣለባት’ እንትናዬ ስትመጣ ሰልፍ መስበር ሳያስፈልገው ልክ ታክሲ እንደመጣ ‘ጋቢና’ ያስገባታል፡፡ ይቅርታ የለ፣ ምን የለ! ስሙኝማ... ‘ወንጀልን በጋራ እንከላከል’ የሚል ጃኬት ተለብሶ አንደ ልብ ህግ የሚፈርስባት ሀገር፣ ከእኛ ቀጥሎ የትኛዋ ነች!
ስሙኝማ... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ለዚህ ‘መካከለኛ ገቢ’ ለሚባለው ነገር ተራ ይዘን አልነበረም እንዴ! (ወይስ የያዝን መስሎን ነው!) አሀ...ልከ ነዋ...እንደውም ብዙ ነገሮች ላይ “ሀገሪቱ መካከለኛ ገቢ ስትደርስ ይሳካል...” ምናምን የሚባል ነገር ተለምዶ ነበር፡፡ ግን አሁን መካከለኛ ገቢ፣ ‘መካከለኛ ህልም፣” ነገር ሆነች መሰለኝ! እንደ ሰሞኑ አይነት ሁሉም ዋጋ ጣራ በነካበትና ኪስ ባዶውን ከርሞ ተከራይ ያጣ ቤት በመሰለበት መካከለኛ ይባል ወደነበረው ቀረብ ብሎ የነበረው ሁሉ ራሱን የት ቢያገኝ ጥሩ ነው... ወለሏ ላይ! ስሙኝማ... በቃ እንዲህ ሆነን ልንከርም ነው! ማለቴ የመጨረሻዋ የጋራ የምንላት ጤፍ እንኳን ቪላ ምናምን እየመረጠች መሄድ ጀመረች እኮ!
እናችላሁ እኛ መካከለኛ ገቢ የሚባለው ስፍራ ለመድረስ ስናልም (ሥንሠራ ሳይሆን ስናልም) መካከለኛ የተባለችው ነገርዬዋ የምትገኝበት መስመር ከሦስተኛ ፎቅ ወደ ዘጠነኛው ተፈናጥራ ቁጭ! ደግሞስ ‘መካከለኛ ገቢ ካላቸው ጋር’ ለመመደብ ተራችንን ‘ሪዘርቭ’ አስደርገናል እንዴ!  ልከ ነዋ...በምኑም፣ በምናምኑም እኛ መሄድ አቅቶን ባለንበት እየረገጥን፣ ሌሎቹ እየቀደሙን ቦታውን ቢሞሉትስ!
“ይቅርታ፣ ቦታ ሞልቷል፡፡ ደግሞም መስፈርቱን አታሟሉም፡፡"
“እንዴት አናሟላም! በቀን ሦስት ጊዜ እየበላን እኮ ነው!”
“በቀን ሦስት ጊዜማ በዛኛው ዘመን መለኪያ ነው!”
እናላችሁ ብዙ ነገሮች ላይ ተራ እየጠበቅን ወይ አንደርስም፣ ብንደርስም በሩ ተከርችሞ ይጠብቀናል፡፡
“የተሻሻለውን መስፈርት ስታሟሉ ተመልሳችሁ ኑ!”
በነገራችን ላይ... ያ “ተረኛ ነኝና እንዳትሸበሪ" ብሎ የዘፈነው ወገናችን፣ ጠዋት ወደ ቤቱ ተመለሰ ወይስ ባደረበት ከእንትን መውረጃ ሹሮ ፍትፍት ቀረበለት! ቂ...ቂ...ቂ...
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 893 times