Saturday, 13 February 2021 13:15

የራስን ቤት ማጽዳት ነው!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

      "-ማን ያልጠመደን አለ፡፡ አሁንማ ለይቶላቸው ግንባር ገጥመው ይኸው ጋዜጣ አይቀራቸው፣ ቴሌቪዥን አይቀራቸው፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች አይቀሯቸው…. አንድዬ በቀላሉ ከጥይት ያልተናነሰ ዘመቻ እያካሄዱብን ነው፡፡--"
          
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እኔ ነኝ፡፡
አንድዬ፡— አሁን፣ አሁንማ ምንም እኮ መናገር አያስፈልግህም፡፡ ገና በኮቴህ አንተ መሆንህን አውቅሀለሁ፡፡ ለምን ብለህ ጠይቀኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ለምን አንድዬ?
አንድዬ፡— አረማመድህ ግራ የተጋባ ነዋ፡፡ ወይ እየተራመድክ ነው አይባል፣ ወይ እየሮጥክ ነው አይባል፣ ወይ ሰክረህ እየተንገዳገድክ ነው አይባል፡፡ ብቻ መላ ቅጡ የጠፋ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በምን አቅሜ ቀጥ ብዬ ልሂድ ብለህ ነው!
አንድዬ፡— ለነገሩ አንተ አቅም አለኝ ብለህ ታውቃለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ በአንድ ወቅት አቅምማ ነበረኝ፡፡ አባቶቻችን፣ አያቶቻችን....
አንድዬ፡— ቆየኝ፣ ቆየኝማ፡፡ ስለ አባቶችህና ስለ አያቶችህ አይደለም የጠየቅሁህ፡፡ ስለ አንተ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እኔስ ብሆን የመጣሁት ከእነሱ አይደለም እንዴ!
አንድዬ፡— ቢሆንስ እነሱ በሠሩት ለመመስገን፣ ለመወደስ ከመፈለግ አንተም በራስህ የሚያስመሰግን ሥራ ብትሠራ አይሻልም፡፡ ያን ጊዜ የአባቶቼ፣ የአያቶቼ ልጅ ነኝ ብትል ያምርብሀል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱስ ልክ ነህ፣ አንድዬ፣ እሱስ ልክ ነህ፡፤
አንድዬ፡— ስማ አባቶችህና አያቶችህ በጊዜያቸው እንደ እናንተ በየቀኑና በየሰዓቱ አቤቱታ እየተሸከሙ በሬን አይቆረቁሩም ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ጊዜው እኮ ተለውጧል፣ አንድዬ፡፡ እኛ ጥሩ ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡
አንድዬ፡— ከእነሱ ጊዜ ምን የጎደለባችሁ ነገር አለ፡፡ አሁንም የምትወጣው ፀሀይ በአባት፣ አያቶቻችሁ ጊዜ ስትወጣ የነበረችው ነች፡፡ አሁንም ያለው መሬቱ እነሱ ሲያርሱት የነበረው ነው፡፡ ያኔም ይዘንብ እንደነበረው አሁንም ይዘንባል፡፡ ያኔም ይፈሱ የነበሩ ወንዞች አሁንም  እየፈሰሱ ነው፡፡ እንደውም እናንተ ትራክተር፣ ማዳበሪያ ምናምን የምትሏቸው ደጋፊ ነገሮች አሏቸው። ግን እንኳን ለሌላ ልትተርፉ ለራሳችሁ መብቃት አልቻላችሁም፡፡ በእነሱ ጊዜ እኮ ለተራበ የአውሮፓ ሀገር የምግብ እርዳታ ሁሉ ልከው ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እሱ ነገር እውነት ነው እንዴ?
አንድዬ፡— ትጠራጠራለህ እንዴ!?
ምስኪን ሀበሻ፡— መጠራጠር ሳይሆን...
አንድዬ፡— አየህ አይደል፤ አየህ አይደል ምስኪን ሀበሻ! ዋነኛ ችግራችሁን አየህ አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን አጠፋሁ አንድዬ?
አንድዬ፡— ስለ ራሳችሁ ደግ ደጉን መቀበል ይቸግራችኋል፡፡ ይህን ጊዜ እኮ በዛ ዘመን የሚበሉት፣ የሚቀምሱት ስላልነበራቸው ድንጋይ ሁሉ ይቆረጥሙ ነበር ብልህ ኖሮ ታምነኝ ነበር፡፡ እርዳታ ሰጥተው ነበር ስልህ ግን  ደነገጥክ..
ምስኪን ሀበሻ፡— መደንገጥ ሳይሆን...
አንድዬ፡— ሁልጊዜ ግራ የሚገባኝ ነገር ነው፡፡ ለምንድነው  የትናንት ህብረተሰቦችን ጥንካሬና ድክመት በራሳችሁ ሚዛን  የምታስቀምጡት፡፡ ለምንድነው ስላለፈው ታሪካችሁ ደግ፣ ደጉ ላይ ጀርባችሁን እያዞራችሁ ክፉ፣ ከፉ የተባለውን ብቻ የምታምኑት፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ በእኛ ሚዛን ብንመዝነው ምን ችግር አለው?
አንድዬ፡— ጎሽ፣ ጥሩ ጥያቄ ነው የጠየቅኸኝ፡፡ መጀመሪያ ምን ሚዛን አላችሁና ነው፡፡ እናንተ እኮ ሚዛን የሚመስላችሁ ዝም ብሎ የተሳከረ ህልማችሁንና ቅዠታችሁን ነው፡፡ ተቆጣሁህ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ በጭራሽ፣ አንድዬ!
አንድዬ፡— ለነገሩ ብቆጣስ! አሁን ወደ ጉዳዩ እንመለስና...ዛሬ የመጣኸው ሀፒ በርዝዴይ ልትለኝ ነው እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ተው አንድዬ፣ እንደሱ ስትል በቃ...
አንድዬ፡— ግዴለም፣ ግዴለም፣ በላ ንገረኛ ደግሞ አሁን ምን ተፈጠረ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን ያልተፈጠረ ነገር አለ አንድዬ፣ ምን ያልተፈጠረ ነገር አለ!
አንድዬ፡— እኮ ንገረኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እያየኸን ነገር ሁሉ ተሳከረብን እኮ፡፡ አንድዬ፣ ለምንድነው እንዲህ የጠመዱን፡፡
አንድዬ፡— ማን ነው የጠመዳችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ማን ያልጠመደን አለ። አሁንማ ለይቶላቸው ግንባር ገጥመው ይኸው ጋዜጣ አይቀራቸው፣  ቴሌቪዥን አይቀራቸው፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች አይቀሯቸው…. አንድዬ በቀላሉ ከጥይት ያልተናነሰ ዘመቻ እያካሄዱብን ነው፡፡
አንድዬ፡— ራሳችሁን መከላከል ነዋ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ስንቱን እንቻለው..
አንድዬ፡— ስማ ቅድም ስታነሳቸው የነበሩት አባቶቻችሁና አያቶቻችሁ እኮ ስንቱን ችለውታል፡፡ ዝም ብሎ በጦር በጎራዴ ታንክ የማረኩ ማለት ብቻ አይበቃም፡፡ ያንን መንፈስ ነው መያዝ ያለባችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምከረና አንድዬ...
አንድዬ፡— ምንድነው የምመክራችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እነኚህን ሁሉ ጠላቶቻችንን እንዴት እንደምንከላከል ምከረና...
አንድዬ፡— ጭራሽ እኔው መካሪ ልሁን!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ...
አንድዬ፡— ስማኝ፣ ምክር ሳይሆን መጀመሪያ ማወቅ ያለባችሁ ከውጭ የበዙትን ጠላቶች ከመመከት በፊት ራስን ማጥራት አይቀድምም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አልገባኝም፣ አንድዬ...
አንድዬ፡— እንዴት አይገባህም፣ መጀመሪያ የራሳችሁ ጠላቶች ራሳችሁ መሆናችሁን ማመን አለባችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አን...
አንድዬ፡— ቆይ አስጨርሰኛ፡፡ መጀመሪያ ነገር እናንተ መሀል ማን የማን ወዳጅ እንደሆነ፣ ማን የማን ጠላት እንደሆነ ታውቃላችሁ? ሳትዋሽ መልስልኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ አንድዬ..
አንድዬ፡— አየህ በአንድ ጊዜ መመለስ እንኳን አልቻልክም፡፡ ለምን እንደሆነ ልንገርህ...እናንተ ወዳጅና ጠላት የምትሉትን ለይታችሁ አታውቁም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ግን እኮ አንድዬ፣ የውጪዎቹ የጋራ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡
አንድዬ፡— እርስ በእርስ እየተጫረስክ የጋራ ጠላት ብሎ ነገር ምንድነው? ነው ወይስ ሌላው ከሚጨርሰን እኛው እንጨራረስ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አይደለም፡፡ ግን አንድዬ እንደው የውጭ ጠላት የለባችሁም ነው የምትለን?
አንድዬ፡— ወጣኝ፣ አሁን እንደዛ ወጣኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደሱ ማለቴ ሳይሆን...
አንድዬ፡— እንደውም ጥሩ ነገር አመጣህልኛ፡፡ አንዱ ትልቁ ችግር ይኸው ነው፤ ነገሮችን በራሳችሁ አረዳድ ነው የምትተረጉሙት፡፡ እናንተ እኮ ገና ጥያቄውን ሳትሰሙ መልስ አዘጋጅታችሁ የምትቀመጡ ናችሁ፡፡ ልትግባቡ ያልቻላችሁት እኮ ለዚህ ነው፡፡ እኔ ጋ እኮ አስር ጊዜ የሚያመላልስህ አንድም እርስ በእርስ ስለማትተማመኑ፣ ተነጋግራችሁ መግባባት ስለማትችሉ  ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱስ ልክ ነው...
አንድዬ፡— እንደው እኔም እንዳይደክመኝ አንተም ሳይመሽብህ ቤትህ እንድትደርስ በዚህ ይብቃንና ያው ሌላ ጊዜ መምጣትህ ስለማይቀር ያኔ እንጨዋወታለን፡፡ ዋናው ግን ሌላኛው ቤት ላይ ጣትን ከመጠቆም በፊት የራስን ቤት ማጽዳት ነው፡፡ ሰላም ግባ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1429 times