Saturday, 13 February 2021 13:09

የኢዜማ የምርመራ ውጤት ምን ያሳያል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  በመቀሌ፣ መተከል፣ ማይካድራ እና ኮንሶ የተሰማራው አጥኚ ቡድን ግኝቱን ይፋ አድርጓል
           

          መቀሌን ጨምሮ ባለፉት ወራት ግጭትና ጥቃት እንዲሁም የደህንነት ስጋት ወደተፈጠረባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች ቡድን ልኮ ማጥናቱን ያስታወቀው ኢዜማ፤ መንግስት በአካባቢዎቹ ተጨማሪ የማረጋጋት ስራዎች እንዲሰራ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ወደ መቀሌ፣ ኮንሶ፣ መተከል እና ማይካድራ ልኡክ ቡድን በመላክ የተፈጠሩ ችግሮችንና የአካባቢዎቹን ወቅታዊ ሁኔታ ለማጣራት ጥረት ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን የልኡካን ቡድኖቹም የየተሰማሩበትን አካባቢ ግኝት ከትናንት በስቲያ ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል።
ወደ መቀሌ የተጓዘው የጥናት ቡድን፣ በጦርነቱ ሳቢያ ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች የተጠለሉ ዜጎችንና የመንግስት አካላትን ማነጋገሩን አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ለተፈናቀሉት መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የልኡክ ቡድኑ መረዳቱን፣ ነገር ግን አሁንም የህጻናት አልሚ ምግብ፣ የመድሃኒትና  የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እጥረት እንዳለ መገንዘቡን አመልክቷል።
የልኡክ ቡድኑ ከተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ባሻገር ከመቀሌ ከተማ ወጣቶች ጋርም ለመወያየት መሞከሩን፤ በዚህም ወጣቶቹ በኤርትራ ወታደሮች ተፈጸሙ ያሏቸውን አሰቃቂ ጥቃቶች ለቡድኑ ማስረዳታቸውን፣ ህውኃት ቢወገድም የህዝቡን ስነ-ልቦና ለመጠገን ጊዜ እንደሚጠይቅ፣ አሁንም የህወኃት አመራሮች ይመጣሉ የሚል ተስፋ በተለይ በወጣቶቹ ዘንድ እንዳለ፣ አብዛኛው ወጣት ቀዬውን ለቆ መሸሹንና የት እንዳለ እንደማይታወቅ ከወጣቶቹ መረዳት እንደተቻለ የልዑክ ቡድኑ ሪፖርት ያስገነዝባል።
በአሁኑ ወቅት ፖለቲካውን ወደ ጎን ትቶ ሰብአዊ ድጋፍ ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ የኢዜማ ልዑክ ቡድን መረዳቱንና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እንዲሁም ከሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ሃላፊ አብርሃ ደስታ ጋር በተደረገው ውይይትም ድጋፎቹ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ መገንዘቡን አስታውቋል።
ከ1100 በላይ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ወደ ተጨፈጨፉባት ማይካድራ ያመራው ሌላው የኢዜማ የጥናት ቡድን፣ በአካባቢው የጅምላ መቃብሮችን፣ ለተለያዩ ጥቃት መፈጸሚያ የተዘጋጁ ድምጽ አልባ መሳሪያዎች የተከማቹባቸው ህንጻዎችን፣ ከፍተኛ ግጭት የተካሄደባቸውን ሥፍራዎችና የህወሃት ወታደራዊ  ካምፖች የነበሩ ቦታዎችን መጎብኘቱን አስታውቋል።
ስለ ሁኔታውም ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ የጥቃት ሰለባዎችና ወታደሮች መረጃ ማሰባሰቡን ጠቁሟል።
በማይካድራው ስለተፈጸመው የንፁሃን ጭፍጨፋ የተለያዩ አሃዛዊ መረጃዎች እንደሚነገሩ ያስታወቀው ቡድኑ፤ ሟቾች በጅምላ መቀበራቸውን መረዳቱን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ቂም በቀል ሳይኖር ማህበረሰቡ ሰላማዊ ህይወቱን እየመራ እንደሚገኝና ከተማዋ ሰላማዊ መሆኗን አመልክቷል።
ምንም እንኳ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እያጋጠመ ባይሆንም በሌሊት ዘረፋ እየተፈጸመ ስለመሆኑና አሁንም ሳምሪ የተባለው ቡድን ሙሉ ለሙሉ ስለመጥፋቱ ነዋሪዎች እርግጠኛ አለመሆናቸው ስጋት  እንደፈጠረባቸው መረዳት መቻሉን ነው ቡድኑ ያስታወቀው።
ከደህንነት ስጋቱ ባሻገር የመሰረተ ልማት አለመኖርና ተቋማት ሙሉ አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸው ችግር መፍጠሩንም የቡድኑ ሪፖርት ይጠቁማል።
ሌላው ወደ ኮንሶ ያመራው የኢዜማ ቡድን በበኩሉ በኮንሶ በተለይ ከድንበር አከላለል ጋር በተያያዘ በየጊዜው የሚፈጠረው ግጭት የበርካቶችን ህይወት መቅጠፉን በዝርዝር አስረድቷል።
በኮንሶ በተፈጠሩ ግጭቶች በርካቶች ከመሞታቸው ባለፈ በአጠቃላይ 9,541 የሳር ቤቶች፣ 1871 የቆርቆሮ ቤቶች ፣ 198 ሺ 418 ኩንታል እህል፣ 64 ሺ 381 የቤት ውስጥ ቁሳቁስ፣ 33 ሺ 566 የእርሻ መሳሪያዎች፣ 32 ሺ 345 የቁም እንስሳት እና 12 ወፍጮ ቤቶች መውደማቸውን እንዲሁም 84 ሺ 244 ዜጎች መፈናቀላቸውንና 51  ሺህ ያህሉ ቤት ንብረታቸው ሙሉ ለሙሉ እንደወደመባቸው  መረዳቱን ቡድኑ አስታውቋል።
በአሁን ወቅት በኮንሶ የምግብ እጥረት፣ የተፈናቃዮች ከእንስሳት ጋር በአንድ መጠለያ አብሮ መኖር፣ የሚሞቱ ሰዎች መብዛት፣ የታጠቁ ሃይሎች የሚያደርጉት ዘረፋ፣ የት/ቤቶች መዘጋትና አሁንም የተኩስ ልውውጥ አለመቆሙ አሳሳቢ መሆኑን ሪፖርቱ ያትታል። በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ሰላም አስከባሪ ሃይል በቁጥር አናሳ መሆን ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ እንዳያገኙ እንቅፋት መሆኑም ተመልክቷል።
በመተከል ዞን ደግሞ በአሁኑ ወቅት 44 ቀበሌዎች ወታደራዊ ጥበቃዎች እንደሚያስፈልጋቸውና  በ22 ያህሉ ላይ ጠንካራ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች እየተካሄዱ መሆኑን ማረጋገጡን ወደ ስፍራው የተጓዘው የኢዜማ ቡድን አስገንዝቧል።
በመተከል በተፈጠረው ግጭት ከሞቱት በርካቶች ባሻገር 126ሺህ ዜጎች መፈናቀላቸውን ከእነዚህ ውስጥም 15 ሺህ ያህሉ ብቻ ወደቀያቸው መመለሳቸውን የጠቆመው የቡድኑ ሪፖርት፤ በዚህም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ሰብአዊና ማህበራዊ ቀውስ መፈጠሩን ያመለክታል።
በዞኑ አፋጣኝ እርዳታ ማድረስ እንደሚገባም በሪፖርቱ ተመልክቷል።
በአጠቃላይ ኢዜማ ባቀረበው ምክረ ሃሳብ፤ በትግራይና መተከል ላለው የሰብአዊ ድጋፍ  ሁሉም እንዲረባረብና የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን መገናኛ ብዙሃንም ተገቢውን ሽፋን እንዲሰጡ አሳስቧል።
በትግራይ ክልል የተጠናከረ መደበኛ የፀጥታ ሃይል በአፋጣኝ እንዲዋቀርም ኢዜማ ጠይቋል። በአጠቃላይ የመንግስት ፀጥታ አካላት በተደጋጋሚ ንፁሃን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ሳይፈጸሙ የሚያስቆሙበትን ብቃት እንዲያዳብሩ፣ ስጋት ውስጥ ላሉ በአፋጣኝ እንዲደርሱላቸውና ስጋቶችን እንዲቀርፉ ኢዜማ ጥሪ አቅርቧል።




Read 1945 times