Monday, 15 February 2021 00:00

ምን በዛ? አደገኛ ባለስለት አጥር!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

     • የፖለቲካ ዲስኩር ሌላ፤ የኑሮ ተግባር ሌላ!
        • ወይ የህግ ከለላ ይኖርሃል። ወይ በስለት አጥር ራስህን ትከልላለህ።
        • “የጋራ ማንነት”፣”የብሔረሰብ ማንነት” የሚል ወሬ ሲበዛ፣ የግል መኖሪያውን በእሾህ በስለት አጥሮ የሚመሸግ ሰው ይበረክታል። ታዲያ፣ የግቢ        አጥር ለጊዜው ቢጠቅምም፣ ያለ ህግና ስርዓት፣ አገር አይዘልቅም። በአጥር ብቻ፣ ኑሮ አቀናም፤ ሰላምም አይገኝም። እስቲ፣ ገዢው ገዢው ፓርቲና
    ተቃዋሚዎች፣ ለምርጫ ምን እንደሚሉ እንሰማለን፤ “ህግን አክብሮ ማስከበር” ዋና አላማ ከሆነ እናያለን።
               
          ሃሳብ ከእውነታ ጋር ሲጣላ፣ ፖለቲካ ከህልውና ጋር ሲጣረስ፣ የቤቱን አጥር በእሾህ እየጠቀጠቀ ግቢውን ለመከርቸም ተፍተፍ የሚል ሰው ይበረክታል። በየከተማው፣ ከቤቱ አስበልጦ፣ አጥሩን ለማስረዘም፣ ቀና ደፋ የሚል ነዋሪ እየበዛ ይሄዳል። በላዩም ላይ፣ የጠርሙስና የብርጭቆ ስብርባሪ ያርከፈክፍበታል።
ዛሬ ዛሬ ደግሞ፣ የስለታማ አጥር ገበያ ደርቷል። ድሮ ድሮ በኤምባሲዎች ላይ ነበር የሚታየው። አሁን ግን፣ በየመኖሪያ ቤቱ፣ በትንሹም በትልቁም፣ የስለታማ አጥር መቀነት፣ በድርብ በድርቡ ሆኗል። በረዥሙ የተሰራ ግንብ አልበቃ ብሎ፣ ጥልፍልፍ ስለታማ አጥር እየተጨመረበት ነው። ባለ ኤሌክትሪክ የሽቦ አጥርም ይታከልበታል። የዘመናችን የአጥር ጥልፍና ጥለት በሉት።
ከእሾህና ከግንብ በተጨማሪ፣ አጥር ላይ፣ አደገኛ ባለስለት ጥልፍ ለመስራት የሚፍጨረጨሩ ሰዎች ቢበረክቱ፣ አይፈረድባቸውም። የሚሰሙትና የሚያዩት ነገር፣ ከእውነታና ከኑሮ ጋር ቢጣረስባቸው ነው። “ወሬ ሌላ፣ ኑሮ ሌላ” ቢሆንባቸው ነው።  
በየዕለቱ፣ ነጋ ጠባ የምንሰማቸውን ዲስኩሮች ተመልከቱ። አንድ የጋራ ባሕርይ አላቸው። “ለግል ኑሮና ለግል ህልውና”፣ ቅንጣት ክብር አይሰጡም። እንዲያውም፣ “የግል” የተባለውን ነገር ሁሉ የማጣጣልና የማንቋሸሽ ስብከት ይመርቁበታል። ማለትም፣ እርግማንና ውግዘት ያወርዱበታል።
የግል ማንነንትና የግል ህልውናን ለማጣጣል፣ እሽቅድምድም ሞልቷል። “የጋራ ማንነት፣ የብሔር ማንነት”፣…. ምናምን እየተባለ፣ ያለእረፍት በጅምላ የሚጎርፈው ጭፍን ዲስኩር፣ እየተመነዘረ የሚቸረቸረው የተሳከረ የወሬ መዓት፣ ስፍር ቁጥር የለውም። የግል ማንነትን የሚያብጠለጥል የስካር ሃሳብ፣ በምሁራን ይሰበካል፣ በፖለቲከኞች ይደሰኮራል።
ብዙ ሰውስ፣ ይህን ሁሉ ሰምቶ ምን ያደርጋል? በግል፣ ወደ ቤቱ ሄዶ፣ የግቢ አጥር ያስረዝማል። አንዳንዱ ሰው፣ የዘረኝነት ሃሳብ ባይጥመውም፣ ሌላ የተሻለ ትክክለኛ ሃሳብ በማጣት፣ በዝምታ ይሰማል። አንዳንዱ ሰው፣ በአላዋቂነት ሳቢያ፣ ወይም ብልጣብልጥ የሆነ እየመሰለው፣ ከነፋሱ ጋር ይነጉዳል፣ አጨብጫቢ ሆኖ ያዳምቃል - የብሔር ማንነት፣ የጋራ ማንነት እያለ ይዘፍናል። አንዳንዱ ሰው ደግሞ፣ በዘረኝነት ሜዳ ውስጥ፣ የተቀናቃኝ ጎራ አስተባባሪና አራጋቢ እየሆነ ያጫፍራል።
ምኑ ይዘረዘራል? እያያችሁት አይደል? የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካና ዲስኩር ነግሷል። ወሬው ሁሉ “የብሔር ማንነት” በሚል መፈክር ተጥለቅልቋል። ይሄ፣ በጭፍንነት የተደናበረ የፖለቲካና የዲስኩር ዓለም ነው፣ የተሳከረ የምናብ ዓለም  ነው። አብዛኛው ሰው ይህን ሲሰማ ውሎ፣  ወደ ኑሮ ዓለም ሲመለስስ?
“የጋራ ማንነት”፣ “የብሔር ማንነት”፣…. የምር ለኑሮው እህል ውሃ እንደማይሆንለት ይገባዋል - አብዛኛው ሰው። መቼም፣ የግል ኑሮውን ትቶ፣ የጋራ ጎጆ ለመስራት፣ የብሔረሰብ ድንኳን ለመዘርጋት ጠብ እርግፍ ሲል አታዩትም።
የግል ጎተራውን ወይም ጓዳውን ትቶ፣ የብሔር ጎተራ ለመስራትና በእህል ለመሙላት ተፍተፍ የሚል ሰው፣የትም የለም ማለት ይቻላል። እስከዛሬ አልታየም። የብሔረሰብ መጋዘን ለመገንባትስ ይሟሟታል? እህሉንና ንብረቱን የጋርዮሽ፣ የግል የባንክ ሂሳቡም የብሔር ብሔረሰብ ሂሳብ እንዲሆንለት “ሕዝባዊ ጥያቄ” የሚያቀርብ፣ ሆ ብሎ ለሰልፍ የሚንጋጋ ሰው አጋጥሟችኋል?
ኑሮዬ፣ ቤቴ፣ ንብረቴ፣ ሃብቴ፣ ደሞዜ ሁሉ… “የጋራ የህዝብ ይሁን” ብሎ፣ የቤቱን በር የሚገነጥል፣ ግቢውን አጥር የሚያስፈርስ ሰው እስከ ዛሬ አልተፈጠረም። ወደዚያ ደረጃ ገና አለመዝቀጣችን ተመስገን ነው።
በእርግጥ፣ እንደ አያያዛችን፣ ወደለየለት አዘቅት መውረዳችን አይቀርልንም። “የጋራ ማንነት” “የብሔር ማንነት”፣ “የሃብት ክፍፍል”፣ “ማህበራዊ ሃላፊነት”፣ “ህዝባዊነት”፣… በሚባሉ የስካር ሃሳቦች እየተደናበርን፣ እንዴት ከጥፋት እንድናለን? የእስከዛሬውን ትርምስና ጥፋት ማየት ትችላላችሁ።
እንዲያም ሆኖ፣ አብዛኛው ሰው፣ “የሙሉ ጊዜ ስካር” ውስጥ ለይቶለት አልገባም። በኑሮና በተግባር፣ “ለግል ማንነት ፣ ለግል ሃላፊነት” የተወሰነ ያህል ክብር አለው።”የጋራ ማንነት”፣ “የብሔር ማንነት”… ለወሬና ለዲስኩር ይመስለዋል። እናም የስካር ሃሳቦችን፣እህ እያለ ይሰማል። ያወራም ይሆናል። ከምር ወደ ኑሮ ጉዳይ ሲመጣ ደግሞ፣ የግል መኖሪያ ቤቱን በእሾህ ያጥራል። ለምን?
“የሰው ማንነት” ማለት፣ በዋናነት “የግል ማንነት” ማለት እንደሆነ፣ ከተግባርና ከኑሮ ይታዘባላ። የሰው ብቃትና ቀሽምነት፣የግል ናቸው፡፡ አምራችና አምታች.፣ ሙያተኛና ቀማኛ፣ እውነተኛና ውሸታም፣… የግል ማንነት እንደሆኑ፣ “የዘር የብሔር ማንነት” ብሎ ነገር እንደሌለ፣ በተግባር እንኖረዋለንና። በየቦታው እስር ቤት የሚገነባው፣ለምን ሆነና! ከውጭ አገር የሚመጡ ወንጀለኞችን ለማሰር ነው እንዴ? በሁሉም ቦታና ሁሉጊዜ በሰዎች ዘንድ፣ ንፁህ አምራችና ዘራፊ ወንጀለኛ እንደሚኖር በተግባር በማየት ነው፤ በየአገሩ በየወረዳው እስር ቤትን መገንባት የግድ የሚሆነው፡፡
“እዚህ አካባቢ፣ የሌላ ብሔረሰብ ተወዳጅ የለም” ማለት፣ እስር ቤት አይኑር ማለት ነው? እንዴት ተደርጎ!አዳሜ፣ መኖሪያ ጎጆውን፣ እርሻውንና ጎተራውን ከፍቶ ያድራል?... “ሁሉመናዬ የብሔር ብሄረሰብ ይሁን!” ብሎ ዙሪያ ገባውን ይጋብዛል? ለፖለቲካ ዲስኩርና ለወሬ እንደዚያ ሊሆን ይችላል። ኑሮ ላይ ግን፣ የግል ኑሮውንና አጥሩን ለማጠናከርና ለማስከበር ይሞክራል… አብዛኛው ሰው። የእሾህና የጠርሙስ ስብርባሪ፣ ከተቻለም፣ ጥልፍልፍ ባለስለት ወይም ባለ ኤሌክትሪክ አጥር የሚበረክተውም ይሄኔ ነው። ለምን ቢባል፣…
“የግል ማንነትንና የግል ህልውናን የሚያንቋሽሽ አስተሳሰብ” በተስፋፋ ቁጥር፣ የግል ኑሮ ላይ አደጋ ይበረክታል። “ያንተ ቤት የኔም ቤት ነው”፣ “ያንተ ንብረት፣ የኔም የጋራችን የብሔረሰባችን ንብረት ነው”፣ “የኔ እዳ፣ ያንተም እዳ ነው”፣ “የኔ አመፅ፣ የጋራ የሕዝብ አመፅ ነው”… እያለ ለዝርፊያና ለውድመት የሚዘምት ወንጀለኛ ሲበረክት ምን ይደረግ?
አዳሜ፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ የመኖሪያ ቤት አጥር ለማጠናከር ቢሞክር ይፈረድበታል?
“ለግል ጥቅም አታስብ። ለህዝብ ቅድሚያ ስጥ። የሌሎች ሰዎችን ጥቅም አስቀድም” የሚል ዲስኩር ይሰማል። በዚህ ዲስኩር ስሌት፣ አምራችና አምታች ሰዎች እንደ እኩል ነው የሚታዩት። ራስ ወዳድ ተብለው ይወገዛሉ።
በጥረት ንብረት የሚያፈራ ታታሪ ሰውና፣ ንብረት የሚሰርቅ ቤት ሰርሳሪ ሰው፣ ልዩነት የላቸውም? ሰራተኛንና ቀማኛን ለይቶ የማይመለከት፣…
“ራስ ወዳድ አትሁን” የሚል ነው ዋነኛው የአገራችን መጥፎ ዲስኩር። “እኔ አትበል፤ እኛ በል” የሚል ነው የአገራችን ስብከት።
ይህን ሲሰማ የሚውል ብዙ ሰውስ? አዎ፣”እኔ፣የኔ አትበት” የሚሉ ዲስኩሮችን ይሰማል። ነገር ግን፣ “የኔ” የሚለውን መኖሪያ ቤት ቢኖረው ይመኛል። ለመስራትም ይጣጣራል። ከተሳካለትም፣ የስራ ውጤቱን ከአደጋ ለመከላከል ፤ በአደገኛ ባለስለት አጥር ዙሪያውን እየደራረበ ቢያጥር ይፈረድበታል? የግል ንብረት፣ ለብዙ አደጋ የተጋለጠ እንደሆነ ይገባዋል… “የኔ አትበል፤ የኛ በል” እየተባለ ሲለፈፍ እለት በእለት ሲሰማ እየዋለ፣ ስጋት ቢያድርበት ይገርማል?
በአንድ በኩል፣ የግል ማንነትንና የግል ህልውናን የሚጣጥል፣ አደገኛ የዘረኝነት ሃሳብና ዲስኩር ነግሷል። “የብሔር ማንነት፣ የጋራ ማንነት” የሚሉ ፈሊጦች ይራገባሉ።
በሌላ በኩል፣ “የግል ጥቅምን ሳይሆን የህዝብን ጥቅም አስቀድም። የኔ ሳይሆን የኛ በል። እኔነት ይወድማል፤ እኛነት ያሸንፋል” የሚል ዲስኩር ይዥጎደጎዳል።
ምን ይሄ ብቻ!
“ለዚህ አለም ኑሮ አታስብ፣ አትስራ። የዚህን ዓለም ሃብትና ንብረትን አትመኝ” በማለት የግል ኑሮንና ንብረትን የሚያጣጥል ስብከትም አለ። በዚህ ላይ፣ አዲስ ፈሊጥ ተጨምሮበታል።
“ዲሞክራሲዊነትና ብዝሃነት” በሚሉ መፈክሮች፣ ማንኛውም ነገር፣ “በውይይት፣ በድርድርና በህዝባዊ የጋራ ውሳኔ” አማካኝነት መካሄድ አለበት እያለ የሚሰብክ ምሁር ሞልቷል።
ሁሉም ነገር በድርድር? “የገበያ ዋጋ ድርድር” የሚኖረው፣ በቅድሚያ፣ የግል ንብረት ሲኖር ነው። የግል ንብረት፣ ያለድርድር ከተከበረ ብቻ ነው፤ የዋጋ ድርድር የሚኖረው፡፡ በዘመነኛው ፈሊጥ ግን፣ ለድርድር የማይቀርብ ነገር የለም። እንግዲህ በአስቡት፡፡ በግል ንብረትህ ላይ ማንም ሰው መጥቶ “እንደራደር” የሚልህ ከሆነ፣ ምን አማራጭ ይኖራል?
የእሾህ አጥር ወይም ባለስለት አጥር ለመዘርጋት የሚሯሯጥ ሰው ቢበዛ ይገርማል?
ብቻ ምን ልበላችሁ?
የግል ማንነትና የግል ህልውና ላይ፣ የግል ስራና ኑሮ፣ የግል ንብረትና ሃብት ላይ፣ አደጋውና ዘመቻው እየከፋ መጥቷል። ለጥቃት ለወንጀል፣ ሰበብና ማምከኛው ተትረፍርፏል። የግል ማንነትና የግል ኑሮ ማጣጣያ የፖለቲካ ዲስኩርና የተሳከረ አስተሳሰብ በዝቷል።
በዚያው ልክ፣ የህግ አስተማማኝነት እየመነመነ እየሟሸሸ ይሄዳል። የግል ማንነትን የሚያኮስስ አስተሳሰብ ሲራገብ፣ በዚው ልክ የግል ሃላፊነትና የግል ተጠያቂነት ይጠፋል። “የህግ ዳኝነትና የፍትህ ውሳኔ” በተፈጥሮው፣ የግል ማንነትና የግል ሃላፊነት ከሌለ፣ ዋጋ አይኖረውም።
የህግ አስተማማኝነት ሲመናመን፣ የህግ ጥበቃና የህግ ከለላ ሲሳሳ፣ ምን አማራጭ አለ? የእሾህና የስለት አጥር?
ታዲያ፣ የግቢ አጥር ለጊዜው ቢጠቅምም፣ ያለ ህግና ስርዓት፣ አገር አይዘልቅም። በአጥር ብቻ፣ ኑሮ አቀናም፤ ሰላምም አይገኝም።
እስቲ፣ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች፣ ለምርጫ ምን እንደሚሉ እንሰማለን፤ “ህግን አክብሮ ማስከበር” ዋና አላማ ከሆነ እናያለን።


Read 11183 times