Saturday, 13 February 2021 12:14

2 ማስኮችን ደራርቦ መጠቀም ኮሮናን በእጥፍ ይከላከላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      የአሜሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል አንድ ማስክ ከማድረግ ይልቅ 2 ማስኮችን ደራርቦ መጠቀም የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ በእጥፍ ውጤታማ እንደሆነ በምርምር ማረጋገጡን ይፋ እንዳደረገ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ማዕከሉ በላቦራቶሪ ባደረገው ምርምር አንድ ከጨርቅ የተሰራ ወይም ሰርጂካል ማስክ ብቻ በማድረግ 40 በመቶ ያህሉን ቫይረስ መከላከል ሲቻል፣ ሁለቱንም አይነት ማስኮች ደራርቦ ማድረግ ደግሞ 80 በመቶ ያህሉን ቫይረስ ለመከላከል እንደሚያስችል የሚያሳይ ውጤት ማግኘቱን ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሁለት ሰዎች በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው ሁለቱም ማስኮችን ደራርበው ሲያደርጉ 95 በመቶ ያህሉን ቫይረስ መከላከል እንደሚችሉ በጥናቱ ማረጋገጡን የጠቆመው ማዕከሉ፤ ያም ሆኖ የማስክ እጥረት ስለሚያስከትል ከተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች በስተቀር ሁሉም ሰዎች ማስኮችን ደራርበው ማድረግ እንደማይጠበቅባቸውም ምክሩን ለግሷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፤ በኮሮና ቫይረስ መነሻ ዙሪያ ምርመራ ለማድረግ በቻይና የነበረውን ቆይታ ያጠናቀቀው የአለም የጤና ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን፣ ቫይረሱ በቻይና ከሚገኝ ላቦራቶሪ አምልጦ በመውጣት ወደ ሰዎች ተሰራጭቷል የሚለውን ጥርጣሬ አጣጥሎታል፡፡
ቫይረሱ በተገኘባት የቻይናዋ ውሃን ግዛት ምርመራውን ያደረገው ቡድኑ ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ እንዳለው፣ ቫይረሱ ከላቦራቶሪ የወጣ ነው የሚለው ጥርጣሬ መሰረተ ቢስ እንደሆነ የሚያመለክቱ መረጃዎችን ለማግኘት ተችሏል፤ ያም ሆኖ ግን ሌሎች ሶስት መላ ምቶችን ግን አሁንም ድረስ ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
የቫይረሱን መነሻ በተመለከተ አራት መላምቶች ሲሰጡ መቆየታቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤ እነሱም ከእንስሳት በቀጥታ ወደ ሰዎች የተላለፈ ነው፤ ከእንስሳት በሌላ አስተላላፊዎች አማካይነት ወደ ሰዎች የተሰራጨ ነው፤ ከሌላ አካባቢ ወደ ቻይና የገባ ነው እንዲሁም ከላቦራቶሪ አምልጦ የወጣ ነው የሚሉ መሆናቸውን አስታውሷል፡፡
ቫይረሱ ወደ ሰዎች የተሰራጨው ከእንስሳት መሆኑን የጠቆሙት የቡድኑ መሪ ፒተር ቤን ኢምበረክ፤ያም ሆኖ ግን ትክክለኛውን የቫይረሱን መነሻ ለማወቅ በቀጣይ ተጨማሪ ጥናትና ምርመራዎች መደረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ በጋና ፓርላማ የህዝብ ተወካዮችንና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ168 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው መረጋገጡን ተከትሎ ፓርላማው ለሶስት ሳምንታት ያህል እንዲዘጋ መወሰኑን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በቫይረሱ ከተጠቁት መካከል 17 ያህሉ የፓርላማ አባላት ሲሆኑ 151 የሚሆኑት ደግሞ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ፓርላማው ባለፈው ማክሰኞ እንዲዘጋ መወሰኑንና የጽዳት ስራዎች ሊሰሩ መታቀዱንም አክሎ ገልጧል።
ከወደ ፈረንሳይ በተሰማው ሌላ በጎ ዜና ደግሞ፣ በአሁኑ ወቅት በአለማችን የረጅም እድሜ ባለጸጋ እንደሆኑ የተነገረላቸውና በኮሮና ቫይረስ የተጠቁት የ117 አመቷ መነኩሲት ሉሲሊ ራንደን ከበሽታው ማገገም መቻላቸው ተነግሯል፡፡
በእድሜ ከአለም ሁለተኛ ከአውሮፓ አንደኛ የሆኑትና በጥር ወር አጋማሽ ላይ በቫይረሱ መጠቃታቸው የተነገረው አይነስውሯ ሉሲሊ ራንደን በአሁኑ ወቅት ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ማገገማቸውን የዘገበው ቢቢሲ፣ መነኩሴቷ በሚኖሩበትና በደቡብ ፈረንሳይ በሚገኘው የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ውስጥ ልደታቸውን ለማክበር እየተዘጋጁ መሆኑንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 3475 times