Saturday, 13 February 2021 11:11

የምሽት ጭፈራ ቤቶች የነዋሪዎቹን ሰላም እያወኩ ነው ተባለ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 የወረዳው አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ “ሁኔታው ከአቅሜ በላይ ሆኗል” ብሏልየነዳጅ
              በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ ቦሌ መሰናዶ ት/ቤት ጀርባ የሚኖሩ ነዋሪዎች አካባቢያችን ላይ በተከፈቱ በርካታ የምሽት ጭፈራ

ቤቶች ምክንያት መኖር አልቻልንም ሲሉ አማረሩ። በደርግ ዘመን ከተለያዩ የመንግስት መ/ቤቶች የተውጣጡ 25 ማህበራት በመኖሪያ ቤትነት
የገነቡትና 25ቱ አፓርትመንቶች ነዋሪዎች ማህበር እየተባለ የሚጠራው አካባቢ 35 ዓመታትን ያስቆጠረና እጅግ ሰላም የሰፈነበት አካባቢ
እንደነበረ ገልጸው፣ በህይወታችን ላይ እክል የገጠመንና መረበሽ የጀመርነው በ1991 ዓ.ም የተካሄደውን የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት መጠናቀቅን
ተከትሎ ነው ይላሉ።
እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ከሆነ መንግስት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለነበራቸው የመከላከያ መኮንኖችና የደህንነት ሰራተኞች
በጦርነቱ ላበረከቱት አስዋጽኦ ከቦሌ መሰናዶ ት/ቤት 5 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በመቀነስና  ቀድሞ የቦሌ መድኃኔዓለም ጥምቀተ-ባህር የነበረውን
ቦታ ወስዶ ለነዚህ የጦር መኮንኖችና የደህንነት ሰዎች ለእያንዳንዳቸው 500 ካ.ሜ ቦታ  ለመኖሪያ  ቤት ግንባታ እንደሰጣቸው ነዋሪዎቹ
ይናገራሉ።
“ለሀገራቸው ህይወታቸውን ለሰጡ ሰዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መንግስት መስጠቱ ባልከፋ” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ይህንን
ተከትሎ እነዚህ በኮሎኔል እና በብ/ጀነራልነት ማዕረግ ላይ ያሉ የመከላከያ መኮንኖች፣ የደህንነት ሰዎች፣ ሲቪል ሚኒስትሮችና ሚኒስትር
ዲኤታዎች ለመኖሪያ የተሰጣቸውን ቦታ ሰርቪስ ቤቶችን እየጀመሩና ሙሉ 500 ካ.ሜ ቦታ እንደመጋዘን እየደፈኑ ማከራየት መጀመራቸውና
ተከራዮቹም የሌሊት ጭፈራ ቤቶች  እያደረጉ የነዋሪዎቹ ህይወት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሰላም ማጣቱን ይናገራሉ።
ነዋሪዎቹ በተለያየ ጊዜ ለወረዳው ሃላፊዎች ቅሬታ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን የገለጹ ሲሆን በተለይ ከለውጡ በፊት አከራዮች የመከላከያ
መኮንኖች ስልጣናቸውን  በመጠቀምና ተከራዮቹም የአከራዮቻቸውን ስልጣን ተጠቅመው በማስፈራራት ለወረዳው መንግስት ባስልጣናት
ፈተናና እንቅፋት ሆነው መክረማቸውን ነው የተናገሩት።
ከለውጡም በኋላ ይሄው የምሽት ክበብ ጩኸትና ሁካታ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚረብሻቸው የገለፁት ነዋሪዎቹ የሺሻ ቤት መስፋፋት የቦሌ
መሰናዶ ት/ቤት ተማሪዎች በአጥር እየዘለሉ ሺሻ ቤት በመግባት ከትምህርታቸው እየተስቲጓጎሉ በመሆናቸው መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ
እርምጃ ሊውሰድ ይገባዋል ብለዋል፡፡
ይህንን ተከትሎ ለወረዳው፣ ለክፍለ ከተማውና  ለወረዳ የህዝብ  አቤቱታና ቅሬታ  ሰሚ ኮሚቴው አቤቱታ ብናቀርብም የመጣልን መፍትሄ
የለም፡፡ በአንድ በባለ ስድስት ወለሉ ብሌን ህንፃ ላይ ብቻ እንኳን “ፐርል” የምሽት ክበብ “ፖሽ” የምሽት ክበብና “ኮምፓውንድ ላውንጅ”
የተሰኙ 3 የምሽት ክበቦች አሉ። ነዋሩዎቹ አካባቢው 95 በመቶ ወደ ጭፈራ ቤትነት ተለውጦ ሰላማችንን አጥተናል ሲሉ የአማረሩ ሲሆን ከቦሌ
መሰናዶ ት/ቤት በተጨማሪ በዚሁ አካባቢ ጊብሰን አካዳሚ የተሰኘ ታዳጊዎች የሚማሩበት ት/ቤት በመኖሩ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንገኛለን
ብለዋል።
ከ10 ዓመት በፊት በባርና ሬስቶራንት ፈቃድ ያወጣውንና  አሁን በዲጂና በቀጥታ ሙዚቃ የጭፈራ ቤት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውን
በእምነት ባርና ሬስቶራንትን ጨምሮ በአሁኑ ሰዓት “ኤክሶ ኤክሶ” ፓራጎን እና ኦርጋኒክ የሚባሉ በርካታ የምሽት ክበቦች ተከፍተዋል።
አንዳንዶቹ በወረዳው ተከስሰው እስከመዘጋት ቅጣት የተጣለባቸው ቢሆኑም ተመልሰው ተከፍተው ረብሻና ጩኸታቸውን መቀጠላቸውንና
ነዋሪዎቹ ከነህፃናት ልጀቻቸው አንቅልፍ አጥተው እንደሚድሩ ተናግረዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ አክለውም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 52/2009 መሰረት የፀደቀው 10ኛው
መዋቅራዊ ፕላን መሰረት ከትምህርት ቤቶች 500 ሜትር ክልል ውስጥ ምንም አይነት የምሽት ጭፈራ ቤት፣  ባር (ቡና ቤት)፣ጫት ቤት፣ ማሳጅ
ቤትና ሺሻ ቤት መክፈት የተከለከለ ነው የሚለውን አዋጅ በመቃረን የሚሰራው ትውልድ አምካኝ ስራ እንዲቆምና መንግስት ነዋሪዎቹን
ከሁከት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡን ለቦሌ ክፍለ ከተማ የህዝብ አቤቱታና ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ነስረዲን አሜን ደውለን
በሰጡን ምላሽ በኗሪዎች የቀረበው ቅሬታ ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ መሆኑን አምነው አጠቃላይ ትንተና ተሰርቶ ለድምጽ ብክለት ቁጥጥር
ተመርቷል። በአስተዳደር ኮሚቴም ታቷል። አንዳንዶቹን ከስሰን እያሳሸግን ሲሆን ተጠሪነታችን ለክፍለ ከተማው ስራ አስፈጻሚ በመሆኑ
ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እየሰራን ነው ብለዋል።
የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 3 የህዝብ ቅሬታና አቤቲታ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል በቀለ መርሻም በበኩላቸው “አካባቢው ሙሉ ለሙሉ
በሚባል ደረጃ ወደ ጭፈራ ቤትነት ተለውጧል” ያሉ ሲሆን ጉዳዩን ከአቅም በላይ ያደረጉብን ተግዳሮቶች ገጥመውናል ይላሉ። አንደኛው
እነዚህ የምሽት ክበቦች በቀን አለመሰራታቸው፣ ሁለተኛው በማታ ደንብ አስከባሪ ስንልክ ከእኛው ባልደረቦች ውስጥ ቀድሞ ለምሽት ክበብ
ባለቤቶች መረጃ በመስጠት እዛ ስንደርስ ድምጽ እየቀነሱ ማስቸገራቸው ሲሆን ሲረብሹ ደርሰን ፍ/ቤት ከስሰን ካሳሸግነው በኋላ ከአራዳ
ፍ/ቤት 1ኛ ምድብ ችሎት ከታሸገም እንዲከፈት ካልታሸገም እንዳይታሸግ የሚል ማዘዣ እያመጡ ቤቶቹን እንደሚያስከፍቱና የፍ/ቤትን ትዕዛዝ
መጣስ የሚያመጣውን ችግር እያየን መስራት አልቻልንም ብለዋል፡፡ በማሳጅ ቤት ስም የሚሰራውን ነውር፣ በምሽት  ክበብ የሚፈጠረውን
ረብሻ ለማስቆም በይግባኝ እስከ አዲስ አበባ ም/ቤት ጉዳዩ መድረሱንም ተናግረዋል።
የህጉና የመዋቅሩ አወቃቀር መወሳሰብ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንቅፋት ሆኖብናል ያሉት አቶ ዳንኤል፣ በቀጣይ ከክ/ከተማው ስራ
አስፈጻሚና ከሚመለከታቸው የበላይ አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ለመቅረፍ በትግል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።


Read 2150 times