Saturday, 06 February 2021 14:13

...I put a spell on you...

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ...’cause you’re mine... “ ትላለች Nina Simone...
እኔ አይኔን ጨፍኜ በሷ ድምፅ እሰማዋለው ዘፈኑን...
የኔ ቆንጆ ፍፁም ነች!
Nina በድምፅ እንኳን አጠገቧ አትደርስም... በኔ perfect አለም “I put a spell on you... ‘cause you’re mine...” የምትለኝ እሷ ነች...ጆሮዬ ስር...
አንገቴን የሶፋዬ መደገፊያ ጠርዝ ላይ እየወጠርኩ ተንጠራርቼ ሰፊውን የሳሎኔን ጣሪያ እቃኛለው... ሙሉ ቤቴን እሷው ነች... ፈገግ ስትል እንደ ጂኒ ከጥርሷ ተፈልቅቆ የሚወጣ ግዙፍ ውበት አላት... ቤት... ሰፈር... ሀገር የሚያክል...
ብትኖር... አቅፌያት ቢሆን ኖሮ ምን አባቴ ይውጠኝ ነበር? አንድዬ ሲያስብልኝ የሌላ ናት!
እኔ አስቃታለው... ትን እስኪላት ሆዷን በእጆቿ ደግፋ ፍርፍር እስክትል አስቃታለው... እኔ ስቀልጥ... እሷ ሲደክማት “ፍቅር ደወለ...” ብላ እብስ ትላለች...
እሱን ብሎ ፍቅር...
እኔ እኩያዋ፣ አጫዋቿ፣ ጓደኛዋ ነኝ...
እሱ አስተዋይዋ፣ አፍቃሪዋ፣ ፍቅረኛዋ ነው...
እንደሷ አይነት መልዓክ ከእንደሱ አይነት ጭራቅ እንዴት እንደሚገጥም አይገባኝም። ቁጣውን ስትታገስ ቱግ እል፣ እቆጣና ደግሞ ተናግሬ እንዳላጣት ንዴቴን ዋጥ አድርጌ እፈግጋለው።
ጭንቅላቴ ውስጥ ስንት ጠርሙስ አናቱ ላይ እንዳፈረስኩ መድሐኒዓለም ነው የሚያውቅ...
ትወደዋለች...
ብዙ ትወደዋለች...
ሱቋን 10:30 ዘግታ 11:00 እስኪል ስልኳ ላይ አፍጣ ነው ምትጠብቀው... ተንደርድራ ልትለጠፍበት...
እቤቱ ይዟት እንዲሄድ ስትለማመጥ ሳይ ጥውልውል ያደርገኛል...
አንድ ጊዜ ጨብ ብላ አንሶላው ላይ የሌላ ሴት ጠረን እንዳለ አጫውታኛለች... ጓደኛዋ ነኛ...
እሷ ግዷ አይደለም... ዋናዋ የሱ ጠረን ነው... የሆነ Intimately Beckham የሚባል ሲጃራ ሲጃራ የሚል ሽቶ ይቀባል... ስለምናባቱ ጠረን እንደምታወራ አይገባኝም... ባይገባኝም አያገባኝም... እወዳታለው!
አንድ የከፋት ቆንጆ ቀን አንገቴ ስር ተወትፋ ቀና ብላ እያየችኝ ትንፋሿ ቅርብ ብሎ ሲያጓጓኝ ድክም ብዬ አፍንጫዋን በአፍንጫዬ ነካሁት... ዐይኗን ጭፍፍን አድርጋ መሀል ከንፈሬ ላይ ሳም አደረገችኝ... እኔ ከከፍታዬ ወርጄ ለመንቃት ስታገል እሷ ቀና ብላ ምንም እንዳልተፈጠረ እሮሮዋን ቀጠለች...
ብዙ ቀን “ይኼ ነገር ሆኗል ወይስ ጭንቅላቴ ውስጥ ነው?” እያልኩ ተወዛግቤያለው...
እሷ እቴ...
ምን አለባት...
“የባለፈዋን ቸከስ ምን አረካት?” ትለኛለች ፈገግ ብላ...
ምን አደርጋታለው ሌላ?
ስለ ሌላ ሴት ስታወራ እናደዳለው...
ምን ይሉት ጥያቄ ነው? ምን አዲስ ነገር አደርጋለው...?
“የታባቷ... ክብር ካልወደደላት” እልና አኮርፋታለው... ልቤ “when hell freezes over...” ምናምን እያለ ይደክምብኛል...
“የምታፈቅራት ታፍቅርክ!” ይሉት ምርቃት የሞኝ ፀሎት እየመሰለ ያስቀኝ ነበር... ምርቃቱን እጁ ላይ ያቀለልኩበት መድሐኒዓለም ቁልቁል እያየ እምባው ጠብ እስኪል ይስቅብኛል...
አምርሬ እንዳልጠላው በዛች የአንገቴ ስር ተዓምር አጉል ጫፍ አስይዞኛል...
አይኔን ጨፍኜ ብቻዬን እሰማታለው...
“ ...I put a spell on you...
...’cause you’re mine... “
ትለኛለች ጆሮዬ ስር...
የአንገቴን ስር ቅፅበት እያሱን በሚያስንቅ እምነት በየቀኑ እለጥጣታለው... እኖራታለው... እወዳታለው...



Read 1694 times