Thursday, 11 February 2021 00:00

በአለማችን ከ104.7 ሚ. በላይ የኮሮና ክትባቶች ተሰጥተዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  አሜሪካ 33.7 ሚሊዮን ክትባቶችን ስትሰጥ፤ አልጀሪያ 30 ክትባቶችን ብቻ ሰጥታለች

          በአለም ዙሪያ በሚገኙ 66 አገራት እስካለፈው ረቡዕ ድረስ በድምሩ ከ104 ሚሊዮን በላይ የኮሮና ክትባቶች ለዜጎች መሰጠታቸውንና ብዛት ያላቸው ክትባቶችን በመስጠት አሜሪካ፣ ከህዝብ ብዛት አንጻር ከፍ ያለ የክትባት ሽፋን በማስመዝገብ ደግሞ እስራኤል ከአለማችን አገራት ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ 33.7 ሚሊዮን ያህል የኮሮና ክትባቶች መሰጠታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በቻይና 24 ሚሊዮን፣ በእንግሊዝ 10 ሚሊዮን፣ በእስራኤል 5.9 ሚሊዮን፣ በህንድ ደግሞ 4.14 ሚሊዮን ያህል ክትባቶች መሰጠታቸውንም ገልጧል፡፡
ከ100 ሰዎች 58 ያህሉ የኮሮና ክትባት ያገኙባት እስራኤል ከህዝብ ብዛት አንጻር ከፍተኛ መጠን ያለው ክትባት በመስጠት ከአለማችን አገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ 35፣ እንግሊዝ 15፣ ባህሬን 10 እንዲሁም አሜሪካ 9.8 በመቶ የሚሆነውን ነዋሪ ህዝብ በመከተብ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም የብሉምበርግ ዘገባ ያሳያል፡፡  
ባሳለፍነው ሳምንት በአለም ዙሪያ በየዕለቱ በአማካይ 4.25 ሚሊዮን ያህል የተለያዩ አይነት ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ የኮሮና ክትባቶች ለተጠቃሚዎች መሰጠታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ክትባት መስጠት ከጀመሩት 66 የአለማችን አገራት መካከል አልጀሪያ 30 ክትባቶችን ብቻ በመስጠት በመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም አመልክቷል፡፡
ያደጉ አገራት የኮሮና ክትባት ሽሚያቸውን አጠናክረው እንደገፉበት የጠቆመው ዘገባው፣ እስካለፈው ወር አጋማሽ ድረስ ከክትባት አምራቾች ጋር ግዢ ከፈጸሙት የአለማችን አገራት መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ያደጉ አገራት መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡
በሌላ የኮሮና ክትባት መረጃ ደግሞ የአለም ባንክ ለአፍሪካ አገራት የኮሮና ክትባት መግዣ የሚውል የ12 ቢሊዮን ዶላር በብድርና በድጋፍ መልክ ለመስጠት መወሰኑን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራትም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መነገሩን አመልክቷል፡፡
የታንዛኒያ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን አስገብቶ ለዜጎቹ የማዳረስ እቅድ እንደሌለው ማስታወቁን የዘገበው ቢቢሲ በበኩሉ፤ የአገሪቱ መሪም፣ ነጮች የሚያመርቱት የኮሮና ክትባት እጅግ አደገኛና ጎጂ በመሆኑ ክትባት እንዳትወስዱ ሲሉ ከሰሞኑ ማስጠንቀቃቸውን አስታውሷል፡፡


Read 5730 times