Saturday, 06 February 2021 12:27

የ‘ኖርማል’ ነገር

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

  “እንዴት ሰነበታችሁሳ!”
“ምን ልታዘዝ?”
“ሦስት ክትፎ ታመጭልናለሽ?”
“ኖርማል ነው ስፔሻል?”
እናላችሁ... ‘ኖርማል’ ሚጢጢ ሆና በሦስት አራት ጉርሻ ሙልጭ የምትል፣ ‘ስፔሻል’ በዛ ብላና በጎመናጎመን በመጠኑ ታጅባ ትመጣለች፡፡ (ሥጋው ከኖርማሉ ከተለየ ከብት ለመምጣቱ ‘መረጃ’ የለኝም። ቂ...ቂ...ቂ...)
ስሙኝማ... የክትፎ ቤቶች ነገር እንዴት ነው፡፡ አይ ማርኬትየው ‘ሞቅ’ እንዳለ ነው ወይ ለማለት ነው፡፡ ከክትፎ ቤቶች ከራቅን ስለከረምን ነው፡፡ (በሆዳችሁ ..አለ አይደል...“ገና ምን አይተህ ከሹሮ ቤትም ትርቃታለህ” የምትሉ ወዳጆች፤ የ‘ፌቨራየት’ ምግባችን የሹሮ ዋጋ ወደ ክትፎው እየተጠጋ መሆኑን ልብ እንድትሉ ለማለት ያህል ነው።) እኔ የምለው ...የድራፍት ዋጋ እንደገና ጨመረ እንዴ! ለዚህ ነው እንዴ ወዳጆቼ ሰላምታ ቀዘቀዘብን! አሀ... አህያውን ፈርቶ ዳውላውን አታድርጉታ! ካኮረፋችሁ ሂዱና ቢራ ፋብሪካ በራፍ ላይ አኩርፉ እንጂ እኛን የምን ማሙያ ማኩረፊያ ነው፡፡
 እንበልና ከሆነ ሰው ጋር ትጋጫላችሁ። ዘንድሮ እንደሁ የሚችል ትከሻ ይስጣችሁ እንጂ፣ ዘወር ባላችሁ ቁጥር የሚያጋጭ ነገር መአት ነው፡፡
“እኔማ እሱን በምንም አይነት ዝም ልለው አልችለም፡፡”
“አንተ ምን ያጋጭሀል፣ ለምን ሁሉንም ነገር አትተውም?”
“ሞቻለኋ!”
“አንተ ግን ይሄን ያህል ያበሳጨህ ምንድነው?”
“ሦስት ሺህ ብር ተበድሮ ነው እኮ የካደኝ!”
“እና ምን ይገርማል... አሁን እኮ ተበድሮ መካድ ኖርማል ሆኗል!”
እናላችሁ... ብዙ አጉል ነገሮች ‘ኖርማል’ ሆነዋል፡፡
ደግሞላችሁ...
“ስማ አያሳዝንም?”
“ምኑ ነው የሚያሳዝነው?”
“እንትናና እንትና እኮ ዓመት ሳይሞላቸው ተፋቱ!”
“ምኑ ይገርማል፣ ተጋብቶ ወዲያው መፋታት እንደሁ ኖርማል ሆኗል፡፡”
በሚገባ የማያስተናግዱ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ስነ ምግባር የጎደላቸው የደንበኞች አገልግሎት አቅራቢዎች ሠራተኞች፣ ለተሳፋሪዎች አክብሮት የሌላቸው የህዝብ ትራንስፖርት ሹፌሮችና ረዳቶች፣ ሙያቸውን በተገቢው መንገድ የማይወጡ ደንብ አስከባሪዎችና የጥበቃ ሠራተኞች። እነኚህ ሁሉ ኖርማል የሚባለውን ነገር ሊሆኑ ምንም አልቀራቸው።
ስሙኝማ... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ይቺ አዲስ አበባ ያልያዘችው ጉድ ያለ አይመስልም እኮ! በተለይ ስለ እኛ ነዋሪዎቿ ባህሪያትና ከመጋረጃ ጀርባ ያሉ የአኗኗር ሁኔታዎች የምንሰማቸው ነገሮች የሆሊዉድ ፊልሞችን ያስንቃሉ፡፡ ልክ ነዋ... የምን ‘ፋታል አትራክሽን’ የምን ‘ቦዲሂት!’ የምን ሻሮን ስቶን!
ስንት ጉድ እየሰማን አይደል እንዴ!
የምር በየቀኑ የምንሰማቸው ነገሮች መአት ‘ፌክ ኒውስ’ ቢኖርባቸውም የሚገራርሙ ደግሞ ቢጋነኑ እንኳን ፌክ ያልሆኑ የሚመስሉ ጉዶች መአት ናቸው፡፡
በቅጽል የተሞላ ማድነቅ፣ በቅጽል የተሞላ እርግማን ኖርማል ሆነዋል። ከተገቢው በላይ ጥቅም ላይ እየዋሉ ቃላት ከጊዜ ብዛት የሚመናመኑ ቢሆን ኖሮ፣ ቅጽሎቻችን ሁሉ ጉድ ይፈላባቸው ነበር። እናላችሁ... የሚደግፉትን ሰማይ ላይ አውጥቶ ከመላእክት ጎን ማስቀመጥ፣ የጠሉትን ከመሬት በታች አውርዶ ከዲያብሎስ ጋር አስተቃቅፎ ማስደነስ ‘ኖርማል’ ሆኗል፡፡ ሀሳብ አለን በአፍሪካም፣ በዓለምም አንደኛ የምንሆንባት አንድ ድንቅ (ቅጽል) የቅጽል ኮታ ይደልደልልን፣ በተለይ ለቦለቲከኞች። አንድ ግለሰብ ፖለቲከኛ በወር ከአምስት በላይ፣ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በወር ከሰባት በላይ የማድነቅም፣ የመርገምም ቅጽል መጠቀም አይችሉም፡፡ ይህንን የሚጥሱ ግለሶቦች ከእቁብ ጸሀፊነት ለበለጠ ህዝባዊ ስልጣን መወዳደር አይችሉም። ይህንን የሚጥሱ ድርጅቶች የፖለቲካ አካልነታቸው ተሰርዞ የጥሬ ሥጋ ማህበር መሆን ይችላሉ።” ቂ...ቂ...ቂ...
የምር ግን “ፍትህ ለቅጽሎቻችን” የሚል መመሪያ አንግበን የሆነ ውድድርማ ከእለታት አንድ ቀን ሳንገባ አንቀርም። እኔ የምለው… እንዲህ ስድደብ የበዛብን ለምንድነው?  ሁላችንም እኮ ተሳዳቢ ሆነን አረፍነው፡፡
ምድረ ፈረንጅ ደግሞ በሆነ ባልሆነው ይቺን ሀገር ማብጠልጠል አሁን፣ አሁን በየማህበራዊው ሚዲያ ‘ኖርማል’ እየሆነ ነው ማለት ብቻ ሳይሆን ድሮም ‘ኖርማል’ ነበር፡፡ አሁን ከሌላው ጊዜ በበለጠ ለነገሮች ትኩረት መስጠት ስለጀመርን የበዛ መስሎ ታይቶን ነው እንጂ በፊትም ነበር፣ ነገም ከነገ ወዲያም እነ ማርቲን ፕላውትና አጃቢዎቻቸው ይኖራሉ፡፡ 
‘ኖርማል’ የሆኑ የመግለጫና የቃለ መጠይቆች ቃላት አሉላችሁ... እንደውም ‘እርምጃ ይወሰዳል፣’ ‘አጠናክሮ ይቀጥላል’ ምናምን የሚሉ ሀረጎች ከ‘ኖርማልነት’ አልፈው ‘ክሊሼዎች’ እየሆኑ ነው፡፡ የምር እኮ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... አለ አይደል... ፈገግ አልልም ብትሉም እኮ በቀበሌም ባትገደዱም በነገርዬው ፈገግ ማለታችሁ አይቀርም፡፡ ገና ይችን ታክል ዓይን የምትገባ እንቅስቃሴ ሳትታይ… ምኑን ነው አጠናክሮ የሚቀጠለው፣ ምኑ ነው የሚቀጠለው፡፡ ቀሺም የህዝብ ግንኙነት ሥራ አይሆንም?
እናላችሁ... መሆን የማይገባው አሉታዊና አፍራሽ ነገር ሁሉ “በቃ ኖርማል ነው...” እየተባለ ስነምግባሩም ስነ ስርአቱም መላቸው እየጠፋ ነው፡፡ እናማ... መንገድ ላይ ስትሄዱ ሠላሳ ዘጠኝ ቁጥር እግራችሁ ላይ አርባ አራት ቁጥር ጫማ ቢቆምባችሁ...አለ አይደል... ወከባ መፍጠር፣ “አይተህ አትሄድም እንዴ! ዝም ብለህ ኩንታል ዘንጋዳ ይመስል ትከመርብኛለህ እንዴ!” ብሎ ስላለ ዋጋ የለውም፡፡ ‘ኖርማል’ ነዋ! አዎ መንገድ ላይ መረገጥ እጅግ ‘ኖርማል’ ከሆኑ የዕለት ዕለት ‘ኤክሲፒሪየንስ’ አንዱ ነው፡፡
ስሙኝማ... ሌላው ኖርማል ነገር ምን መሰላችሁ... ሁሉንም አዋቂ ነን የምንል ሰዎች መብዛታችን፡፡ የምር እኮ... አንዳንዴ የዓለም ‘ጂኒየስ’ ሁሉ እዚህ የተሰበሰቡ ነው የሚመስለው፡፡  
በአንዳንዶቻችን አካባቢ መንቀባረር ‘ኖርማል’ እየሆነ አይመስላችሁም፡፡
እኔ የምለው... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... እዚህ ሀገር ስም አወጣጥን የሚደነግግ ህግ ወጥቷል እንዴ! ግራ ገባና! ለልጁ የፈረንጅ ስም የሚሰጥ በዛብና! ነው ወይ ለአቅመ የአሜሪካ ቪዛ ሲደረስ ነገሩን ያቀለዋል ተብሎ ነው? “ለአሜሪካ ያለኝን ወዳጅነትማ ማሳያ ከፈለጋችሁ… ልጄን እኮ ስሙን ሮበርት ነው ያልኩት፡፡” ምን! አይገጥምማ፡፡
“ሮበርት!”
“የስ፣ ሮበርት፡፡”
“ሮበርት ሁ?”
“ሮበርት ድፋባቸው፡፡”
ቆይ ቆይማ፡፡ ወይ ሮበርትን ወዲህ ማምጣት፡፡ ወይ ድፋባቸውን ወደዛ መውሰድ፡፡ አለ አይደል... ለምሳሌ ሮበርት ድፋባቸውን ወደ ዴቪድሰን መለወጥ! የምር ግን... ድፋባቸው አሪፍ የራሱ ትርጉም ያለው ስም ነው፡፡ ሮበርት ፈረንጅ ‘ከማስመሰሉ’ በስተቀር ትርጉሙ ምንድነው? አሀ... በኋላ ቀበሌ አገልግሎት ለማግኘት ያስቸግራላ!
“ስም ማን ልበል?”
“ሮበርት ድፋባቸው፡፡”
“ይቅርታ፣ ማን አሉኝ?”
“ሮበርት ድፋባቸው፡፡”
የቀበሌው ሰውዬ ግራ ይገባዋል፡፡ ትንሽ አሰብ አደርጎ ምን ቢል ጥሩ ነው...
“የትውልደ ኢትዮጵያዊነት መታወቂያዎትን ሊያሳዩኝ ይችላሉ?” ቂ...ቂ...ቂ...
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1169 times