Saturday, 06 February 2021 11:39

እጅህን እውሃው ውስጥ ክተት፤ ከቀናህ አሣ ታገኛለህ ካጣህም እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን ፣ አንድ በተማሪዎች ሥራ ሙሉ በሙሉ የማይረካ መምህር ነበር።
መምህሩ ስለ ድራማ አሠራር (Drama craft) ጥበብ የሚያስተምር ነው!
አንደኛውን፡-
“እስቲ ዐይነ-ስውር ሆነህ ስራ!” ይለዋል።
ተማሪውም በእንቅስቃሴ ዐይነ-ስውር ሆኖ ይተውናል።
መምህሩም፣ “ትንሽ ይቀርሃል። ግን ጥሩ ሙከራ ነው!” ይለዋል።
ለሚቀጥለው ተማሪ፡-
“እስቲ ሆዱን የቆረጠው ሰው እንዴት እንደሚመስል አሳየን!”
መምህሩም፡-
“ትንሽ ይቀርሃል!”
እንዲህ እንዲህ እያለ የአንዲት ሴት ልጅ ተራ ደረሰና፣
“እስቲ አንካሳ ሴት በአንቺ ዕድሜ ያለች ምን እንደምትመስል አሳይ!” ተብላ ተጠየቀች።
ልጅቱም እንደ ሌሎቹ ተማሪዎች ሁሉ ክህሎቷን አሳየችና፤
“እንዴት ነው ጥሩ አልሰራሁትም?” ስትል ጠየቀች።
መምህሩም እንደተለመደው፡-
“ጥሩ ሰርተሻል። ግን ትንሽ ይቀርሻል።” አላት።
በዙሪያው ያለ ተመልካችም፤
“አይ አዋቂነት? አይ የጥበብ ሰው መሆን?” አለ።
ለካ ልጅቷ በተፈጥሮዋ አንካሳ ናት!
*   *   *
እናውቃለን ለምንለው ነገር ቅድሚያ በመስጠት፣
“I am quite what I am!” ማለት ከሁሉ ነገር በላይ ነው!
“እኔ እኔ ራሴ ነኝ” የማለት አካሄድን ካልለመድን፣ ረጅሙን መራራ ተግባር አንወጣውም። የዕውቀት ሁሉ ማሰሪያው ጥበብ፤ መለወጥን ማወቁ ላይ ነው። “Transcendence of Wisdom” እንዲሉ።
መማር ብቻውን ያለ ገቢር የአገር ሀብት አይሆንም! የዕውቀት ብርታቱ፣ ወደ ጥበብ መለወጡ ላይ ነው! በተግባራዊነቱ አገርን መለወጥ ይቻላልና። ለዚህ ሁሉ መጠቅለያው ትውልድ ለመለወጥ ዝግጁ መሆን ነው። ዕውነታው ግን የትውልዳችን ከድጡ ወደ ማጡ መጓዝ ነው! ፅድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ ማለታችን ነው!
የፖለቲካችን በሳልነትን ማጣት፤
የኢኮኖሚያችን  ውድቀት፤
የማህበራዊ ገፅታችን ምስቅልቅልነት፤
በጭራሽ የአገር ጤንነት ምልክት ሊሆን አይችልም!
“ሌላው ሁሉ ይቅር ሰው መሆን የገባው አንድ ወጣት እንፍጠር” የምንለው፣ የትውልዱ ቁልቁል ማደግ ስለሚያሳስበን ነው።
ወደ መልካም አስተዳደር ካላመራን፣ ጉዟችን የዕውር የድንብር ይሆናል! ማን መሪ፣ ማን ተመሪ መሆኑን ለመለየት፣ እስከማቃት ልንደርስም እንችላለን!
ዱሮ ጉዟችን ረጅም ትግላችን መራራ ይባልልን የነበረው፤ እንዲያው ለአንደበት ወግ አልነጠረም።
የዕለት ዕለቷን ኢትዮጵያ ብናያት፣ ቀሪውን ረዥም መንገድ ማሰብ አይሳነንም!
ወጣቱ ላይ የለብ ለብ ሳይሆን የልብ ሥራ መስራት ያሻናል!
ትምህርት ላይ አገም ጠቀም ሳይሆን ስር የሰደደና የበሰለ፣ ለብዛት ብቻ ሳይሆን ለጥራትም የቆመ፣ የስነ-ልቦናን እረቃ የሚያደርግ ቃና እንዲኖር በየጎራው መንቀሳቀስ ይቻላል! አስመራሪና አንገፍጋፊ ቢሆንም፣ “ላይችል ሰጥቶን የሚያስችለን” መሆን መቻል አለብን! ፈረንጆቹ  Small is beautiful  እንደሚሉት፤ ከትንሹ እንጀምር። ትንሽ በትንሽ እንደግ! ትንሽ በትንሽ እናሳድግ። መሳሳትን አንፍራ! በመሞከር እንማር!
“እጅህን እውሃው ውስጥ ክተት
ከቀናህ አሳ ታገኛለህ
ካጣህም እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ!” የሚባለው ለዚህ ነው።

Read 13333 times