Saturday, 30 January 2021 10:34

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተመራቂዎች ሁሉንም ዋንጫዎች ጠራርገው ወስደዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ዩኒቨርሲቲው 4859 ተማሪዎችን አስመርቋል

              ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ የትምህርት ፕሮግራሞች በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 4859 ተማሪዎች ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በዋናው ካምፓስና በቡሬ ካምፓስ፣ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያስመረቀ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲና በካምፓስ ደረጃ የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የተዘጋጁትን የዋንጫ ሽልማቶች በሙሉ የወሰዱት ሴት ተመራቂዎች ሆነዋል፡፡
ከአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ነጥብ ያመጣችውና በ4.00 ነጥብ የተመረቀችው በቡሬ ካምፓስ የእጽዋት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተማሪ የነበረችው ይቀደም አማረ ናት፡፡ ከወሰደቻቸው ኮርሶች ውስጥ በ42ቱ A+ ያስመዘገበችው ተመራቂዋ፤ በዩኒቨርሲቲና በካምፓስ ደረጃ የተዘጋጁትን ሁለት ዋንጫዎች አንዲሁም የቡሬ ካምፓስን የወርቅ ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ለመሸለም በቅታለች፡፡ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የዋናው ግቢ ተመራቂዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በካምፓስ ደረጃ የተዘጋጀውን የዋንጫ ሽልማት የወሰደችው ደግሞ 3.98 ያስመዘገበችው የፋርማሲ ምህርት ክፍል ተመራቂዋ ሃናን ፈድሉ ስትሆን፣ በኮሌጅ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት 1ኛ ደረጃን ለያዙ ተመራቂዎች ከተበረከቱት የሜዳሊያ ሽልማቶችም ሴቶች ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለ12ኛ ዙር ባከናወነው የምረቃ ስነስርዓት ላይ ከተመረቁት አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል 1873 ሴቶች ሲሆኑ፣ ዩኒቨርሰቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በመሬት አስተዳደር ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 30 ተማሪዎችም አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የኢፌድሪ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ፤ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያሳዩትን የአብሮነት የመረዳዳትና የመከባበር ባህል አንዲሁም አንድነት በቀጣይም ሊያጎለብቱት እንደሚገባ ጥሪያቸውን በማቅረብ የላቀ ውጤት ላመጡት ተመራቂዎች ሽልማት አበርክተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ በበኩላቸው፣ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ተመራቂዎች ወደየትውልድ ስፍራቸው ሲመለሱና ወደ ስራው አለም ሲገቡ፣ ለአገር ሰላም ግንባታ፣ ለህዝብ ለህዝብ ትስስር መጠናከርና ለኢኮኖሚ እድገት መፋጠን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ከ1999 ዓ.ም አንስቶ በድምሩ ከ37 ሺህ 860 በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የሙያ መስኮች በብቃት አሰልጥኖ ማስመረቁን ያስታወሱት ዶ/ር ታፈረ፤ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ጊዜ በሁለቱም ካምፓሶቹ 28 ሺህ 995 ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝም አክለው ገልጸዋል።

Read 1282 times