Wednesday, 27 January 2021 00:00

የአለማችን ስደተኞች ቁጥር 281 ሚሊዮን ደርሷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    በመላው አለም የሚገኙ አለማቀፍ ስደተኞች ቁጥር በአዲሱ የፈረንጆች አመት መጀመሪያ 281 ሚሊዮን መድረሱን ያስታወቀው ተመድ፣ ባለፈው አመት አገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ ተብለው የተገመቱት የአለማቀፍ ስደተኞች ቁጥር በ2 ሚሊዮን ያህል መቀነሱንም አክሎ ገልጧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ የስደተኞች ሪፖርት እንዳለው፣ ባለፈው አመት የስደተኞች ቁጥር ሊቀንስ የቻለው ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አገራት ድንበሮቻቸውን በመዝጋታቸውና የእንቅስቃሴ ገደቦችን በመጣላቸው ሳቢያ ሲሆን በአመቱ 219 አገራት ከ80 ሺህ በላይ የጉዞ ገደቦችን መጣላቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመላው አለም የሚገኙ አለማቀፍ ስደተኞች ቁጥር ከመላው የአለም ህዝብ 3.6 በመቶ ያህሉን እንደሚይዙ የጠቆመው የተመድ ሪፖርት፣ 70 በመቶ ያህሉ ስደተኞች በ20 አገራት ውስጥ እንደሚገኙ የገለጸ ሲሆን፣ 51 ሚሊዮን ስደተኞች የሚገኙባት አሜሪካ ከአለማችን አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ያሉባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗንም አክሎ ገልጧል፡፡
ጀርመን 16 ሚሊዮን፣ ሳዑዲ አረቢያ 13 ሚሊዮን፣ ሩስያ 12 ሚሊዮን፣ እንግሊዝ 9 ሚሊዮን አለማቀፍ ስደተኞችን በማስጠለል እንደሚከተሉም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
18 ሚሊዮን ሰዎች አገራቸውን ትተው የተሰደዱባት ህንድ በርካታ አለማቀፍ ስደተኞች የተሰደዱባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር እንደሆነች የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ሜክሲኮና ሩስያ አያንዳንዳቸው በተመሳሳይ 11 ሚሊዮን ሰዎች፣ ቻይና 10 ሚሊዮን ሰዎች፣ ሶርያ 8 ሚሊዮን ሰዎች አገራቸውን ጥለው እንደተሰደዱባቸውም አመልክቷል፡፡

Read 17144 times