Print this page
Monday, 25 January 2021 00:00

ያለ ኮሽታ የተጠናቀቀው የጎንደር ጥምቀት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ (ከጎንደር)
Rate this item
(0 votes)

በዘንድሮው ጥምቀት እስከ 6 ሺህ የሚደርሱ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ሊታደሙ እንደሚችሉየጎንደር ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ሐላፊ አቶ ቻላቸው ዳኛው የተነበዩ ቢሆንም ለጥምቀት የተገኘው ቱሪስት ግን ወደ 1 ሚሊዮን እንደሚጠጋ ነው መረጃዎች ያመለከቱት።
ከጥምቀት በፊት በነበረው የባህል ሳምንት ማለትም አጼ ቴዎድሮስ 202ኛ ዓመት የልደት በዓል፣ ግጥም በመሰንቆ፣ የተለያዩ የኪነ-ጥበባዊ የጎዳና ላይ ትርኢቶችና  “ለፋሲል እሮጣለሁ” የሩጫ መርሃ ግብርን ለመታደም ጭምር እንግዶች ቀደም ብለው ነበር ከተማውን ሞቅ ማድረግ የጀመሩት።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቃና ዘገሊላ በዓል እስከሚከበርበት ባለፈው ረቡዕ ጥር 12 ድረስ ጎንደር በሰው ተጨናንቃ ሰንብታለች። በከተማዋ አልጋ የሚባል ሁሉ በእንግዳ ተሞልቶ እንደነበር፣ ምግብ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ የባህል ምሽት ቤቶችና፣ ካፍቴሪያዎች በሙሉ በሰው ተሞልተው እንደነበር ተዘዋውረን ባደረግነው ቅኝት ተመልክተናል።
የከተራው እለት 44ቱ ታቦታት ወደ ባህረ ጥምቀቱ በሚሸኙበት ጊዜ በርካታ ህዝብ የታደመ ሲሆን የጸጥታ ችግር እንዳያጋጥም የአማራ ልዩ ሃይል፣ የከተማው ፖሊስና የጎንደር ወጣቶች በሚገርም ቅንጅት ሁኔታዎችን ሲከታተሉ፣ ዙሪያ ገባውን ሲቃኙ ነበር። በዚህም ያለምንም ችግር ታቦቱን ወደ ማደሪያቸው ሸኝተው ተመልሰዋል። ጥር 11 ቀን በዋናው የጥምቀት እለት የጥምቀተ ባህሩ ቦታ በብዙ ሺህ በሚቆጠር ሰው ተሞልቶ ነበር። ጠጠር ቢጣል መውደቂያ የማይኖርበት ጥቅጥቅ የሰው ደን ማለት ይቻላል።
በዚህ ቦታ ላይ ለመገኘት ከጫፍ ጀምሮ እስከ ውስጠኘው ክፍል ብዙ ዙር  ፍተሻዎችን ማለፍ የግድ ይላል። በማለዳው ታቦታቱ ወዳደሩበት ጥምቀተ ባህር ቀድሞ ከደረሰው ህዝበ ክርስቲያን በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልዑካን፣ የኤርትራ ልዑካን፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ በርካታ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ታዋቂ ድምፃውያንና ጋዜጠኞችም ታድመው ነበር።
እውቁ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ አዲስ አጥንትና ነፍስን የሚያለመልም ትምህርት አስተምረው ሲያበቁ በቦታው የነበሩት የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተጨንቆና ተጠቦ ይህን ደማቅ ዝግጅት በማዘጋጀቱ፣ የፀጥታ ክፍሉም ሆነ የከተማው ወጣት ጥምቀት የተሳካ እንዲሆን ላደረጉት ርብርብ እንዲሁም ከመላው ኢትዮጵያ መጥተው ላከበሩት ሁሉ ምስጋና ቀርቧል።
በእለቱ ለዋድባ ገዳም ሲታገሉና ህወሃትን ሲፋለሙ የነበሩት እንዲሁም “ዋልድባና የህዋሃት ፍጥጫ” የተሰኘ መፅሐፍ ያሳተሙት አባ ገ/ኢየሱስ ዘዋልድባ እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ወንጀል ሲሰራ ወይም ሲሰርቅ ለተገኘ ወዲያው ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜያዊ ፍ/ቤት በባህረ ጥምቀቱ አጠገብ እስከ ማዘጋጀት ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጎ የነበረ ሲሆን አንድ ወጣት የእንግዳ ተንቀሳቃሽ ስልክ ሲሰርቅ እጅ ከፍንጅ በመያዙ በዚያው ጊዜያዊ ችሎት የሁለት ዓመት እስራትና አስራ አምስት ሺህ ብር ቅጣት እንደተፈረደበት ሰምተናል።
“የኮሮና ነገር መረሳቱ ስጋት ፈጥሯል”
ከተማ አስተዳደሩ ወደ ጥምቀተ ባህሩ ለሚመጡ ሁሉ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ወደ ቪ አይ ፒ ለሚገቡ እንግዶች ደግሞ ከጭምብል በተጨማሪ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር በነጻ ያቀረበ ቢሆንም፤ ታዳሚው በአብዛኛው ጭምብል አላደረገም ነበር። ይህም የኮቪድ 19ን ስርጭት እንዳያባብስ አስተያየት ሰጪዎች ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ታቦታቱ ከተሸኘም በኋላ ከቴዎድሮስ አደባባይ ዝቅ ብሎ በሚገኘው ሜዳ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በሆታና በጭፍራ ባህሉን ሲያደምቅ የዋለ ሲሆን። በዚህም ላይ ጭምብል ያደረገ አለመኖሩ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል።
ሌላኛው ከተማ አስተዳደሩና የከተማዋ የሆቴል ማህበር ልብ ሊለው የሚገባው ጉዳይ የሆቴል አልጋ ዋጋ ማሻቀቡ ነው። አንዱና የመጀመሪያው ችግር አልጋ ለመያዝ የ3 ቀን ማለትም ከተራ፣ ጥምቀትና ለቃና ዘገሊላ እለት ካልሆነ በተናጠል አለመፈቀዱ ነው።
ሁለተኛው የቱሪስቶች ቅሬታ በአዘቦት ቀን 200 ብር እና 300 ብር ይከራዩት የነበሩት ተራ መኝታ ክፍሎች ሳይቀሩ ዋጋቸው እስከ 1500 ብር አድርገው ስለነበር ታዳሚውን ቅር አሰኝቷል።
ከዚህ በተቃራኒ ለጥምቀት ብለን ዋጋ አንጨምርም ብለው ነገር ግን ደግሞ ደረጃውን የጠበቀ አልጋ ኖሯቸው በቀደመው ዋጋ ተቀብለው እንግዳ ሲያስተናግዱ የሰነበቱ የሆቴል ባለቤቶችም ነበሩ።
እነዚህን ባለሃብቶች ከተማ አስተዳደሩ ማወደስ መሸለምና ለሌሎች አርአያ እንዲሆኑ እውቅና መስጠት እንደሚገባው ያነጋገርኳቸው የጥምቀት ታዳሚዎች ነግረውኛል።
በሃገር ውስጥ ቱሪስቶች መመካት እንደሚቻል ታይቷል
የመጀመሪያው ጉዳይ በትጋትና በመናበብ ከተሰራ የቱንም ያህል ችግር ቢመጣ በስኬት ማለፍ እንደሚቻል ነው ይላሉ። ከአዲስ አበባ ጎንደር ለጥምቀት በየዓመቱ እንደሚመጡ የነገሩኝ ወ/ሮ ጥላዬ አንተነህ የተባሉ ታዳሚ።
በሌላ በኩል ደግሞ እስከ ዛሬ በውጭ ቱሪስት ብቻ ላይ እምነትን የመጣል የተሳሳተ አመለካከትን ያስተካከለ ሁነት መታየቱን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ አደባባይ ገልጸዋል።
ዘንድሮ በጣት የሚቆጠሩ ፈረንጆች ብቻ ናቸው በጥምቀት በዓል ላይ የተገኙት። ነገር ግን የሃገር ውስጥ ታዳሚ አልጋውን ሞልቶ ከዘመድና ወዳጅ ጋር እስከ ማረፍ ድረስ ከተማውን ሞልቶት መሰንበቱ በሀገሪቱ ውስጥ ጎብኚው ላይ መመካትና ይህንን የሀገር ውስጥ ጉብኝት ማሳደግ እንደሚቻል ማሳያ ነው ተብሏል።
በኮቪድ 19 ምክንያት የተጎዳውን ጎናቸውን ጠግነው ስለመሰንበታቸው ለመግለጽ ጥናት ማጥናትን አያስፈልጋቸውም። የዘንድሮው የጎንደር ጥምቀት በብዙ መልኩ የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል።
የዓመት ሰው ይበለን!


Read 1888 times