Print this page
Saturday, 23 January 2021 11:32

‘ትህትናን’ የበላው ጅብ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)


                "‘ወንድሜ’ የተባለው ሰው ኮስተር ይልና ትንሽ አፈግፍጎ ከእግር እስከ ራሳችሁ ይገላምጣችኋል፡፡ አፍ አውጥቶ ባይናገርም ከአስተያየቱ “የት ያውቀኝና ነው ጤና ይስጥልኝ የሚለኝ!” እንደሚል ይገባችኋል፡፡ ኸረ ለእግዚአብሔር ሰላምታ መተዋወቅ አያስፈልገውም!"
                   
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በዓሉ በአብዛኛው በአሪፍ አለፈ አይደል። በእርግጥም ደስ ይላል፡፡ ስንትና ስንት ችግር በተደራረበበት ጊዜ፣ በየቀኑ “የሰላም እንቅልፍ የሚል ነገር ሲያምራችሁ ይቅር...” የሚል እርግማን ያለብን ይመስል አንዱን ችግር አለፍነው ስንል ሌላው እየተፈለፈለ ባለበት ሰዋችን እንዲህ ተንፈስ የሚልበት ጊዜ ማግኘቱ ተመስገን ነው...ህይወት ይቀጥላልና፡፡ በእርግጥም ደስ የሚል ነው፡፡
በተጨማሪም በዚህ ዘመን በውስጥም በውጭም የሚበተኑብን፣ የሚደነቀሩብን አደናቃፊ ነገሮች ሳይገድበን “የእናንተ በዓል የእኛም በዓል ነው፣” አይነት እምነት ያልገደባቸው ትብብሮች ማየት ደስ አይልም! ተመስገን ነው፡፡ (ኸረ እኔ በጭራሽ ‘ጭቅጭቅ’ ፈልጌ አይደለም!) እናማ... አለ አይደል... አንድዬ ነገንም ከነገ ወዲያንም ችግሮቻችንን ከቅርንጫፎቻቸው ሳይሆን ከስር ከስራቸው እየመነገለልን፣ እንዲህ ካኮረፈው ሰው ይልቅ ፈካ ያለው በብዙ እጥፍ የሚበዛበት ያድርግልን፡፡ 
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ‘ትህትና’ እና ‘ይሉኝታ’ የሚባሉ የእኛው የራሳችን የነበሩ እሴቶች የገቡበት ስላልታወቀ፣ ዓለም አቀፍ የ‘አፋልጉን’ ማስታወቂያ እናውጣ እንዴ?! አሀ..ልክ ነዋ...ነው ወይስ  ትህትናና ይሉኝታ ወደ ውጪ ሽው ሲደረግ ከነበረው ፈራንካ ጋር አብረው ሽው አሉ ይሆን?!
“ጤና ይስጥልኝ፡፡”
“ጤና ይስጥልኝ፡፡”
“ይቅርታ... ሹሮ ሜዳ የሚያስኬደው በየት በኩል ነው?”
“ቀጥ ብለህ ወደ ላይ ትወጣና መገንጠያው ላይ ስትደርስ ወደ ግራ ታጥፈህ...” እየተባለ ሜትር በሜትር የሚመስል መልስ ይሰጣል። ከዚህ ሄድ ሲልም... “እንደውም መንገዴ በዛ አቅጣጫ ስለሆነ እሸኝሀለሁ...” ይባል ሁሉ ነበር፡፡ ያውም አይተውት ለማያውቁት እንግዳ ሰው ነው፡፡ ለመረዳዳት መተዋወቅና ያለመተዋወቅ ጉዳይ ሳይሆን ሰው መሆን ብቻ በቂ የሆነበት ዘመን ነበርና! ምን ይደረግ... አለ አይደል... የመሸበትን የማይታወቅ እንግዳ ሰውን የሞቀ አልጋውን ለቆ፣  መንገድ ያጎሳቆለውን እግሩን ሙልጭ አድርጎ አጥቦ፣ ትኩስ ትኩሱን መግቦ አሳድሮ በማግስቱ “በሰላም ያሰብክበት ያድርስህ፣” ብሎ መልካሙን ሁሉ ተመኝቶ የሚሸኝ  ህብረተሰብ ነበር እኮ ሲባል የማይሞቀው፣ የማይበርደውና ጭርሱን የአሊባባ ተረት የሚመስለው ቦተሊከኛና የ“ደርምሰህ ግባ፣” አክቲቪስት የበዛበት ጊዜ ሆነ እንጂ!
እናላችሁ... ከሰብአዊነት ውጪ ምንም አይነት የፖለቲካ፣ የእምነት፣ የጎጥና መሰል ትስስሮሽ የሌለበት ትህትና፣ በጎ ፈቃደኝነት፣ ትብብርና ‘አንተ ትብስ፣ አንቺ’ አይነት መከባበር፣ መለያው የሆነ ህብረተሰብ የነበረባትና አሁንም የዘረኝነትና በትንሽ ትልቁ የመከፋፈል ጋኔን ባልሰፈረባቸው የሀገራችን ህብረተሰቦች ውስጥ በስፋት ያለ ነው፡፡  
“እህት ስንት ሰዓት ነው?”
“እ...ለአምስት ሰዓት አምስት ጉዳይ፡፡”
“አመሰግናለሁ፡፡”
“ምንም አይደለም፡፡”
እንዲህ የሚባልበት ዘመን ነበር፡፡ ለትንሹም ለትልቁም የትብብር ጥያቄ ሆነ የሴራ ትርክት የማይደረደርበት፡፡ ትህትና ሞልቶ የተተረፈረፈበት ጊዜ፡፡ እና... አሁን ምን ነካን? 
እናላችሁ... የዘመን መለዋወጥ አይገርም ይሆናል፡፡ ሆኖም ትህትናን የመሳሰሉ ለዘመናት አስተሳስረውን የኖሩ እሴቶች ጠፍተው ነገሩ ሁሉ የጉልበተኛና ይሉኝታ አጠገቡ ያልደረሰ እንደፈለገው የሚያደርግበት ሲሆን ያሳዝናል፡፡  
እናላችሁ... ዘንድሮ በእለቱ የሚታዩ ፊልሞች ማስታወቂያዎች አጠገብ ቆሞ “ሲኒማ ኢትዮጵያ የት ነው?" የሚል በበዛበት፣ የትብብር ጥያቄ ፈተና ሆኖላችኋል፡፡
ስሙኝማ... የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ... ይቺን ነገር ‘ምስጢሯን የገለጣችሁልኝ’ በራሳችሁ ቋንቋ ‘ይመቻችሁማ!’ ምን ይሆናል መሰላችሁ... ብዙ ጊዜ ሰዎቹ በእድሜ ገፋ ያሉ ናቸው፡፡
“የእኔ ልጅ፣ እባክህ የኮልፌ መንገድ በየት በኩል ነው?”
“ኮልፌ!” ለምን አይገርማችሁ! መገናኛ መሀል ላይ ሆነው እኮ ነው የሚጠይቋችሁ፡፡ ከመገናኛ ኮልፌ በዚህ እድሜያቸው!
“መገናኛ ነው ያሉኝ አባት?”
“አዎ ልጄ፣ ይኸውልህ የማላውቀው ሰፈር መጥቼ ጉድ ሆንኩልህ፡፡”
“እና፣ በእግርዎ ነው የሚሄዱት?”
“ታዲያስ ልጄ፣ የአውቶብሱንማ ከየት አባቴ አመጣዋለሁ ብለህ ነው!”
ሠላሳ አርባ ብሯን ትመዛላችሁ፡፡ “እንኩ አባት፣ በአውቶብስ ወይ በታክሲ ይሂዱበት።” ያው ምርቃት እየደረደሩላችሁ ጉዟቸውን ይጀምራሉ፡፡ ኮልፌ የሚሄደው ስንት ቁጥር አውቶበስ እንደሆነ፣ የኮልፌ ታክሲ የት እንደሚያገኙ አይነት ጥያቄ ብሎ ነገር የለም፡፡ ልብ በሉልኝማ፣ ሰውየው ‘የማያውቁት ሰፈር’ ነው የመጡት፡፡ ደግሞ ፈንጠር ይሉላችሁና ወጥመዱን ሌላኛው ላይ ይወረውራሉ፡፡
“የእኔ ልጅ፣ እባክሽ የኮልፌ መንገድ በየት በኩል ነው?”
ግራ ገባን እኮ... ጩጬውም ጮሌ፣ ጎረምሳውም ጮሌ፣  ጎልማሳውም ጮሌ‹ የዕድሜ ባለጸጋውም ጮሌ!
እናላችሁ...ትህትና ጀርባዋን ባዞረችብን በዚህ ዘመን ትብብር መጠየቅ ሁልጊዜም በጎ ምላሽ ላያስገኝ ይችላል፡፡
“ጤና ይስጥልኝ፣ ወንድሜ፡፡”
‘ወንድሜ’ የተባለው ሰው ኮስተር ይልና ትንሽ አፈግፍጎ ከእግር እስከ ራሳችሁ ይገላምጣችኋል፡፡ አፍ አውጥቶ ባይናገርም ከአስተያየቱ “የት ያውቀኝና ነው ጤና ይስጥልኝ የሚለኝ!” እንደሚል ይገባችኋል። ኸረ ለእግዚአብሔር ሰላምታ መተዋወቅ አያስፈልገውም! አሀ... ይህ ህዝብ እኮ አወቀ አላወቀ ከጎኑ የሚያልፈውን ሰው ለጥ ብሎ እጅ ነስቶ መልካም ጤንነት የሚመኝ ነበር፡፡
እናላችሁ... ዘንድሮ ነገርዬው ሁሉ እንዳይሆን፣ እንዳይሆን እየሆነ ገና ጉዳያችሁን ሳትገልጡ ሰላምታ በማቅረባችሁ ብቻ የጥርጣሬ መዝገብ ውስጥ ትጻፋላችሁ። ‘ይሄን ደግሞ ማነው የላከብኝ! እነኚህ ሰዎች ምን አድርግ ነው የሚሉኝ!’ (ሚስቱ “የወር ወጪውን በመጠጥ መጨረስህን ካልተወክ በስተቀር ሻንጣዬን ይዤ ጥርግ ነው የምልልህ!” ከማለቷ ውጪ ማንም ምንም አድርግ ብሎት አያውቅም፡፡) መልስ ባይሰጣችሁም እንደመለሰላችሁ ቆጥራችሁት ትቀጥላላችሁ...
“ሹሮ ሜዳ የሚያስኬደው በየት በኩል ነው?”
ይቺ ናት ጨዋታ! ጭራሽ ሹሮ ሜዳ! ቀጥሎ እኮ ለአገሩ እንግዳ ስለሆንኩ ትንሽ መንገድ ሸኘኝ ብሎ እኮ ማጅር ግዴን ሊያሯሩጥልኝ ነው!
እናላችሁ... የዘንድሮ ‘ቦተሊካው፣’ ‘ቡትለካው፣’ ‘ቡትልክናው’ ብዙ ነገሮችን ገለባብጦብናል ለማለት ያህል ነው፡፡ የሚገርም እኮ ነው.. በትንሽ በትልቁ በሌለ ግንብ ካባ ለካብ ካልተያየን እያልን የት ልንደርስ ነው!
“ይቅርታ፣ እህት ስንት ሰዓት ነው?”
በቃ በአንጀሊና ጆሊይኛ ትገለምጣችኋለች። በግልምጫው ውስጥ ግን በሆዷ እያለች የነበረችው ፏ ብሎ ይታያችኋል፡፡ ልክ ልካችሁን እየነገረቻችሁ ነው እኮ!
“ምን አይነቱ የነፈሰበት ፋራ ነው! በእሱ ቤት እኮ መልከፉ ነው፡፡ ትንሽ ብስቅለት እኮ ድቡልቡል ማስቲካ በጊፍት ወረቀት ጠቅልሎ ሊያመጣልኝ ነው፡፡”
 “ሰዓቴን ላይ ስሞክር ብራስሌቴን ሞጭልፎ ሊሮጥ እኮ ነው!”
ከዚችኛዋማ ይሰውራችሁ!
እኔ የምለው...‘ትህትናን’ የበላው ጅብ ‘ሎካል’ ነው ‘ፎሪን?’ ቂ...ቂ...ቂ...
ደህና ሰንብቱልኝማ!   

Read 406 times