Print this page
Saturday, 23 January 2021 11:29

"የግዮን ቀን" ከተከበረ አይቀር ---

Written by  አንሙት አብርሃም
Rate this item
(1 Vote)

   "የግዮን ቀን; ተብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሶስተኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡  ግዮን [ አባይ] ታሪካችን ነው። የአለማቀፍ ግንኙነት ታሪካችን ከአባይ የተነጠለ አይደለም። እረኛ የሚያዜምለት፣ ገጣሚ የሚገጥምለት፣ ሎሬት የሚጠበብበት፣ ምሁራን የሚመራመሩበት የተለያዩ አገራት ሕዝብ አስተሳሳሪ አዛማጅ መረብ ነው።
አባይ ባይኖር ኢትዮጵያዊነት ይጎድላል። የአባይ ተፈጥሮ ማስተሳሰር ነው። ቀለም ፣ ብሔር፣ ኃይማኖት፣ ዳር ድንበር ሳይገድበው አስተሳስሮናል። በ12ቱ ግዙፍ ገባር ወንዞች ያስተሳሰረን በረከት ነው።
አባይ ባህል ነው ፣ እምነትና እሴት ነው፣ ኢኮኖሚ ነው፣ ኪነጥበብና ስነፅሑፍ ነው። አባይ ፖለቲካ ብቻ አይደለም፤ ማንነት ነው! መጠሪያችን ስማችን ነው! አባይ ቁጭታችን ነው።
አስተሳሳሪ ነውና ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለግብፆችም አባይ ስጋና ደማቸው መሆኑን ድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ ) እንዲህ ገልፃዋለች።
ብነካህ ተነኩ አንቀጠቀጣቸው
መሆንህን ሳላውቅ ስጋና ደማቸው
የሚበሉት ውሃ የሚጠጡት ውሃ
ዓባይ ለጋሲ ነው በዚያ በበርሃ
አንተ ወራጅ ውሃ ቢጠሩህ አትሰማ
ምን አስቀምጠሀል ከግብፆች ከተማ ።
ብላዋለች።
እርግጥ ነው ሁለመናችንን፡ ደምና ስጋችንን፡ ታሪካችንን፡ አንድ ቀን ሰይመንለት ብቻ ሳይሆን ሁሌም የምናስበው፡ ሁሌም የምንሠራበት መሆን ያለበት ነው። "የግዮን ቀን" ተብሎ ከተሰየመ አይቀር ግን የምር በጥልቀት የምንነጋገርበት መሆን አለበት። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተፈጠረ አጀንዳ ላይ ከማውጋት ወጥተው ወደ አጀንዳ ፈጣሪነት ቢገቡ መነጋገሪያ ጉዳያችን ብዙ ነው። ነፃ ሆኖ አገራዊ ጉዳይን እስከ ምናምኑ መመርመር ይመስለኛል የአካዳሚክ ነፃነት ፍላጎት። አባይም እንዲሁ በፈርጅ በፈርጁ ሊመከርበት ይገባል። ኢኮኖሚስቶች ስለ ኢኮኖሚ እድሉ፣ ዲፕሎማቶችና ፖለቲከኞች ስለ ጂኦፖለቲካዊ ፋይዳውና ቁመናችን፣ የታሪክ አዋቂዎች የአባይን የታሪክ አንድምታ፣ ፀሐፊያንና ከያንያን አባይና ጥበብን፣ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች የነገውን አባይ ህልውና፣ የማህበረሰብ አጥኝዎች አባይን ከባህል ትውፊትና ማንነት አንፃር ...ወዘተ መምከር አለብን።

Read 303 times