Saturday, 23 January 2021 11:06

ኢትዮጵያ በወታደራዊ አቅም ጥንካሬ ከአፍሪካ በ6ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች

Written by 
Rate this item
(7 votes)

    የአገራትን አጠቃላይ ወታደራዊ አቅም በመገምገም በየአመቱ ደረጃ የሚሰጠው ግሎባል ፋየር ፓወር የተሰኘው አለማቀፍ ተቋም ከሰሞኑም የአዲሱ የፈረንጆች አመት ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ አሜሪካ በአመቱ እጅግ ከፍተኛው ወታደራዊ አቅም ያላት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር መሆኗን አስታውቋል፡፡
በግሎባል ፋየር ፓወር የአመቱ ወታደራዊ አቅም ሪፖርት ውስጥ ከተካተቱት የአፍሪካ አገራት መካከል ግብጽ፣ አልጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያና ሞሮኮ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃን ሲይዙ፤ ኢትዮጵያ በ6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ከ138 የዓለም አገራትም በ60ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች - ኢትዮጵያ፡፡  
ግብጽ ከዓለም አገራት  በ13ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፣ ሱዳን በ77ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብሏል - ተቋሙ፡፡
ተቋሙ ወታደራዊ የሰው ሃይል፣ የገንዘብ አቅምና የጦር መሳሪያ ሃብትን ጨምሮ ከ50 በላይ በሚሆኑ መስፈርቶች በአለም ዙሪያ የሚገኙ 138 አገራትን ገምግሞ ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርቱ፤ ከአለማችን አገራት በወታደራዊ አቅም የሁለተኛነት ደረጃን የያዘችው ሩስያ ስትሆን፣ ቻይና፣ ህንድና ጃፓን እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ደረጃውን ያወጣው ግሎባል ፋየር ፓወር፤ የየአገራቱን ወታደራዊ የሰው ኃይል፣ ከታጠቁት መሳሪያዎች ጋር በማቅረብ አነጻጽሮ ነው የአገራቱን የወታደራዊ አቅም ደረጃን ያወጣው፡፡ በዚህ መሠረት፤ ከአፍሪካ በ6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ 162 ሺህ ወታደሮች፣ 24 ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ 8 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ 365 ታንኮች፣ 130 ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ 480 ከባድ መድፎች፣ 180 የሮኬት መተኮሻዎች እንዲሁም 65 ቀላል መድፎች ሲኖራት፣ የአገሪቱ ዓመታዊ ወታደራዊ በጀት ደግሞ 520 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን  ግሎባል ፋየር ፓወር አመልክቷል፡፡
ከአፍሪካ በወታደራዊ አቅም የምትመራው ግብጽ፣ ከ104 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሲሆን  930 ሺህ ወታደሮች፣ 250 ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ 91 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ 3735 ታንኮች፣ 2200 ከባድ መድፎች፣ 11ሺህ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች  ሲኖራት፣ የመከላከያ በጀቷ 10 ቢሊዮን ዶላር  እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡  
ከ138 አገራት በ77ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ሱዳን፣ ከ45 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሲኖራት፣ አጠቃላይ ያላት የወታደር ብዛት 190 ሺህ ነው። ሱዳን 45 ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ 43 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ 830 ታንኮች፣ 450 ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ያላት ሲሆን የአገሪቱ ዓመታዊ የመከላከያ በጀት 4 ቢሊየን ዶላር ነው።
በአፍሪካ አህጉር ግብጽ በወታደራዊ ኃይል የመጀመሪያውን ደረጃ ስትይዝ፣ ኢትዮጵያ 6ኛ፣ ሱዳን ደግሞ 10ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት መካከል ኬንያ ከአፍሪካ 12ኛ፣ ደቡብ ሱዳን 22ኛ፣ ሶማሊያ ደግሞ 34ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
በወታደራዊ አቅም ቀዳሚዎቹ 20 የዓለም አገራት
አሜሪካ
ሩሲያ
ቻይና
ህንድ
ጃፓን
ደቡብ ኮርያ
ፈረንሳይ
ዩናይትድ ኪንግደም
ብራዚል
ፓኪስታን
ቱርክ
ጣልያን
ግብጽ
ኢራን
ጀርመን
ኢንዶኔዥያ
ሳኡዲ አረቢያ
ስፔን
አውስትራሊያ
እስራኤል

Read 13378 times