Saturday, 23 January 2021 11:00

“በትግራይ አፋጣኝ ድጋፍ ካልተደረገ ሰብአዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል” - ኢሠመኮ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)


                         አስፈላጊው እርዳታ በተገቢው ሁኔታ  እየቀረበ ነው”  - መንግስት
                          
            በትግራይ ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያለው የምግብ እጥረት ወደ ሰብአዊ ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያሳሰበ ሲሆን የክልሉና የፌደራል መንግስት በበኩላቸው፤ አስቸኳይ የምግብና ሌሎች እርዳታዎች በተገቢው ሁኔታ እየተዳረሰ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በሁለት ዙር ማለትም ከታህሳስ 6 እስከ 11 በጎንደርና በዳንሻ ከተሞች እንዲሁም ከታህሳስ 22 እስከ 27 ደግሞ በትግራይ ክልል ጨርጨር፣ ኡልጋ፣ ቢሶበር ወረዳዎች ባለሙያዎችን በመላክ በሰብአዊ እርዳታዎችና በሲቪል ዜጎች ላይ ምርመራና ክትትል አድርጓል።
ምርመራና ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች በጦርነቱ ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን፣ አካላዊ ጉዳትም መድረሱንና በርካቶች መፈናቀላቸውንም ኮሚሽኑ  አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ወደ አካባቢዎቹ በተጓዙበት ወቅት እንደተመለከቱት፤ በተለይ በዳንሻ፣ ቢሶበር፣ ኡልጋ እና ሁመራ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ አፋጣኝ እርዳታ ካልተደረገ ወደ ሰብአዊ ቀውስ ሊያመራ ይችላል ተብሏል።
በአካባቢዎቹ የውሃ መብራትና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንደሌሉ  ያስታወቀው ኮሚሽኑ፤ ከሁመራና ዳንሻ ለተፈናቀሉና አማራ ክልል ለሚገኙ ከ73 ሺህ በላይ ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋል ብሏል።
በቢሶበርና በኡልጋ አካባቢዎች ብቻ 31 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የኮሚሽኑ ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በበኩሉ፣ የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ በቃኘበት ሪፖርቱ፤ አሁንም በገጠራማ የትግራይ አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውንና ሰላማዊ ዜጎች ከለላ ፍለጋ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ መሆኑን አስታውቋል።
ወደ የተለያዩ የትግራይ አካባቢዎችም የእንቅስቃሴ ገደቦች በመኖራቸው ስለ ሁኔታው የተሟላ ግንዛቤ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን የጠቆመው  ሪፖርቱ፤ ህዝቡ ከሁለት ወራት ለበለጠ ጊዜ ያለ ምግብና ውሃ፣እንዲሁም የጤና አገልግሎት መቆየቱ የሰብአዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አስገንዝቧል። በትግራይ የረሃብ አደጋም አንዣብቧል ብሏል ጽ/ቤቱ።
መንግስት በበኩሉ፤ እርዳታ በተገቢው እያቀረበ መሆኑንና ተጎጂዎችን ለመድረስ በሙሉ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል። በተለያዩ አካላት ረሃብ አንዣብቧል እየተባለ የሚነገረው የተጋነነ ነው ያለው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፤ ተገቢው እርዳታ እየቀረበ ነው ብሏል።
የሰላም ሚኒስቴር በበኩሉ፤ በክልሉ 2.5 ሚሊዮን ዜጎችን የእርዳታው ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉንና እስካሁንም 1.8 ሚሊዮን ለሚሆኑት እርዳታው መዳረሱን አስታውቋል።

Read 12079 times