Saturday, 23 January 2021 11:04

ምርጫ ቦርድ 192 የምርጫ መወዳደሪያ አማራጭ ምልክቶችን አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ምርጫ መወዳደሪያ አማራጭ ምልክቶች ይፋ አደረገ፡፡
ቦርዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች 92 ምልክቶች፣ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለሚወዳደሩ የግል እጩዎች 50 እንዲሁም ለክልል ም/ቤት ለሚወዳደሩ የግል እጩዎች 50 በጠቅላላው 192 የተለያዩ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቶችን አቅርቧል፡፡
ለፖለቲካ ፓርቲዎች በአማራጭ ከቀረቡ ምልክቶች መካከል የሳተላይት ዲሽ፣ የግድግዳ ሰዓት፣ ጡጦ፣ የጀርባ ቦርሳ፣ ሙዝ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ንብ፣ ደውል፣ ቀበቶ፣ ብስክሌት፣ መፅሐፍ፣ የምታጠባ እናት ምስል፣ መጥረጊያ፣ ብሩሽ፣ ባልዲ፣ አውቶቡስ፣ ቢራቢሮ፣ ኬክ፣ የፎቶ ካሜራ፣ ኮፍያ፣ መኪና፣ ድመት፣ ፒንሳ፣ ውሻ፣ አህያ፣ አሳ፣ ዝሆን፣ ኳስ፣ መነፅር፣ የሞባይል ቀፎ፣ ልብ፣ ጊታር ምስሎች ይገኙበታል፡፡
ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለሚወዳደሩ እጩዎች ከቀረቡ አማራጭ ምልክቶች መካከል ደግሞ በርገር፣ ኮፊያ፣ ሄሊኮፕተር፣ ማንቆርቆሪያ፣ መሰላል፣ ማይክራፎን፣ ኩባያ፣ ክራር፣ ቃሪያ፣ አውሮፕላን፣ ጥንቸል፣ ምላጭ ፣ ዶሮ፣ መርፌ ቁልፍ፣ መጋዝ ፣ መቀስ ይገኙበታል፡፡
ለክልል ምክር ቤት ለሚወዳደሩ የግል እጩ ተወዳዳሪዎች ከተዘጋጁ ምልክቶች መካከልም ፈረስ፣ ጫማ፣ አካፋ፣ ማጭድ፣ የጠረጴዛ መብራት፣ ቧንቧ፣ የውሻ ምስል፣ አሻንጉሊት፣ ቴሌቪዥን፣ ጥላ፣ የሜዳ አህያ፣ በሬ ይጠቀሳሉ፡፡
ቦርዱ ካዘጋጃቸው ምልክቶች ውስጥ የሚወክለኝ የለም የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ የግል ተወዳዳሪዎች የየራሳቸውን ምልክት ይዘው የመቅረብ መብት እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታቸውን ከጥር 13 እስከ ጥር 24 ቀን 2013 ለቦርዱ እንዲያሳውቁ የጊዜ ገደብ  ተሰጥቷቸዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ከዚህ ቀደም የቦርዱን መስፈርት እንዲያሟሉ ተጨማሪ እድል ከተሰጣቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያማ ፓርቲ፣ ሃረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅትና የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተጠየቁትን አሟልተው በመገኘታቸው እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በተጨማሪም ህዳሴ ፓርቲና  የከፋ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት፣ የሲዳማ አንድነት ፓርቲ  ፣የራያ ራዩማ ለዶሞክራሲያዊ ፓርቲ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው፤ በቀጣዩ 6ኛ ሃገር አቀፍ ምርጫ እንዲሳተፉ ተቀባይነት ያገኙ 52 የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ መሆናቸውንና ከዚህ በኋላ የሚጨመር አለመኖሩን አስታውቋል።


Read 12003 times