Saturday, 23 January 2021 10:59

በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ ፓርቲዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    • ህወሓት ከፓርቲዎች ዝርዝር ተሰርዟል

             ህገ-ወጥ ነው በተባለው የትግራይ ክልል ምርጫና የአመፃ ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ ሶስት የክልሉ ፓርቲዎች ስለ እንቅስቃሴያቸውና ስለቀረበባቸው አቤቱታ ምላሽ እንዲሰጡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠይቋል።
ከእነዚህ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዲፓ) በምርጫ ቦርድ ገና በምዝገባ ሂደት ላይ እያለ  በትግራይ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በተካሄደው ህገ-ወጥ ምርጫ መሳተፉ ተመልክቷል።
ብሄራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) እንዲሁ  በምርጫ ቦርድ ገና በምዝገባ ሂደት ላይ እያለ በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምርጫ ስለመሳተፉ እንዲሁም የፓርቲው አመራሮች በአመፃ ተግባር ላይ ተሳትፎ እንደነበራቸው  ለቦርዱ መረጃ መድረሱን፤ በተመሳሳይ ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ (ሳወት)ም ተመሳሳይ ድርጊት ውስጥ መሳተፉና አመራሮቹም በአመፃ ድርጊት ስለመሳተፋቸው ቦርዱ አመልክቶ፣ በጉዳዩ ላይ አፋጣኝ ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ጠይቋል።
በሌላ በኩል፤ ምርጫ ቦርድ ህወሓትን ሙሉ ለሙሉ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር ሰርዟል፡፡  ለ30 ዓመታት ያህል በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ዋነኛው ሃይል ሆኖ የዘለቀው ህወሐት፣ባለፈው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ፣ሃይልን መሰረት ባደረገ የአመፅ ተግባር ላይ ተሳትፏል በሚል ነው ህጋዊ ሰውነቱን አጥቶ የተሰረዘው፡፡
ቦርዱ  በአመጻ ድርጊት የተሳተፈውን ህወሓትን ከመሰረዙ በፊት የአዲስ አበባ የህወሓት ተወካይ ፓርቲውን በተመለከተ ለማነጋገር መሞከሩንና ከእንግዲህ ፓርቲውን እንደማይወክሉ በመግለፃቸው እንዲሰረዝ መወሰኑን አስገንዝቧል።
የተሰረዘውን የህወኃትን ሃብት ንብረት በተመለከተ በዝርዝር ተጣርቶ ንብረቱ በእዳ ከተያዘ ተሸጦ እዳው እንዲከፈል፣ የተረፈ ገንዘብ ካለም፣ ለምርጫ ቦርድ ለስነ-ዜጋና ለመራጮች ትምህርት ማስፈጸሚያ እንዲውል ወስኗል።


Read 820 times