Wednesday, 20 January 2021 00:00

አለማችን በኢንተርኔት አገልግሎት መዘጋት 4 ቢሊዮን ዶላር አጥታለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በአመቱ በመላው አለም 1.24 ቢሊዮን ሞባይል ስልኮች ተሸጠዋል

            አለማችን በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2020 በኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥና መዘጋት ምክንያት በድምሩ 4 ሚሊዮን ዶላር ያህል ማጣቷን ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ የሆነው ቶፕ10ቪፒኤን የተባለ የጥናት ተቋም አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ ሪፖርት እንዳለው፣ በአመቱ በተደጋጋሚ ኢንተርኔትን በመዝጋት ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን የያዘችው ህንድ ስትሆን፣ አገሪቱ ላለፉት 12 ወራት ከ75 ጊዜያት በላይ ኢንተርኔትን በመዝጋቷ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ አጥታለች፡፡
በ2020 አለማችን በኢንተርኔት መዘጋት ሳቢያ ያጣችው ገንዘብ ካለፈው 2019 አመት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያህል ቅናሽ ማሳየቱን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ በአመቱ በመላው አለም በድምሩ ለ27 ሺህ 165 ሰዓታት ያህል ኢንተርኔት መቋረጡንና በዚህም 268 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ተጎጂ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ዜና ደግሞ፣ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2020 በመላው አለም 1.24 ቢሊዮን ያህል የሞባይል ስልኮች ለሽያጭ መብቃታቸውን ዲጂታይምስ የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት ያስታወቀ ሲሆን፣ አለማቀፉ የሞባይል ስልኮች ሽያጭ በ2019 ከነበረበት የ8.8 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ጠቁሟል፡፡
በአመቱ ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገቡት የአለማችን ሶስቱ ግዙፍ የሞባይል አምራች ኩባንያዎች ሳምሰንግ፣ አፕል እና ሁዋዌ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ዚያኦሚ፣ ኦፖ እና ቪቮ ይከተላሉ ብሏል፡፡
በአመቱ ከ10 በመቶ በላይ የሽያጭ እድገት ያስመዘገቡት ሁለቱ ኩባንያዎች አፕልና ዚያኦሚ ብቻ እንደሆኑ ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ ሳምሰንግ እና ሁዋዌ ሽያጫቸው በሁለት ዲጂት መቀነሱንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 6868 times