Tuesday, 19 January 2021 00:00

የስንሻው ሹምዬ ”ማነው” ፊልም ጥር 24 ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

የደራሲና ዳይሬክተር ስንሻው ሹምዬ”ማነው” ፊልም በተለያዩ የግልና የመንግስት ሲኒማ ቤቶች ከትላንት ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ መታየት የጀመረ ሲሆን ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በድምቀት እንደሚመረቅ ደራሲና ዳይሬክተሩ ገልጿል፡፡ በቆንጆ ምስሎችና ቢንጎ ፒክቸርስ በጋራ የተሰራውና ልብ አንጠልጣይ ዘውግ ያለው “ማነው” ፊልም የ1፡30 ሰዓት ርዝመት ያለው ሲሆን በአንድ ቤተሰብ ላይ የተፈፀመን ወንጀል እየመረመረና የተመልካችን ልብ እያንጠለጠለ እስከ ፍጸሜው የሚያስጉዝ ነው ተብሏል፡፡
በፊልሙ ላይ “ላምባ” በተሰኘው የአንተነህ ሀይሌ ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት  እውቅናና ዝናን ያተረፈችው ወጣት ተዋናይት ሊዲያ ሞገስና በ”አሉላ አባ ነጋ “ቴአትር ላይ ዝናን ያተረፈው ተዋናይ ሄኖክ ዘርዓ ብሩክ በመሪ ተዋናይነት የተወኑበት ሲሆን ሌሎችም አንጋፋና ወጣት ተዋንያን እንደተሳተፉበት ታውቋል፡፡ በምስልና ድምጽ ቀረፃ ደረጃውን ጠብቆ አንደተሰራ የተነገረለት ፊልሙ ከትላንት ጀምሮ በተመረጡ የግልና የመንግስት ሲኒማ ቤቶች መታየት የጀመረ ሲሆን ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም ታዋቂ ሰዎች፣ የኪነ ጥበብ ቤተሰቦች፣የባህልና ቱሪዝም ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በልዩ ስነ-ስርዓት በብሄራዊ ቴአትር እንደሚመረቅ ታውቋል፡፡

Read 7801 times