Print this page
Tuesday, 19 January 2021 00:00

መንግስትን “አጣብቂኝ” የማስገባት፣ ተቃዋሚን “ማኖ” የማስነካት አመል፣ ለማንም አልበጀም።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

      “ዲሞክራሲዊ ከሆንክ፣ ከስልጣን እናወርድሃለን። እምቢ ካልክ ፣ አምባገነን ነህ”… የተባለ ገዢ ፓርቲ፣ ምን አማራጭ ይኖረዋል? አመፅ ሲመጣበት፣ ምን ያደርጋል? አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል።
ወይ በአቅመቢስነት መኮማተርና ስልጣኑን ጥሎ መሸሽ ነው። አልያም፣ እንደ አውሬ በእልህ ማበጥና አመፀኞችን ማሳደድ ነው።  ገዢው ፓርቲ፣ ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ እንዳይታየው ማድረግ፣ እንደ ፖለቲካ ጥበብና እንደ ጀብድ ሲቆጠር አስቡት። እንዲህ የሚያስቡ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጥቂት አይደሉም። መጨረሻቸው ሲያምር አላየንም እንጂ። ለፓርቲያቸውም፣ ለሌሎች ተቃዋሚዎች ጦስ ነው።
ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ወደ አጣብቂኝ ማስገባት የሚፈልጉ የገዢ ፓርቲ ፖለቲከኞችም፣ ሁልጊዜ ይኖራሉ። ጠንቃቃና ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አይመቻቸውም። ምን አይነት ተቃዋሚ ፓርቲ ነው የሚመቻቸው? ተቃዋሚ ፓርቲ፣ “ወይ፣ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ ደካማ ፓርቲ መሆን አለበት።” ወይም ደግሞ፣ ምን? በራሱ ጊዜ ለአመፅ የሚቸኩል የለየለት ነውጠኛ ተቃዋሚ፣ ለሰነፍ ባለስልጣናት ይመቻቸዋል። ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ለአመፅ የሚዘገይና የሚያመነታ ከሆነም፣ ትንሽ ሲገፋፉት በዘፈቀደ እየተደናበረ ወደ አመፅ እየተንደረደረ እንዲገባ ይመኛሉ ቀሽም ባለስልጣናት። በዚህም በዚያም አዋክበው፣ “ማኖ” ቢያስነኩት ይመርጣሉ። ይህንም እንደ ትልቅ የፖለቲካ ጥበብ ስለሚቆጥሩት፣ እጅግ የተራቀቁ ይመስላቸዋል።
ገዢው ፓርቲ፣ እንዲህ አይነት ቀሽም አባላትን ማስተካከልና መግራት ካልቻለ፣ እየዋለ እያደረ መዳከሙ አይቀርም። ሰነፍ አባላትና ባስልጣናት ወደ ቀውስ አዙሪት ሊያወርዱት ይችላሉ።
የቀሽም ተቃዋሚ ምኞት - መንግስትን ወደ አጣብቂኝ መክተት!
የሰነፍ ስኬት፣ ከስራ መገላገል አይደል? የቀሽም ተቃዋሚ ስሌትም፣ ከጥረት ማምለጥ ብቻ ይሆናል። ገዢው ፓርቲ፣ ገና ሲነኩት ምንም ሳያንገራግር ክንብል የሚል ከሆነ፣ “ስራ ቀለለልን” ይላል - ቀሽም ተቃዋሚ። በቃ፣ “በትግል፣ የዲሞክራሲ ለውጥ መጣ” ብሎ ስልጣን መያዝ ይችላል ማለት ነው።
ገዢው ፓርቲ፣ ቁጡ አውሬ ከሆነ ደግሞ፣ “ለውግዘት ቀለለልን” የሚል ስሜት ያድርበታል። ለምን? “ገዢው ፓርቲ፣ የለየለት አምባገነን ሆኗል” ብሎ በደፈናው መቃወም አይከብድማ። ለተቃውሞ የሚመቸን፣ ገዢው ፓርቲ ወይ አቅመቢስ ወይ አውሬ ሲሆን ነው? በዚህ ስሌት ከታሰበ፣ ገዢውን ፓርቲ አጣብቂኝ ውስጥ ማስገባት፣ “የረቀቀ የተቃውሞ ጥበብ” ይሆናል። ችግሩ ምንድነው?
ገዢው ፓርቲ፣ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ፣ አገር ሰላም አያገኝም። ተከባብሮ የመኖር እድል ይጨልማል። ገዢው ፓርቲ፣ ወይ ለአመፅ ተሸንፎ በትርምስ ይሸሻል። ወይ አመፅን አሸንፎ ትንሽ ትልቁን ሁሉ ያሳድዳል። አጣብቂኝ እንዲህ ነው። ወይ ይንቁታል፤ ደካማ ነው ብለው ይሰድቡታል፣ ይደፍሩታል።  ወይ ይፈሩታል፤ የሚረግሙት ግፈኛ ይሆናል፤ እያዋከበ ያንበረክካል። አጣብቂኝ ውስጥ ሌላ አማራጭ ይጠፋል። የመጠፋፋት መንገድ ብቻ ነው የሚቀረው። ወይ ይፈርሳል። ወይ ይደመስሳል። እንዲህ አይነት የጥፋት አጣብቂኝን ነው የምንፈልገው? ፈራሽ የመሆን ወይም ደምሳሽ የመሆን የትራጄዲ ድራማ፣ …. በሁለቱም አቅጣጫ፣ ምንም የሚያምር ነገር የለውም።
አሳዛኙ ነገር፣ የአገራችን ብዙ የፖለቲካ ዲስኩሮች፣ ወደዚህ የጥፋት አጣብቂኝ የሚያንደረድሩ ናቸው።
“መብቴን ማስከበር የመንግስት ግዴታ ነው። ለመንግስት ግን እውቅና አልሰጥም።”  በማለት ይጀመራል። ከዚያስ፣ ህግ አይገዛኝም ለማለት ምን ብሎ ይደሰኩራል? “አለቃችን ህዝብ ነው። ሕዝብ፣ የስልጣን ባለቤት መሆን አለበት።”ይላል። መንገዶችን መዝጋት፣ ከተሞችን መረበሽ፣ ገበያዎችን መበተን፣ ፋብሪካዎች ላይ መዝመት… የተቃውሞ መብት ነው። የህዝብ ጥያቄ ከሆነ፣ ሁሉም ነገር ይቻላል፤ የህዝብ ትግል ነው። መንግስት ግን፣ የሕዝብን ጥያቄ ለማፈን እርምጃ ይወስዳል። አምባገነን ነው። … ካልተወገደ መፍትሄ አይመጣም…” ብሎ ይፈርዳል።
ይሄ፣ የአጣብቂኙ አንድ ስለት ነው። “አምባገነን መሆን አያዋጣማ።”
ግን መንግስት፣ ረብሻንና ህገ-ወጥ ተግባራትን ለማስቆም እርምጃ ባይወስድስ? ... ይሄም አያዋጣውም።
መንገድ በመዝጋት የተጀመረው ተቃውሞ፣ በማግስቱ ንጥቂያ ይታከልበታል። በረብሻ የተቆለፈውን ገበያ፣ በማግስቱ እየሰበሩ የመዝረፍ፣ የማቃጠልና የማውደም ዘመቻ ይጨመርበታል። …ከዚህም ጋር ደብደባና ግድያ፣ ስደትና ጭፍጨፋ እንደሰደድ እሳት እየተዛመተ የሲኦል ትርምስ ይፈጠራል።
“መንግስት፣ የአገሬውንና የዜጎችን ህልውና ለመጠበቅ፣ ለማረጋጋትና ሰላም ለማስፈን አቅም የለውም፤ ካልተወገደ መፍትሄ አይኖርም። “ ተብሎ ይወገዛል።
ይሄ ደግሞ፣ የአጣብቂኙ ሌላኛው ስለት ነው። አምባገነንነትም፣  አቅመቢስ ድንዛዜም አያዋጣማ። በዚህም ተባለ በዚያ፣ መውጫ ቀዳዳ ወደሌለው አጣብቂኝ ውስጥ ገዢው ፓርቲ እንዲገባ ማድረግ ለማንም አይበጅም። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ ልማድ መላቀቅ ይኖርባቸዋል፤ ቀሽም አባላትንና አመራሮችን በመገሰፅ።
የቀሽም ባለስልጣናት ምኞትስ? ተቃዋሚን ማኖ ማስነካት!
ቢወድም ቢጠላም፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማሳተፍና ምርጫ ማካሄድ፣ ግዴታ የሆነበት ዘመን ላይ አይደል የምንኖረው? ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሁሉ ለማጥፋትና ምርጫን ለማስቀረት የሚሞክር ገዢ ፓርቲና ፖለቲከኛ ብዙ አይደለም። የሚመኝ ይኖራል። ለጊዜው ግን፣ ከምኞት አያልፍም። “የአለማችን ወቅታዊ ሁኔታ” አይፈቅድለትም። ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አስወግዶ፣ ምርጫም አስቀርቶ፣ በስልጣን ላይ መቆየት ለዓለማቀፍ ውግዘት ይዳርጋል። ምርጫ ማካሄድ የግድ ነው።
ግን ደግሞ፣ ምርጫ ማካሄድ ማለት፣ “የአመፅ ፈቃድ” እንደመስጠት እየተቆጠረ፣ ከባድ ፈተና ይሆናል። እንዳሻቸው በስድብና በውንጀላ ሁከት የማነሳሳት፣ ልዩ የአመጽ ፈቃድ የያዙ የሚመስላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ እየበረከቱና እየገነኑ እረፍት ይነሳሉ። በእርግጥ፣ አንዳንዶቹ የገዢ ፓርቲ ፖለቲከኞች፣ በዚህ አይጨነቁም። “የለየለት ነውጠኛ ተቃዋሚ ቢመጣ ልኩን እናሳየዋለን” ይላሉ።  ነውጠኛ ተቃዋሚ፣ ለሰነፍ ባለስልጣናት በጣም ቀላል ይሆንላቸዋል። በራሱ ጊዜ ኢላማ ውስጥ እንግባላቸው ይቆጥሩታል። ማኖ፤ ነክቶ ተመቻችቶላቸዋል። አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ምን አይነት ተቃዋሚ ነው? ቀይመስመር የማይጥስ፣ በዘፈቀደ የማይላተም፣ ጠንቃቃና ቆጠብ ያለ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ቢመጣ፣ ለቀሽም የገዢው ፓርቲ ፖለቲከኞች አይመችም።
ጠንቃቃና ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ “አስቸጋሪ” ነው። ንቀው አይረሱት ነገር፣ ጠንካራ ነው። አይዘምቱበት አያስወግዱት ነገር፣ ጠንቃቃ ነው፤ በዘፈቀደ ማኖ የማይነካ። አመፅን እርም ብሎ ባይርቅ እንኳ፣ ገና ከጅምሩ፣ ፊት ለፊት ለንክሻ አይካለብም። ለይቶለት ለአመፅ በግላጭ ከመሮጥ ይልቅ፣ ዳር ዳሩን፣ በዘወርዋራ መሆኑ ነው ችግሩ። ቀሽም የገዢ ፓርቲ ፖለቲከኞች፣ ይሄ ይሄ አይመቻቸውም። ሌላ አይነት ተቃዋሚ ፓርቲን ነው የሚመኙት። ምን አይነት?
ለስም ያህል ተቃዋሚ ፓርቲ ተብለው የሚመዘገቡና በዝምታ አርፈው የሚቀመጡ ይኖራሉ። ለታይታ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ተብለው በስም መታወቅና ዝና ማግኘት ብቻ የሚበቃቸው አቅመ ቢስ ደካሞችም አሉ። “ተቃዋሚ ፓርቲና ፖለቲከኛ በሙሉ፣ ተመዝጋቢና አጃቢ ብቻ ቢሆኑ ጥሩ ነበር” ብለው የሚመኙ  ናቸው ቀሽም የገዢ ፓርቲ ፖለቲከኞች አብዛኛው ሰውም ደካማ ተቃዋ ፓርቲዎችን ንቆ ይረሳቸዋል፤ የስድብ መለማመጃ ያደርጋቸዋል። ለገዢው ፓርቲም ይመቻሉ።  ግን አቅመ ቢስ ወይም አጃቢ ያልሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችስ? “የለየላቸው ነውጠኞች ከሆኑ ችግር የለውም፤ ማኖ ነክተው ይደመሰሳሉ።”  ይላሉ ሰነፍ ፖለቲከኞች።
ይሄው ነው የተቃዋሚ ፓርቲዎች አጣብቂኝ። “ወይ እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡ ደካሞች መሆን አለባቸው። ወይ በዘፈቀደ እየተደናበሩ ማኖ የሚነኩ የለየላቸው አመፀኞች መሆን አለባቸው።” ሁለቱም ብዙ አያስቸግሩም። ተቃዋሚ ፓርቲና ፖለቲከኛ ሁሉ እጃቸውን አጣፍጠው የሚቀመጡ፣ በአጃቢነት እየተጋበዙም የሚያጨበጭቡ ቢሆኑ፣ አንድ አማራጭ ነው። ገዢው ፓርቲ ይዝናናል። ወይ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ሁሉ፣ በፊት ለፊት ለይቶላቸው አመፅና ጦርነት ቢያውጁ፣ ሌላ አማራጭ ነው። ገዢው ፓርቲ አምርሮ እርምጃ ለመውሰድ ቀላል ይሆንለታል። ይህን በማሰብም ተቃዋሚ ፓርቲን ወይም ፖለቲከኛን “ማኖ” ለማስነካት የሚመኙ ባለስልጣናት ሁሌም ይኖራሉ። ይህን አመል መተው ይኖርባቸዋል።

Read 7239 times