Print this page
Monday, 18 January 2021 00:00

የግድቡን ድርድር የማጓተት ደባ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

ዲሞክራቲክ ኮንጎ በአፍሪካ በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ሥር ከነበሩ አገሮች አንዷና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አገር ናት። የሕዝብ ብዛቷ ከ89 ሚሊየን በላይ ነው። በአፍሪካ ከሚገኘው የውኃ ሃብት 52 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በዚህች አገር ሲሆን ከውኃ የኤሌክትሪክ ኃይል  የማመንጨት አቅሟም እጅግ ከፍተኛ ነው።
ከአስራ አንዱ የናይል ተፋሰስ አገሮች አንዷ የሆነችው ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ከአስር ዓመታት በላይ የወሰደው ድርድር ውስጥ የተሳተፈች አገር ብትሆንም የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ካላፀደቁት አገሮች አንዷ ናት። ሁለቱ ግብፅና ሱዳን ናቸው። በድርድር ጊዜ ሁሉ የግብፅና የሱዳን አቋም ብቸኛ ደጋፊም ናት። በቅርቡ የኮንጎው ፕሬዚዳንት አማካሪ ወደ ካይሮ በተጓዙ ጊዜ ያረጋገጡትም ኮንጎ፣ ግብፅ የያዘችውን የድርድር አቋም እንደምትደግፍና ከግብፅ ጎን እንደምትሆንም ነው።
ግብፅ ከፍተኛ የውኃና የማዕድን ሃብት ባለቤት ለሆነችው ዲሞክራቲክ ኮንጎ የልብ ወዳጅ ናት። የግብፅ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን፣ የኮንጐ ወንዝን በመጠቀም ከኪንሳሻ እስከ ኦምቢ  ከተማ ድረስ የሚዘልቅ የውኃ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲውል ለማድረግ የአዋጭነት ጥናት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አል ሞኒተር ከሁለት ወር በፊት ዘግቧል።
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ግብጽ በኮንጎ ወንዝ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚውል ግድብ ለኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑበሊክ ለመሥራት እየተዘጋጀች መሆኑ ቀደም ሲል መዘገቡ ይታወሳል። ለምን ተግባራዊ ማድረግ  እንዳልተቻለ  ባይታወቅም፣ ግብጽ ከኮንጎ ወንዝ ውኃ በመጥለፍ የናይል ወንዝ ፍሰትን ለማጎልበት ሃሳብ እንዳላትም ስትናገር ነበር፡፡
ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያን በአሳሪ ስምምነት ውስጥ ለማስገባት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በምንም አይነት ምክንያት በውኃ ሃብቷ ላይ ያላትን የመጠቀም መብቷን አሳልፋ ላለመስጠት በገጠመችው ትግል፤ የሶስቱ አገራት ድርድር እንደተለመደው ተቋርጧል። ድርድር እየተካሄደ የነበረውን ደግሞ ሱዳን የሁለቱ ማለትም የሱዳንና ኢትዮጵያን ስምምነት አፍርሳ፣ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ “የተወሰደብኝን ግዛት አስመልሻለሁ” እያለች መግለጫ እየሰጠች ባለችበት ጊዜ መሆኑም ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል፡፡ ወረራው ኢትዮጵያን በወታደራዊ ጫና ለማንበርከክ ታስቦ መሆኑ ደግሞ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ዲና ሙፍቲ ጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ፤ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገውን ድርድር፣ ግብጽና ሱዳን በየምክንያቱ እያጓተቱ ያሉት፣ የአፍሪካ ህብረት የሊቀ መንበርነት ወንበር የዲሞክራቲክ ኮንጐ እጅ እስኪገባ ድረስ መሆኑን አስታውቀዋል። ዲሞክራቲክ ኮንጐ ደግሞ ወንበሩን መያዟ የማይቀር መሆኑም የታመነበት ይመስላል።
ስለዚህ ምን መደረግ አለበት? የኮንጐው ፕሬዚዳንት የሚይዙት የሊቀ መንበርነት ወንበር የአፍሪካ እንጂ የኮንጐ ወይም የግላቸውን ባለመሆኑ በእያንዳንዱ ጥቃቅን ጉዳይ እሳቸውም ሆኑ እሳቸውን ተከትለው ወደ ድርጅቱ የሚያመሩ የሀገራቱ ዲፕሎማቶች በገለልተኝነት መንፈስ መያዛቸውን ማረጋገጥ፣ ፈንገጥ ሲሉ ከሥር ከሥር ማጋለጥ የኢትዮጵያ ኃላፊነትና ተግባር ይሆናል።
ምንም ሆነ ምንም ኢትዮጵያ እየታገለች ያለችው በራሷ የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም መብቷን ይበልጥ ለማረጋገጥ በመሆኑ፣ ይህን መብት በምንም አይነት ምክንያት የሚቀንስ ስምምነት እንደማትቀበል በድፍን ሳይሆን በዝርዝር ለዓለም በማሳየት ልትፋለማቸው ይገባል።
በመጪው ጊዜ ግብፅና ሱዳን ድርድሩን በእነሱ ፈቃድ አለመሄዱን ዘርዝረው ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ሁሉ ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሊወስዱትና ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ሥጋት እንደሆነ ሊያስረዱ ይችሉ ይሆናል። ኢትዮጵያ በበኩሏ ችግሩ የተፈጠረው ሁለቱ አገሮች በተደጋጋሚ እየተጠየቁ ኢትዮጵያን አግልለው፣ በ1929 እና በ1959 የዐባይ ውኃ ውል በተዋዋሉ ጊዜ መሆኑን በማውሳት፣ አካባቢው እንዲያገኝ፣ የችግሩ ምንጭ የሆነው የቀደመው ስምምነት፣ በሶስቱ መካከል እንደ አዲስ እንደገና እንዲጻፍና እንዲፈረም መጠየቅ፣ ጥያቄውንም በምክር ቤቱ ጠረጴዛ ላይ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡
ሱዳኖች ሰሞኑን "ኢትዮጵያ ውኃ ልትሸጥልን እያሰበች ነው" በማለት የዓለም መገናኛ ብዙኃንን እያጨናነቁ ነው፡፡ ኢትዮጵያም "ካላችሁ መልካም ነው፤ እኔም ሆንኩ እናንተ ከሌሴቶ መማር ይኖርብናል" ብትላቸው ደግ መልስ ነው፡፡Read 2177 times