Saturday, 16 January 2021 11:24

መቋጫ ባጣው የመተከል ጥቃት ወር ባልሞላ ጊዜ ከ350 በላይ ዜጎች ተገድለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  በማክሰኞው ጥቃት ከ80 ሺ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል
                             
              በመተከል ዞን በተፈፀመ ጥቃት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ350 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን የጠቆመው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በአጠቃላይ ባለፋት አምስት ወራት ከ5 መቶ በላይ ዜጎች በግፍ ተገድለዋል ብሏል ሪፖርቱ፡፡
“መቆሚያ ያጣው በመተከል ያሉ ሰዎች እልቂት!” በሚል መሪ ቃል ከትናንት በስቲያ የአካባቢውን ሁኔታ የተመለከተ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ያወጣው ኢሰመጉ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን፣ ድባጤ እና ዳንጉር ወረዳዎች እስካሁን እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉ በእጅጉ አሳሳቢ ነው ብሏል።
ባለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ ላይ በመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ፣ ታጣቂዎች  ባደረሱት ጥቃት ከ100 በላይ (የመንግስት ሪፖርት 207) ንፁሃን መገደላቸውን ሪፖርት ማድረጉን ያስታወሰው ኢሠመጉ፤ ለዚህ ጥቃት መንግስት አፋጣኝና የተጠና ምላሽ አልሰጠም ሲል ተችቷል።
ታህሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም በዚያው ዞን ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ የሚሄድ መኪና ውስጥ የነበሩ ተጓዦች፣ ማንዱራ ከተማ ላይ በታጣቂዎች እንዲወርዱ ተደርጎ አንድ ሰው መገደሉንና ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ተቋሙ ጠቁሟል።
ከሰሞኑ ደግሞ፣ ጥር 2 እና 3 ቀን 2013 ዓ.ም በቡለን እና በጉባ ወረዳዎች፣ ኦሜድላና አዳነሽምስ በተባሉ ቀበሌዎች ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና በርካታ የመኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ኢሠመጉ አስታውቋል።
በድባጤ ወረዳ ቆርቃ ቀበሌ ዳሊቲ በተባለች መንደር ባለፈው ማክሰኞ ጥር 4 ቀን 2013 ከሌሊቱ 11፡30 ጀምሮ የኦነግ ሸኔ እና የቤኒን ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ82 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ከአካባቢው የዓይን እማኞች ማረጋገጡን፤ ነገር ግን ከሚደርሱት መረጃዎች አንፃር ከ100 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ የገለጸው ኢሠመጉ፤ በዚህ ጥቃትም ሴቶችና ህፃናት በአብላጫው ሰለባ መሆናቸውን አመልክቷል።
በዚህ ጥቃት ከ80 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውንም የኢሰመጉ ሪፖርት ጠቁሟል።
ከጥቃቱ የተረፈ አህመድ ይማም የተባለ ግለሰብ 82 አስከሬኖች መቁጠሩንና 22 ሰዎች መቁሰላቸውን ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ባለፈው ረቡዕ ተናግሯል። “ቀስትና ጥይት ጥቃቱን ለመፈጸም በጥቅም ላይ ቢውሉም በአብዛኛው በስለት ነው የተጠቀሙት” ብሏል አህመድ፡፡ ከ100 በላይ መሳሪያ የታጠቁ ግለሰቦች በማክሰኞው ጥቃት መሳተፋቸውን ለሮይተርስ በስልክ የተናገሩት የ60 ዓመቱ ወርቁ አህመድ፤ አንዳንዶቹ ዩኒፎርም የለበሱ ስለነበር ሊለይዋቸው እንደማይችሉ ጠቁመዋል።
“የእኔና የወንድሜን መኖሪያ ቤት ከ200 ከብቶችና 11 ፍየሎች ጋር አቃጥለውብናል” ብለዋል ለሮይተርስ
በድባጤ ወረዳ በርካታ ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች አሁን ድረስ በፀጥታ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ያመለከተው ኢሰመጉ በበኩሉ፤ መንግስት ድርጊቱን የሚፈጽሙ አካላትን አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድ እንዲሁም ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የሲቪል ማህበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማትና የሃገር ሽማግሌዎች በመንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ፣ የመተከል ዞን በአስቸኳይ በፌደራል መንግስት አስተዳደር ስር እንዲሆን ጠይቋል።


Read 10707 times