Saturday, 16 January 2021 11:08

አዳዲሶቹ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች ወደ 70 አገራት ተሰራጭተዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በጃፓንም አዲስ የቫይረሱ ዝርያ ተገኝቷል

            ከመደበኛው የኮሮና ቫይረስ ጋር ሲነጻጸር በፍጥነት የመሰራጨት አቅማቸው ከፍተኛ እንደሆነ የተነገረላቸውና በብሪታኒያ እና በደቡብ አፍሪካ የተገኙት አዳዲሶቹ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በድምሩ ከ50 በላይ ወደሚሆኑ የአለማችን አገራት መሰራጨታቸውን እንዲሁም በጃፓን ደግሞ አዲስ የቫይረሱ ዝርያ መገኘቱን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
ከአንድ ወር በፊት በብሪታኒያ የተገኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ወደ 50 የተለያዩ የአለማችን አገራትና ግዛቶች መዛመቱንና በደቡብ አፍሪካ የተገኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ደግሞ ወደ 20 አገራትና ግዛቶች መሰራጨቱን ድርጅቱ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
አዳዲሶቹ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች ከ70 በላይ አገራትና ግዛቶች ተሰራጭተዋል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው የአለም የጤና ድርጅት፤ ባለፈው ሳምንት በጃፓን በአዲስ የኮሮና ቫይረስ የተጠቁ 4 ብራዚላውያን መንገደኞች መገኘታቸውንና በቀጣይም አዳዲስ የቫይረሱ ዝርያዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉና አለማችን በአዲስ የኮሮና ወረርሽኝ ማዕበል ልትመታ እንደምትችልም ስጋቱን ገልጧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሁንም በመላው አለም በፍጥነት መሰራጨቱን እንደቀጠለ የገለጸው ድርጅቱ፤ አለማቀፉ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፉት 10 ሳምንታት ብቻ በእጥፍ በማደግ ከቀናት በፊት ከ90 ሚሊዮን ማለፉንና የሟቾች ቁጥርም ወደ 2 ሚሊዮን መጠጋቱን አስታውሷል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ለተጠቁባት አፍሪካ 300 ሚሊዮን የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ከአለማቀፉ የክትባት ጥምረት መገኘቱንና ክትባቶቹ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለተለያዩ አገራት ይከፋፈላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል እንዳስታወቀ አሶሼትድ ፕሬስ አስነብቧል፡:፡
በአፍሪካ ከሚኖረው አጠቃላይ ህዝብ 60 በመቶውን ወይም 780 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ መታቀዱንና ለዚህም 10 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ 1.5 ቢሊዮን ያህል ክትባቶች እንደሚያስፈልጉም ዘገባው አመልክቷል፡፡


Read 3895 times