Print this page
Saturday, 16 January 2021 11:10

ኪሊማንጃሮ ተራራ አናት ላይ የአፍሪካ ህብረት ባንዲራና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ይሰቀላል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  ዘንድሮ ለ8ኛ ጊዜ የሚካሄደው “ጉዞ አድዋ” ዛሬ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግቢ ውስጥ በምክትል ከንቲባዋ አዳነች አበቤ፣ በሃይማኖት አባቶችና በሀገር ሽማግዎች ፀሎት፣ ምርቃና የሰላም ግቡ ንግግር  ይጀመራል። የዘንድሮውን ጉዞ አድዋ ለየት የሚደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው? ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር በጸጥታው ዙሪያ ስጋት የለም ወይ? ምን ያህል ሰዎች በጉዞው ይሳተፋሉ? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከ”ጉዞ አድዋ” መስራቾች አንዱ ከሆነው አርቲስት ያሬድ ሹመቴ ጋር ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርጋለች።


              የዘንድሮው ጉዞ ምን መልክ አለው? የተለዩ ነገሮችስ ተካትተውበታል?
ዘንድሮ የአድዋ ድል የተገኘበት 125ኛ ዓመት ነው የሚከበረው። በጉዞው ላይ 125 ሰዎች ይሳተፋሉ አጠቃላይ የጉዞው መርሃ ግብር ዛሬ ጠዋት ይጀመራል። ለ46 ቀናት ነው የእግር ጉዞው የሚደረገው።  እንደምታውቂው ጉዞ አድዋ ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው።
ኪሊማንጃሮ ተራራን የሚወጡ ተጓዦች እንዳሉ ሰምቻለሁ…
እውነት ነው። ዘንድሮ የአድዋ ድል “የአፍሪካ ድል” (Victory of Africa) በሚል መሪ ቃል ነው የሚከበረው። እናም የአድዋን የአፍሪካ ድልነት ለመላው አፍሪካ ለማብሰር፣ ሰባት ተጓዦች የአድዋ በዓል ቀን፣ ኪሊማንጃሮ አናት ላይ ይወጡና፣ የአፍሪካ ህብረትን ባንዲራ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ፣ የጉዞ አድዋንና የምድረ ቀደምትን አርማ ይሰቅላሉ። ይህ የሚሰራው ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ነው። የተራራው አናት ላይ ለመድረስ የ8 ቀን ጉዞ መጓዝ ያስፈልጋል። ስምንት ቀን ከተጓዙ በኋላ ልክ የአድዋ በዓል ቀን አራቱን ሰንደቆች (አርማዎች) ተራራው አናት ላይ ይሰቅላሉ። አድዋ የአፍሪካ ድል መሆኑንም ያበስራሉ ማለት ነው።
ኪሊማንጃሮን የሚወጡት ተጓዦች እነማን ናቸው?
በዚህ ኪሊማጃሮን የመውጣት ጉዞ ላይ የሚሳተፉት ሰባት ሰዎች ከመጀመሪያው ዙር “ጉዞ አድዋ” እስከ ሰባተኛው ማለትም እስካለፈው ዓመት ድረስ በየዙሩ የተሳተፉ ናቸው። አንዱ ከጉዞ አድዋ አንድ፣ ሁለተኛው ከጉዞ አድዋ ሁለት እየተመረጡ፣ እስከ ሰባተኛው ዙር የተጓዙ ናቸው። በጉዞው ሁለት ሴቶችና አምስት ወንዶች ናቸው የሚሳተፉት።
ዘንድሮ የምታደርጉት ጉዞ ከቀድሞዎቹ ጉዞዎች በጣም በተለየ ድባብ ውስጥ የሚደረግ ነው መንግስት ህግ ለማስከበር እርምጃ እየወሰደ ባለበት ወቅት ማለቴ ነው። ስለዚህ የጸጥታው ጉዳይ አላሰጋችሁም?
እኔ ለዚህ ጥያቄሽ ባጭሩ ስመልስ፣ ጉዞ አድዋን እስከ ዛሬ እየተስተናገድን፤ ሄደናል አያስቸገርንም ተጉዘናል። ችግር የመጣ ቀን ግን መቅረት የለብንም። አንዱም የዘንድሮው የጉዞ አላማ ችግርንም ለመካፈል ጭምር ነው። አገራችን ሰላም እንዲሆን እንፈልጋለን።  ሰላም ያጣ ህዝባችን መሃል ደግሞ ራሳችን  ሰላም አጥተንም ቢሆን መጓዝ መሞከሩ የበለጠ ዋጋ ስላለው በፍፁም ማቋረጥ የለብንም ብለን ነው ዛሬ ጉዞውን የጀመርነው።
ስለዚህ ጉዞ አድዋ አንዱና ዋናው ዓላማው ኢትዮጵያ በፍቅር፣ በሰላም በአንድነት የሚኖሩባት እንዲሁም ዜጎቿ ተከባብረውና ተደማምጠው ለጋራ እድገት በጋራ የሚቆሙባት አገር እንድትሆን ነው ፍላጎታችን። በመሆኑም አሁን የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ወይም አሁን ያለው የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ስጋቱ የቱንም ያህል ስጋት ቢሆንም እንኳን በጆሮአችን ከመስማት ባለፈ ቦታው ላይ ተገኝተን ለማየት በልበ ሙሉነትና የእውነትም ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት ያስፈልጋል። የከፋ ችግር እንዳይመጣ ደግሞ ለሁሉም አካል ጥሪ ነው የምናቀርበው። በተለይ ለፀጥታ አካላትና ለመንግስት ማለቴ ነው። ህዝቡ እንኳን ጥሪ የሚያቀርቡለት አይደለም። ሁሌም ለመቀበል ዝግጁ ነው።
ስለዚህ ይሄ ጉዞ የሰላም ጉዞ ነው፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር የተሳተፉበት፣ አንድም ሰው ያልጎደለበት የሁላችንም የድል በዓል ስለሆነና ያንን አንድነት በሚያንፀባርቅ መልኩም ስለምናከብረው የከፋ ችግር ይገጥመናል ብለን አናስብም። ነገር ግን ጥንቃቄም ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ከሚመለከተው አካል ጋር እየተመካከርን፣ ጉዟችንን እንቀጥላለን። እንደሚታወቀው ጉዞው ከመንግስት እውቅና አለው። እውቅና አለው ሲባል ጉዞ አድዋን መንግስት ያውቀዋል ማለት ብቻ ሳይሆን የዘንድሮን ጉዞ ለማድረግም የሚያስችለንን ፈቃድ ከመንግስት አግኝተናል። ይህ ማለት መንግስት የዘንድሮውን የአድዋ በዓልም ለማክበር እንደውም በተለየ ሁኔታ መዘጋጀቱን ያሳያል። ይሄ አንዱ ጥሩ ማስተማመኛ ስለሆነ ያግዘናል ብለን እናምናን። ከዚያ ውጪ ጉዟችን የድል ጉዞ በመሆኑና ህዝቡን በመተማመን የሚደረግ ጉዞ በመሆኑ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በስኬት እጠናቅቃለን ብለን እናምናለን።
በዘንድሮው ጉዞ ከእድሜም ከእውቅናም አንፃር ለየት ያሉ ተጓዦች አሉ?
በዘንድሮው ለየት የሚለው ትልቁ የእድሜ ጣሪያ 38 ዓመት ነው። በፊት የ54 ዓመት ጎልማሳም ተጉዞ ያውቃል። በዘንድሮው ግን አብዛኛው ተጓዥ ወጣት ነው ማለት ይቻላል። ከእውቅና አንፃር ላልሽው “በጉዞ አድዋ” አስተሳሰብ ሁሉም ተጓዥ እኩል ነው። እከሌ ታዋቂ ነው፤ እከሌ ደረጃው ይሄ ነው የሚባል መደላድል አይወጣም። ስለዚህ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከኪነ-ጥበብ እያልን ስታተስ አናወጣም።
ከ125ቱ ተጓዦች ምን ያህል ሴቶች ይሳተፋሉ? ከአዲስ አበባ ውጪ ካሉ አካባቢዎች የተሳተፉ አሉ?
ዘንድሮ  ከሚጓዙት ከግማሽ በላይ ያህሉ ከአዲስ አበባ ውጪ ካሉ የሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚሳተፉ ናቸው። 63ቱ ማለቴ ነው። ስለዚህ ከሰሜንም ከደቡብም፣ ከምዕራብ ከምስራቅም.. ከሁሉም አካባቢ ሊባል በሚችል ደረጃ የተውጣጡ ናቸው። ቀሪዎቹ ከአዲስ አበባ ሲሆኑ ከ125ቱ 18ቱ ሴቶች ናቸው። ስብጥሩ በጣም የሚያስደስት ነው።
የሽኝት ስነ-ስርዓቱ ምን ይመስላል? ከጉዞ መልስ እንደ ከዚህ ቀደሙስ የእውቅናና የኪነ-ጥበብ ምሽት ታዘጋጃላችሁ?
የሽኝት ስነ-ስርዓቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግቢ ውስጥ (ማዘጋጃ ቤት) ውስጥ ነው የሚካሄደው። ጉዟችን ከዜሮ ኪ.ሜ ነው የሚጀምረው። ዜሮ ኪ.ሜ የሚለካው ደግሞ ከምንሊክ አደባባይ ነው። የሽኝት መርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳች አበቤ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባትና ሌሎችም ጥሪ የሚደረግላቸው እንግዶች በሚገኙበት ተጸል©ልንና ተመርቀን ነው የምንሸኘው። እንደ ከዚህ በፊቱ፣ ፎክረን ሸልለን ጉዞ የምንጀምረትበት ሁኔታ ላይ አይደለንም። አገራችን ከምንጊዜውም በላይ ፀሎት የሚያስፈልጋት ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው። በእርግጥ ከዚህ በፊትም ፀሎትና ምርቃት ተደርጎልን ነው የምንጓዘው። ነገር ግን አሁን ላይ በሀገራችን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት እንዲሰፍን ጸሎት የሚስፈልግበት ጊዜ በመሆኑ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ጭምር በሽኝት ስነ-ስርዓቱ ላይ ተጋብዘዋል። የቀድሞ ተጓዦችም በሽኝቱ ላይ ይሳተፋሉ። ተጓዦችን አጅበው ከአዲስ አበባ እስኪወጡ የሚሸኙ አጃቢ ተጓዦችም እንደዚሁ ተገኝተው ይሸኙናል።
ከጉዞ ስንመለስ እንደተለመደው ተጓዦችን ሜዳሊያ የመሸለምና እውቅና የመስጠት መርሃ ግብር አገርን ከፍ ከሚያደርግ  የኪነ-ጥበብ ምሽት ጋር በጣይቱ ሆቴል ወይም በሌላ ቦታ ይኖረናል ማለት ነው። በዚህ አጋጣሚ ለጉዞ አድዋ መሳካት ጊዜያቸውን እውቀታቸውን ቤተሰባቸውን …ሁሉ ሰጥተው አብረውን ለሚሆኑ፣ “እንዴት ሆናችሁ? ምን ልታደርጉ አሰባችሁ” እያሉ ልክ እንደ እናንተ የሚጠይቁንንም የሚዲያ አካላት በጉዞ አድዋ ስም አመሰግናለሁ።Read 2580 times