Saturday, 16 January 2021 11:03

የአሜሪካ ሴናተሮች የኢትዮጵያ መንግስት የሚዲያ ነፃነትን እንዲያከብር ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

መንግስት ያሰራቸውን ጋዜጠኞች እንዲፈታና የሚዲያ ነፃነትን እንዲያስጠብቅ የአሜሪካ ሶስት ሴናተሮች ከትናንት በስቲያ ለጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፃፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል።
ሴናተር ክሪስ መርፊ፣ ሴናተር ፓትሪክ ሌይ ቤን ሴናተር ቤን ካርዲን ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በፃፉት ደብዳቤ፤ ባለፉት ጥቂት ወራት መንግስት ጋዜጠኞችን በማዋከብ በሚዲያ ነፃነት ላይ ጥቃት ሲፈጸም ቆይቷል ብለዋል።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ 13 ጋዜጠኞች መታሰራቸውንና ከእነዚህ  ውስጥ  7 ያህሉ በትግራይ ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር ተያይዞ የታሰሩ መሆናቸውን የሚዲያዎችን ሪፖርት በመጥቀስ ያመለከቱት ሴናተሮቹ፤ እነዚህ የእስር አዝማሚያዎች የሃገሪቱን የሚዲያ ነፃነት የሚፈታተኑ ናቸው ብለዋል።
በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንዲሁም ለሚዲያ አፈናዎች በር የሚከፍቱ አካሄዶችን መንግስታቸው እንዲያጤንና የሚዲያ ነፃነት የበለጠ እንዲጠናከር  ሴናተሮቹ በደብዳቤቸው ጠይቀዋል።
ከ13ቱ የታሰሩ ጋዜጠኞች 12ቱ ከፖለቲካ አቋምና ዘገባዎች ጋር  በተያያዘ መታሰራቸውንና አንድ ጋዜጠኛ ብቻ ከኮቪድ 19 ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተሳሳተ መረጃ በማስተላለፍ በሚል መታሰሩንም ሴናተሮቹ ጠቁመዋል።
ከጋዜጠኞች  እስር ባሻገር የኢንተርኔትና አፈና የሃገሪቱ ዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት እየገደበ ያለ፣ ዲሞክራሲን የማያበረታታ አካሄድ መሆኑም በደብዳቤው ተመልክቷል። በትግራይ ክልል የኢንተርኔት አግልግሎት እንዲለቀቅም ሴናተሮቹ ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በፃፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል።

Read 11394 times