Saturday, 16 January 2021 10:33

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አበርክቷቸው እውቅና ሊሰጣቸው ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  በቅርቡ 70ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ያከብራሉ
                                 
           እውቁ ፖለቲከኛና ምሁር የኢሶዴፓ መስራችና ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ በፖለቲካው ትግል ውስጥ ለነበራቸው የረጅም ጊዜ የሰላማዊ ትግል እሳቤና አበርከቶ እውቅናና ሽልማት ሊበረከትላቸው ነው፡፡
እውቅናና ሽልማቱ የሚበረከትላቸው በቀጣዩቹ ሳምንታት 70ኛ ዓመት የልደት በዓል በሚያከብሩበት ጊዜ እንደሆነ ለዚሁ ሥነ-ስርዓት የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ አስተባባሪዎች ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት በጌት ፋም ሆቴል “የሰላማዊ ትግል ፋይዳ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን በዚሁ መድረክ ላይ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ፕሬዚዳንት አረጋሃዊ በርሄ  (ዶ/ር)፣ ወዳጄነህ መሃረኒ (ዶ/ር)፣ የፍልስፍና ምሁሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር እና አምባሳደር ተስፋዬ ሀቢሶ  በሰላማዊ ትግልና ፋይዳው ዙሪያ እንዲሁም በዚህ የትግል ዘርፍ ፕሮፌሰሩ የነበራቸውን አስተዋፅኦ ባደረጉት ንግግር ገልፀው ምስጋና አረዋቸዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ራሳቸው ባደረጉት ንግግር፤ በምንም ሁኔታ ቢሆን ሰላማዊ ትግል ተመራጭ መሆኑንና ጊዜ ቢወስድም ውጤት እንደሚያመጣ አብራርተዋል። “አንዳንድ ደፋርጋዜጠኞች ጉዳዩን ባለመረዳት ሰላማዊ ትግል ሰላማዊ ትግል ትላለህ፤ ምን ጠብ ያለልህ ነገር አለ? በሚል ይጠይቁኛል” ፕሮፌሰሩ “ሰላማዊ ትግል ግን በብዙ መልኩ አትራፊ ነው፡፡” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።  በርካታ ምሁራን ወዳጆቻቸው፤ የስራ ባልደረቦቻቸው፣ አብሮ አደጎቻቸውና አድናቂዎቻቸው በሚገኙበት ከሳምንት በኋላ 70ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን የሚያከብሩት ፕሮፌሰር በየነ ጰጥሮስ እስከ ዛሬ በመጡበት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በእጅጉ ደስተኛ እንደሆኑም  ተናግረዋል፡፡
ብሔራዊ ኮሚቴው፤ የእውቅና የምስጋና መርሃ ግብሩና 70ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው፣ ክብራቸውን በሚመጥን ሁኔታ እንዲካሄድ፣ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።

Read 1348 times