Wednesday, 13 January 2021 20:09

በ2020 በአውሮፕላን አደጋ 300 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት  በመላው አለም 40 የአውሮፕላን አደጋዎች መከሰታቸውንና በእነዚህ አደጋዎች በድምሩ 300  ሰዎች ለሞት  መዳረጋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአመቱ የተከሰቱ የአውሮፕላን አደጋዎች ቁጥር ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያህል ቢቀንስም፣ በአደጋዎቹ የደረሰው ጥፋት ግን በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ላለፉት 20 ያህል አመታት እያደገ የነበረውን የአውሮፕላን መንገደኞችን ቁጥር ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲቀንስ እንዳደረገው ሲሪየም የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የአለማቀፍ የአውሮፕላን መንገደኞች ቁጥር ከአመት በፊት ከነበረበት በ67 በመቶ ያህል ቀንሷል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ተቋሙ፣ የአገር ውስጥ በረራ መንገደኞች ቁጥር በአንጻሩ በ40 በመቶ ያህል መቀነስ  ማሳየቱን አስታውሷል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በአመቱ ከ40 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ አገራት አየር መንገዶች ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ ከማቆማቸው ወይም ከማቋረጣቸው ጋር ተያይዞ በቀጣዩ አመትም የመንገደኞች ቁጥር ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተቋሙ ጠቁሟል፡፡
የአለማችን አየር መንገዶች ባለፈው የፈረንጆች አመት በድምሩ 16.8 ሚሊዮን በረራዎችን ማድረጋቸውን ያስታወሰው የተቋሙ ሪፖርት፣ በ2019 የተደረጉት በረራዎች ግን 33.2 ሚሊዮን እንደነበሩ አክሎ ገልጧል፡፡


Read 2289 times