Thursday, 14 January 2021 00:00

ኬኩን እየበሉ "ኬክ አለኝ” ማለት አይቻልም

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)

 "ስለ ሕጋዊነት የሚብሰከሰኩት የደርጉ ሊቀ መንበር፤ አስተዳደራቸው ከሕግ ጋር ይተዋወቅ ነበር ማለት ያስቸግራል። በቅርብ ታሪክ ከታዩ መንግሥታት በደም አፋሳሽነቱ ወደር አልነበረውም።--"
             
            ‘የኢትዮጵያ ሕዝብ’
ሰሞኑን ከቀድሞ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያ ባልደረባ አዲሱ አበበ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የኮሎኔል መንግሥቱ ሃይለማርያም ልጅ ዶ/ር ትዕግሥት፤ አባታቸውን ለፍርድ ለማቅረብ መንግሥት የነበረውን ብቃት ጥያቄ ውስጥ አስገብተዋል። “የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፍርድ ሊያቆመኝ ከፈለገ እቆማለሁ። ነገር ግን ወያኔ ፍርድ ቤት ውስጥ አልቆምም” ብለዋል፤ ሲሉ የአባታቸውን አቋም አስረድተዋል። አስተያየቱ:- የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት እንዴት ነው የሚታወቀው? በእሳቸው ፍርድ መቅረብ ዙሪያ ሕዝበ ውሳኔ መሰጠት አለበት ወይ? በየትኛውስ ሀገር ነው ተጠርጣሪዎች በሕዝብ ስምምነት ለፍርድ የሚቆሙት? የሚሉ ጥያቄዎችን ያስነሳል።
ከ60 ዓመት በፊት ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከሰው የሞት ቅጣት በተፈረደባቸው ወቅት ይግባኝ ይሉ እንደሁ ሲጠየቁ፤ “የሚመለከትልኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢሆን ኖሮ ይግባኝ ማለት በፈለግሁ ነበር” ብለዋል እየተባለ ይነገራል። በቅርቡ በሀገራችን በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በሽሽት ላይ ያሉት የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ተይዘው ለፍርድ ቢቀርቡ የከሳሻቸውን ሕጋዊነት መሞገታቸው አይቀርም። እነ አቶ ጌታቸው ረዳን የመሳሰሉ ባለሥልጣናት ከመስከረም 25 በኋላ ያለው መንግሥት ተቀባይነት እንደሌለው ይናገሩ ስለነበር፣ ይህ ጥያቄ ቢቀርብ የሚገርም አይሆንም።
መንግሥት ማነው?
ማንኛውም አካል በግድም ሆነ በውድ ሥልጣኑን በሕዝብ ላይ ጭኖ ማስተዳደር ከቻለ መንግሥት ይሆናል የሚል የፖለቲካ አስተሳሰብ አለ። ማክስ ዌበር የተባለው ጀርመናዊ የማህበራዊ ሳይንስ ሊቅ፤ የመንግሥት ሕጋዊነት ምንጭ የሆኑ ሶስት ሁኔታዎችን ያብራራል፡-  በምርጫ መምጣት፤ የተቀባሁ ነኝ ብሎ መንገሥና ለዘር ማስተላለፍ (ንጉሳዊ አገዛዝ)፤ እንዲሁም በመፈንቅለ መንግሥትም ይሁን በሌላ በጉልበት ሥልጣን መጨበጥ። ስለዚህ ሕወሓት/ኢህአዴግ ከአንዱ ወይም ከሁለቱም የተቀነጫጨበ ባህርይ ያለው ሲሆን  ኮሎኔል መንግሥቱን ችሎት ለማቆም የማንንም መልካም ፈቃድ አይጠይቅም።
የሞራልና ሕግ ብቃት የሚለው በትምህርት ዓለም ለሚደረጉ ውይይቶች ይጠቅም ይሆናል እንጂ መሬት ላይ ባለው ሁኔታ ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ አይሆንም። ሥርዓቱን መውደድና መጥላት ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የለውም። ኮሎኔል የሚፈልጉት “የሕግና የሞራል ብቃት” ያለው መንግሥት ከምፅዓት በፊት ይመጣል ተብሎ አይታሰብም።
"ሀገር ወዳዱ መሪ"
ስለ ሕጋዊነት የሚብሰከሰኩት የደርጉ ሊቀ መንበር አስተዳደራቸው ከሕግ ጋር ይተዋወቅ ነበር ማለት ያስቸግራል። በቅርብ ታሪክ ከታዩ መንግሥታት በደም አፋሳሽነቱ ወደር አልነበረውም። 17ቱ ዓመታት የጦርነት፥ የረሃብ፥ የነፃነት እጦት ዘመናት ነበሩ። ዜጎች መገደላቸው ሳያንስ ለተረሸኑበት ጥይት ክፍያ የሚጠየቁበት፤ የምሁራን ሬሳ በየጎዳናው የሚጣልበት፤ የጦር መኮንኖችን “ማዕረጋቸውን በመቀስ ቆረጥንላቸው” እያሉ ማበሻቀጥ ወግ  የነበረበት ሥርዓት ነው። በዘመኑ ሞት ተራ ከመሆኑ የተነሳ በሥልጣናቸው ላይ የሚመጡትን ትተን በማጀት ጉዳይ እየገቡ የበርበሬ ዋጋ ጨመሩ ተብለው የሚገደሉ ሰዎች ነበሩ።
አንድ አንቀፅ የሚወጣው ማዕረግ ደራርበው የሥርዓቱ ፊታውራሪ የነበሩት ‘ሀገር ወዳዱ መሪ’፤ ከማንም በላይ ሙሉ ሃላፊነት ወስደው ለዳንሱ መዘጋጀት ነበረባቸው። ነፃና ገለልተኛ የሚባለውን የሕግ ሥርዓት እሳቸውን የሚገዳደሩበት ምንም ሃይል የሌላቸውን እዛው ቤተ መንግሥት አስረው ያቆይዋቸውን 12 ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ከማስረሸናቸው በፊት ሊያሳዩ በተገባ ነበር። ይህ እንግዲህ ሕዳር 17 ቀን 1967 ዓ.ም. እጅ እያወጡ ሞት የፈረዱባቸውን 60 ባለሥልጣናት ሳናነሳ ነው። ዶ/ር ትዕግሥት ገና ማዳመጫ አንገታቸው ላይ ሳያንጠለጥሉ የተጎጂ ቤተሰቦችን የልብ ትርታ ለማዳመጥ ዕድል አግኝተዋል።
“‘እኔ አባት የለኝም - አባቴ ሞቷል
ምን ሆነው ነው የሞቱት?
ከ60ዎቹ መሀል አንዱ ነው
የቶቹ 60ዎች?
እንዴት ነው አንቺ 60ዎቹን የማታውቂው?’
ብለውኝ ቤት መጥቼ አባቴን ጠይቄ ነው ምን እንደተፈጠረ የተረዳሁት” ሲሉ በቃለ ምልልሱ ተደምጠዋል።
ቀድሞ እንደሰማነውና በድጋሚም እንዳስገነዘቡን ኮሎኔሉ “ለትንኝ የሚያዝኑ” ሰብዓዊነትን የተላበሱ ናቸው። እንደዚህ አይነት ሰብዕና ያለው ግለሰብ ለፍርድ ለመቅረብ መፍራት የለበትም። እርግጥ ዶ/ር ትዕግሥትን ሊደግፋቸው የሚችለው “ጊዜ ቁስልን ያደርቃል” እንደሚባለው እነዚህ ጉዳዮች የተፈፀሙባቸው ጊዜያት ስለራቁ ሰው ይረሳል፤ በሀገሪቱም ተቋማዊ የማስታወስ ችሎታ ባለመዳበሩ መንግሥቱ የተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች ይከስማሉ የሚል ነው። ቃለ ምልልሱን ተከትሎ ከሰፈሩት አስተያየቶች መካከል ጀግንነታቸውንና ሀገር ወዳድነታቸውን የሚጠቅሱ አሉ። ያ የልብ ልብ ይሰጣል።
ሁሉም ነገር ወደ ሃራሬ
መንግሥቱ ኃይለማርያም ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም. ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛን የሚጎበኙ መስለው መጀመሪያ ኬንያ፣ ከዛም በሌላ አውሮፕላን ወደ ዚምባብዌ አምርተዋል። ሀገሪቱን ከነፃነት ጊዜ ጀምሮ ለ37 ዓመታት የመሯት የሮበርት ሙጋቤ ልዩ እንግዳ ሆነው ኖረዋል። ከሙጋቤ ህልፈትም በኋላ ቤተኛ ናቸው። ልጆቻቸው በሀገሪቱ ሆስፒታሎች ይሰሩ እንደነበር ይነገራል። ጥገኝነቱ የተቸራቸው ሮዴሽያ ተብላ ትታወቅ የነበረችው ሀገር ለነፃነት ታደርገው ለነበረው ትግል ድጋፍ በመስጠታቸው ውለታ ለመመለስ የተደረገ መስተንግዶ እንደሆነ ይታመናል። መንግሥቱ ዕድለኛ ሆነው በተጠረጠሩበት የዘር ማጥፋት ወንጀል ለፍርድ ሳይቀርቡ ሰላሳ ዓመታት ዚምባብዌ ተደላድለው በመቀመጥ ሶስት ልጆቻቸውን ዩጋንዳና ምናልባትም ጀርመን ልከው ህክምና አስተምረዋል።
መንግሥቱ በሌሉበት የታየው የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ 14 ዓመት የፈጀ ሲሆን ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው መጀመሪያ እድሜ ልክ በኋላ ግን አቃቤ ሕግ ይግባኝ በመጠየቁ በግንቦት 2000 ዓ.ም. ሞት ተፈርዶባቸው መዝገቡ ተዘግቷል። በዛው መዝገብ ተመሳሳይ ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች ቅጣቱ ወደ እድሜ ይፍታህ ተቀይሮላቸው ሃያ አመታት በእስር ካሳለፉ በኋላ በ2004 ዓ.ም. በአመክሮ ተለቅቀዋል።
የሰሞኑ ቃለ ምልልስ ኮሎኔሉ ኢትዮጵያ እንዲገቡ በስማ በለው ጥሪ የቀረበበት ይመስላል። “እንቅልፍ የሚነሳኝ ጧት ማታ ከጭንቅላቴ የማይወጣው ሀሳብ፣ አባቴ ሀገሩን ሳያይ በሰው ሀገር እንዳያልፍ ነው። እንደዚህ ሸክም ሆኖ የሚከብደኝ ነገር የለም…አባቴን ኢትዮጵያ ውስጥ የማስገባት ፕላን በቀን በቀን የምፀልይባቸው ጉዳዮች ናቸው” ይላሉ፤ የኮሎኔል መንግስቱ ሁለተኛ ልጅ።
በነገራችን ላይ መንግሥቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክል ሕግም ሆነ ጥሪ አልቀረበም። በተቃራኒው በተለይ በ1980ዎቹ መጨረሻ የዚምባብዌ መንግሥት አሳልፎ እንዲሰጥ ጥያቄዎች ሲቀርቡ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይልቁንስ ግራ የሚያጋባው በተደጋጋሚ የሚነሱት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች በምን በምን አድርጎ ከክሱ ጋር እንደሚያያዝ ነው። ልዩ አቃቤ ሕግ ክስ ሲመሰርት አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ስራ ላይ አልዋለም ነበር። ወንጀለኛ መቅጫው ገና ሰው ከእንቅልፉ ሳይነቃ በ1949 ዓ.ም. የወጣ ሲሆን ‘ጓድ ሊቀ መንበር’ በቀኝ ጎናቸው ሲነሱ ይጠቀሙበት የነበረ ሕግ ነው።
‘ቁርጡን ንገሪኝ’
“እንኳንስ የሰው ሕይወት ቀርቶ ትንኝ ያሳዝነኛል የሚለው እውነቱን ነው … ንብም ይሁን ሸረሪት አትግደሉ የሚል ሰው ነው።” እንደዚህ ሰብዓዊነት ያላቸው ከሆኑ በሕግ አደባባይ ለመታየት ምንም የሚያስፈራ ነገር ሊኖር አይገባም። ለትንኝ የሚያዝን ሰው ምህረት መጠየቅ አይገባውም። ፍርድ ቤት ነፃ ያወጣዋል። እንደዛ አይነት መከራከሪያ ግን በተፈፀመው ጥፋት ያለመፀፀትን የሚያሳይ እንጂ ምህረትን የሚጠይቅ ሰው የሚያቀርበው መለማመኛ አይደለም። በደቡብ አፍሪካ የዘር መድልዎ ሥርዓት መፍረስን ተከትሎ፤ በከፊል ደግሞ በሩዋንዳና በላይቤሪያ በተካሄዱ የእርቅና ሰላም ጉባኤዎች አጥፊዎች ድርጊታቸውን ተናዝዘዋል። የሰሩትን ወንጀል በማመን ይቅርታ ጠይቀዋል። ሂደቱ ተበዳዮች እርም እንዲያወጡ ረድቷል። ያንን ምዕራፍ በመዝጋት ወደፊት እንዲራመዱ አስተዋፅኦ እንዳበረከተም ይታመናል።
በ’መንጌ’ የሥልጣን ዘመን ሀገሪቱ ብርክ ውስጥ እንደነበረች ምንም የፖለቲካና የታሪክ ትንተና ሳያስፈልግ ከልጅነት ጓደኞች ግንኙነት ማየት ይቻላል።
እነ ጄኔራል ተፈሪ በንቲን ገድለው “አብዮቱ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት” መሸጋገሩን ስላበሰሩበት ጥር 26 ቀን 1969 ብዙ ተብሏል። በዛ ዕለት ‘ቆራጡ መሪ’ ብቻ ሳይሆኑ መላው ቤተሰብ ለሰዓታት ታንክ ውስጥ ተደብቆ ነው የተኩስ ልውውጡን ያሳለፈው። መቼም ከዛ በኋላ የቤተ መንግሥት ታንኮች መፀዳጃ ሳይገባላቸው አልቀረም። በዚያ ቀውጢ ሰዓት ሽንት መውጫ ችግር ሆኖ እንደነበር ሰምተናል። ያኔ ያፋፋሙት ቀይ ሽብር ቤታቸውን እንዳያንኳኳ ልጆቻቸውን ለስድስት ዓመት ሩሲያ (በወቅቱ ሶቪየት ሕብረት) ልከው ደብቀዋል። እዛም ከአንዷ ጋር ሲጫወቱ ተገፋፍተው “የመንግሥቱ ልጅ ብትሆኚ የምፈራሽ መሰለሽ” የሚል ነገር ተነስቷል። 

በትምህርት ቤት ጨዋታ ላይ ጓደኛዋ ጫማዋን ትሰርቃትና በካልሲ ብቻ በመሆኗ መምህሯ ያሾፈች ስለመሰላቸው አንቺ ልትረብሺ ነው ብለው እጇን በማስመሪያ መቷት። በዛ የተነሳ ከልጅቷ ጋር ተጣላች። ቤት ስትገባ ለአባቷ ታሪኩን ታስረዳለች። አባትም (መንግሥቱ) ይቅርታ እንድትጠይቅ ነገሯትና በማግስቱ ይቅርታ ልትጠይቅ ሄደች። ጓደኚት ካሁን አሁን ወታደር በሩን ሰብሮ ይገባል ስትል እንቅልፍ ባይኗ ሳይዞር ነግቷል።

እንደዚህ አይነት በሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚታዩት ሁኔታዎች ቁጥር ሆነው ብቻ ከሚቀሩት የሟቾች ብዛት  ባልተናነሰ በሀገሪቱ ያጠላውን ዳመና ያሳያሉ።
በተረፈ ግን መንግሥቱ ከሁለቱ አንዱን ነው መምረጥ ያለባቸው። ወይ “ጥፋት ሰርቻለሁ ይቅርታ ይደረግልኝ።” አለበለዚያም “ትንኝም ገድዬ የማላውቅ ሰብዓዊነት የሚሰማኝ ፍጡር ነኝ” ብለው ችሎት መዋል አለባቸው። አለበለዚያ ኬኩን እየበሉ ”ኬክ አለኝ” ነው የሚሆነው።


Read 4196 times