Saturday, 09 January 2021 11:46

ሀገር አንድ አራሽ…. አንድ ቀዳሽ….አንድ ተኳሽ ያስፈልጋታል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ከእለታት አንድ ቀን  አንድ ንጉስ ፈላስፋቸውን ጠርተው  እንዲህ አሉት።
“ሶስት ልጆች አሉኝ። የትኛው የተሻለ እንደሆነ ግን አላውቅም። እስኪ የእውቀታቸውን ልክ የሚያሳይ ጥያቄ ጠይቅልኝና ልኬታቸውን ልወቅ” ሲሉ አማከሩት።
ፈላስፋውም፡-  
“እሺ ንጉስ ሆይ! አንድ አይነት ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ ከዚያም መልሶቻቸውን እናወዳድራለን”  አላቸው።
 በዚሁ ስምምነት ላይ ተደረሰና ጥያቄው በተናጠል ቀረበላቸው።
ለአንደኛው- “ለመሆኑ ለአንድ ሀገር ምን ያስፈልጋታል ብለህ ታስባለህ?”
እሱም-  “አራሽ ያስፈልጋታል" አለ
ለሁለተኛውም-  "ለመሆኑ ለአንድ ሀገር ምን ያስፈልጋታል ብለህ ታስባለህ?” ተብሎ ሲጠየቅ
መልሱ “ተኳሽ ያስፈልጋታል”
ሶስተኛውም- "ለመሆኑ ለአንድ ሀገር ምን ያስፈልጋታል ብለህ ታስባለህ?” ተብሎ ሲጠየቅ
"ቀዳሽ  ያስፈልጋታል" ብሎ መለሰ።
ፈላስፋውም ለንጉሱ እንዲህ አላቸው።
“ንጉስ ሆይ፤ ሁሉም በየበኩላቸው ትክክለኛ መልስ መልሰዋል፤ሁሉም ትክክለኝነታቸው  የዋናውን መልስ አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው።  ስለዚህ የሽልማቱን ነገር እርስዎ ቢያስቡበት ነው የሚሻለው” አላቸው።
ንጉሱም ነገሩን አሰላስለው፤
“እንደዚያማ ከሆነ ሽልማቱን ሲሶ ሲሶ መካፈል አለባቸው፤ ምክንያቱም  የጥያቄው ሙሉ መልስ፡-
ሀገር  አንድ አራሽ …. አንድ ቀዳሽ…. አንድ ተኳሽ ያስፈልጋታል ነው፤ በአንድም በሶስትም መንገድ  እምትንቀሳቀስ መሆኑ ላይ ነው። አሉና “ሶስቱንም ይባርክልን” ሲሉ አሳረጉ።
*   *   *
እነሆ ይህን አባባል  በተዘዋዋሪ መንገድ ስናጤነው፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ባህል  ለአንድ ሀገር  ወሳኝ አንጓዎች ናቸው እንደማለት ነው። ምነው ቢሉ፤ አራሹ አርሶ የምግብ ፍጆታችንን ካላሟላልን፤ ወታደሩም የመከላከያ ኃይሉም ተጨንቆና ተጠቦ ዳር ድንበራችንን በልበ ሙሉነት ካልጠበቀልን፤ ቄሱ  ከመቅደሱ ቆሞ  በምህላ ካላገዘን  አገር አትፀናም፡፡  ከዚህ በላይም ደግሞ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለን፤ “አገር እንደ ኮረዳ አካል ያለ ፍቅር አትጠናም።"  
የሀገር ፍቅር እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የሀገር ፍቅር ሲባልም ለልጆቻችን የምንሰጠው ፍቅር፣ ለአባቶቻችንና ለእናቶቻችን የምንሰጠው ፍቅር፣ ለህዝባችን የምንሰጠው ፍቅር፣ ለመልክአ ምድራችንም የምንሰጠው ፍቅር ማለት ነው።
ለዚህ ሁሉ ማእቀፍ ይሆን ዘንድም ለታሪካችን፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ ያለን አክብሮት ታላቅ ቦታ የሚቸረው ነው። እነዚህ ሶስት አላባውያውን በግማሽ-ጎፌሬ ግማሽ-ልጭት  ስንቆምባቸው ረጅም መንገድ ሄደናል። አሁን ግን ቢያንስ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ረግተው የሚኖሩባትን እናት ሀገር  እንተውላቸው እያልን ነው። ልቧ ባዶ ፣ሌማቷም ባዶ የሆነች ኢትዮጵያን እንዳናወርሳቸው እንጨነቅ፣ እንጠበብ።
- የሚታደጓትን ወጣቶች፣ ሴቶችና ሀገር ጠባቂዎች  ፈጥረንላታል ወይ?
- ትምህርትና ጤና  መስፈርቱን ባሟላ ሁኔታ ተይዟል ወይ?
- ኢኮኖሚዋ እያደገ ነው እየቀጨጨ?
-  ምሁራኗ ያገባኛል የሚል ተቆርቋሪነት አላቸው ወይ? ወይስ የምን ግዴ እየመሩ ነው?
- መምህራን ለተማሪዎች ያላቸው ኃላፊነት ምን ይመስላል?
- ፕላንና እቅድ አውጭዎቻችን የነደፉትን ሀሳብ  እስከ ፍጻሜው የመከታተል ሀሞት አላቸው ወይ?
- ጥያቄዎቻችን አያሌ ናቸው፡፡ ጥቂት ትጉሃን  ቢያንስ የሚያነሱት ጥያቄዎች  በቀና እንዲጠየቁ ማድረግና ለመፍትሄያቸው ቀና ሰዎች የሚታቀፉበት ቡድን  መፍጠር ጤናማ አካሄድ ይሆናል።
ዙሪያችንን በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ወረራ - ከበባ መኖሩ አያጠራጥርም።  የጥንትም የአሁንም ከባቢዎች የየበኩላቸውን እኩይ ወረራ  ለማካሄድ መለስ ቀለስ ማለታቸው  ዛሬ ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው። ስለሆነም ዙሪያ ገባውን  በአይነ ቁራኛ ማየት  የሚመለከተው ሁሉ ግዴታ ነው።  በጥንቱ አነጋገር ፡-
"ለአፍ ልመና ሳይያዙ ገና
ከተያዙ ብዙ ነው መዘዙ” ማለት ግድ ነው።
ዛሬም  ደግመን ደጋግመን  ሀገር  አንድ አራሽ …. አንድ ቀዳሽ…. አንድ ተኳሽ  ትፈልጋለች የምንለው ከላይ ባነሳናቸው ምክኖች ሳቢያ ነው!


Read 13761 times