Saturday, 09 January 2021 11:29

የሱዳን ወታደሮች በድንበር አካባቢ ንፁሀን ኢትዮጵያውያንን ገድለዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   የሱዳን ወታደሮች በሃይል በያዙት የድንበር አካባቢ በርካታ ንጹሃን ኢትየጵያውያንን መግደላቸውን የኢትዮጵያ መንግስት ያስታወቀ ሲሆን የሱዳን መንግስት የተፈጠረውን ችግር በዲፕሎማሲያዊ ውይይት ለመፍታት እንደሚፈልግም ገልጿል፡፡ ደቡብ ሱዳን በበኩሏ የሱዳን መንግስት ውይይትን እንዲያስቀድም አሳስባለች።
የሱዳን ወታደሮች በከባድ መሳሪያና መካናይዝድ ጦር በመታገዝ በድንበር አካባቢ ወረራ መፈፀማቸውን ጠቁሞ፤ በዚህ ወቅትም በርካታ ንጹሃን መግደላቸውን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
በአካባቢው በግብርና ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ሃብትና ንብረታቸውን መዘረፋቸውንና  በርካቶች በሱዳን  ወታደሮች መገደላቸውን  ያመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ለሀገራቸው መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሠጡት የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ቃመር አልዲን በበኩላቸው፤ የሃገራቸው ጦር አወዛጋቢ ሆኖ የቆየውን  የአልፋሽቃ አካባቢን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩንና ከእንግዲህ በኋላ ችግሩ ሊፈታ የሚችለው በዲፕሎማሲያዊ ውይይት  ብቻ መሆኑን ነው የተናገሩት ፡፡
ቀደም ሲል የኢትየጵያ መንግስትም በተመሳሳይ ችግሩን ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ውይይትን እንደሚያስቀድም የገለፀ ሲሆን እስከ አሁን ሁለቱ ሃገሮች በጉዳዩ ላይ አለመምከራቸው ተጠቁሟል።


Read 24837 times