Saturday, 11 August 2012 10:27

ማዘር ቤቶች!

Written by  ዘካርያስ አትክልት
Rate this item
(0 votes)

አረቄ ቤት ቺርስና ዲጄ የለም

32 እና 34ን አያውቋቸውም? ይሄ እንኳን ጐጃም በረንዳን አልፈው፤ በሜይ ዴይ ትምህርት ቤት ገባ ብሎ ያለው፡፡ እንዴ … ከአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ጀርባ ያለው እኮ ነው፡፡ 32 ቀበሌና 34 ቀበሌ ይባላሉ፡፡ ወዳጄ፤ በዚህ መንደር ያሉት ቤቶች ፍቅረኛሞች ይመስላሉ፡፡ እፍግፍግ ብለው፤ ትስርስር ያሉ ፍቅረኛሞች፡፡ ፍቅራቸው ግድግዳ እስከመጋራት እሚዘል የምስኪኖች መኖሪያ፡፡ መንደሩን ሾፍ ሲያደርጉ እነዚህ ቤቶች በዓይንዎ መቅረፀ ምስል ላይ እርፍ ይላሉ፡፡ ድንገት ሣት ብልዎት ብረት ጊቢ ሊያዩ ይችላሉ፡፡ ፐ! የሀብታም ቤት ካሉ ተሳስተዋል፡፡ ብረት በሩ ሽፋን ነው፡፡ በሩን ተሻግረው ሲገቡ ነፍ ማዘር ቤቶች፣ አረቄ ቤቶች፣ ማደሪያ ቤቶች…ያገኛሉ፡፡

ቤቶቹ በጠቅላላ ማለት ይቻላል G+1 ናቸው፡፡ መቼም በእርሶ ቤት G+1 ማለት ቤት በቤት ላይ የተደረበበት ነው፡፡ ለመንደሩ ግን ይሄ አይደለም - ሌላ ነው፡፡ አራት በአራት የሆነች ጠባብ ቤት በጣውላ ወይም በአጠና ለሁለት ተከፍላ ላይዋ ቆጥ፣ ታቿ ሣሎን ማለት እኮ ነው - G+1፡፡  በመንደሩ ውስጥ ያሉት ቤቶች በሙሉ ማለት ይቻላል፤ አረቄ ቤት፣ ማደሪያ ቤት፣ ዶቴ ቤት (ቁማር ቤት)፣ ማዘር ቤት፣ በርጫ ቤት ናቸው፡፡

እያንዳንዱን ሙድ እነሆ:-

ድንገት እግር ጥልዎት ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት በኋላ 32 እና 34 ቢመጡ በየሁለት ሜትር ርቀት “አልጋ አለ …አልጋ ትፈልጋለህ … ንፁህ አልጋ … ክፍል ለብቻ…ንፁህ ፍራሽ አለ…ወለል ትፈልጋለህ…” የሚልዎት ልጅ እግር፣ ሴቶችና እናቶች ያጋጥምዎታል፡፡ መሄጃ ከሌለዎትና በኪስዎ ውስጥ ያለው ብር ከተመናመነ አልጋ በአስራሁለት ብር፣ ክፍል ለብቻ ብለው ተነጋግረው ወደ መኝታዎ (አልጋዎ) ይሄዳሉ፡፡

ልክ ቤቱን ሲያዩ ክው ይላሉ፡፡ ጠባብ ቤት፤ 3በ3 ወይም 4በ4 የሆነ፡፡ ቆይ አልጋዎን ላሣይዎት ብላ ያመጣችዎት ልጅ በመሠላል ወደ ቆጥ ወጥታ ክፍል ለብቻው ያለችዎትን ቤት ታስረክብዎታለች፡፡ እዛች ቆጥ ላይ እኮ ነው፡፡

ክፍል ለብቻው ያለችዎ’ኮ ቆጥ ላይ/ምድር (ሣሎን) ውስጥ ስድስት ሰባት አልጋ ተደርድሮ አልጋዎቹ በመጋረጃ ወይም በካርቱን የተከፈሉትን ነው፡፡ ንድድ ይሉና መቼስ ምን ይደረጋል ብለው ብርድልብሱን ገልጠው አረፍ እንዳሉ፤  “የእንኳን ደህና መጣህ” አቀባበል የሚያደርጉልዎ ክስትስት ያሉ ትኋኖች ናቸው፡፡ ገና ከማረፍዎ አፍታ እንኳን ሳይቆዩ ውርር ያደርግዎታል፡፡

አከክ አከክ ቢያረጉም እነሱ አይቀንሱም፡፡

ንድድ ብለው ብርድልብስዎትን ቢገልጡ ሰውነትዎ ሁላ በተባይ ተሞልቷል፡፡ ብሽቅ ብለው እዚህ አላድርም፣ የፈለገ ነገር ይምጣ ይሉና ሱሪዎትን ታጥቀው እግርዎትን መሬት ሊያስረግጡ ቢሞክሩ መሬት ይናፍቅዎታል፡፡

አልጋ ስሩና ወለሉ በጠቅላላ “በኬሻ በጠረባ” ተከራዮች ተወሯል፡፡ (ኬሻ በጠረባ - ወለል ላይ ኬሻ ተነጥፎ እሚተኛበት ነው፡፡) ይቅርታ ጠይቀው… ተለማምጠው … እንደምንም ቤቱን ለቀው ላጥ!

ለምቦጭዎትን ጥለው አሁን የት ነው እምሄደው? በዛ ላይ ብሬ ትንሽ ናት… ምናምን እያሉ ሰዓት ሲያዩ ከምሽቱ ሰባት ሰዓት ሆኗል፡፡ አስፓልቱን ይዘው ወደ ዋናው መንገድ ሲጓዙ እግር ኳስ፣ አባሮሽ፣ መዝሙር…የሚጫወቱ ህፃናትን ያያሉ፡፡ “ማነህ አቡሽ መሽቶ የለ’ንዴ ወደ ቤት ግባ እንጂ” ብለው ቢመክሩ ህፃናቶቹ ተሰብስበው ይላጡብዎታል፡፡

እነዚህ ህፃናት’ኮ ተረኞች ናቸው፡፡ ቀን ከትምህርት መልስ ይተኛሉ፡፡ ሌት አልጋቸው ይከራያል፡፡ እርስዎ ደግሞ ቶሎ ነገር ይግባዎት እንጂ…

ሃሳብዎ ግራና ቀኝ ተማትዎብዎት ሲጓዙ፣ ቀድመው የሰሙት ድምጽ ጆሮዎት ውስጥ ይገባና ጭስስ ያደርግዎታል፡፡ “አልጋ አለ…ክፍል ለብቻ አልጋ አለ…ወንድም አልጋ ትፈልጋለህ…”

***

ወዳጄ፤ በ32 እና 34 የትኛውም አረቄ ቤት ብትገባ አንድ ወይም ሁለት የፊት ጥርስ የሌላቸው ቀምቃሚዎች አታጣም፡፡ በተለይ አይናቸው ልዩ ነው፤ የሆነ ጥቁር በቢጫ፣ ጥቁር በቀይ፣ ደብዛዛ ጥቁር በደብዛዛ ነጭ ምናምን ነው፡፡ ሁሉም ህይወት ያደቀቃቸው ህያው ምንዱባን ናቸው፡፡ ጉስቁልቁል ያሉ፡፡

ባለባበስም በሞራልም… እኔ ሠርኬ ጋ እየጠጣሁ ነው፡፡ የደሞዜ ቀን እኮ ነው፡፡ አዲስ ወሬ የለም፡፡ ምንም ጨዋታም የለም፡፡ ደበረኝ፡፡ ሒሳቤን ከፍዬ ልወጣ ስል ከጐኔ ከተቀመጡ ጓደኛሞች አንዱ “አንድ ልጠጣ በናትህ?” ይጠይቃል ጓደኛውን፡፡ “የያዝኩት 6 ብር መሆኑን እየነገርኩህ” ይላል ሌላው፡፡

ችስታ መሆናቸው ገባኝና አስቀድቼላቸው ወግ ጀመርን፡፡ ብዙ አወራን፡፡ በመጀመሪያ ከሰማኋቸው ቀልዶች አንዷን፡-

ራሺያ ውስጥ አንድ ሰነፍ ወታደር አለ፡፡ በቃ ኢላማውን ጠብቆ ተኩሶ መትቶ አያውቅም፡፡ ሁሌ ይተኩሳል፤ ሁሌ ይስታል፡፡ አለቃው በጣም ተናደደና ሠራዊቱን ሰበሰበ፡፡ “ጓዶች፤ ይሄ ወታደር በተደጋጋሚ ኢላማውን ያልጠበቀ ተኩስ በመተኮስ ይታወቃል፡፡ ወታደር አልሞ የጠላቱን ልብ በጥይት ካልነደለ ምኑን ወታደር ይባላል?” አለ የሰነፉን ወታደር ክንድ ይዞ፡፡ ተሰብሳቢው በሆታ “አይባልም” አለ፡፡ “ይሄ ሰነፍ ስንፍናውን እንዳያጋባብን ሊቀጣ ይገባል፡፡ ቅጣቱንም ራሱ በራሱ ይወስዳል…” ይልና ራሱን እንዲያጠፋ ይወስናል፡፡

ሰነፉ ወታደርም ሰወር ካለ ስፍራ ይገባና ጥይት ይተኩሳል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ግን ሠነፉ ወታደር ይመለሳል - ወደ ካምፑ፡፡ አዛዡ ቱግ ብሎ “አንተ ራስህን አጥፋ ብዬህ አልነበረ?” ሲለው “ጌታዬ ራሴን ስቼው ነው!” አለ፡፡ …

የቺክ ጦስ!

የህሊናዬ አይኖች ካነቡባቸው የቀምቃሚዎች ታሪክ ባጭሩ እነሆ፡- ፋሲካ ይባላል፡፡ አዲስ አበባ ነው የተወለደውና ያደገው፡፡ በትምህርቱ ጐበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች አንዱ ነበረ፡፡  ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሲገባ የሆነች አማላይ ቺክ ሾፈ፡፡ አፈቀራት፡፡ ፍቅሩን እንዳይገልጽ ፈራ፡፡

ጠዋት የሠልፍ ስነ-ስርዓት ላይ፣ ወደ ምሣ ሲለቀቁ፣ ከሠዓት ወደ ቤት ሲሔዱ ተከታትሎ ያያታል፡፡ የዓይኑ ምግብ አደረጋት፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ማጠቃለያ ፈተና ተፈትኖ ሦስት ነጥብ አራት አመጣ፡፡ ደስ አለው፡፡ ደስታው ግን ምሉዕ አልሆነም፡፡ የልቡን ቋንቋ የሚገልጽበት ዓይኑ የሁለት ዓመት ፍቅሩን ፈለገ፡፡ ህይወት አልተሣካላትም፡፡ ውጤቷ ለቴክኒክና ሙያ የሚያበቃ ነበር፡፡ አዘነ፡፡ የህይወት እንባ ደስታውን አጠበው፡፡ ተጨነቀ፡፡ ጥሏት የመሠናዶ ትምህርት መማር እንደማይገባው ወሠነ፡፡ በስንት አታካራ ቤተሠቦቹን አሣምኖ አብሯት ለመማር ተመቻቸ፡፡ ህይወት ሴክሬቴሪ ደረሣት፡፡

እርሱ ሠርቬይንግ ደረሠው፡፡ ተናደደ፡፡ ሴክሬተሪ ነው መማር የምፈልገው ብሎ የኮሌጁ ዲን ጋ አመለከተ፡፡ ማንም አልሠማውም፡፡ አሁንም ያያታል፡፡ ውበቷን ሲገልጽ “የወጣላት ቆንጆ ነች” ይላል፡፡ ሁለተኛ ዓመት ላይ ህይወት ጓደኞች አበዛች፡፡

ከተለያየ ዲፓርትመንት ተማሪዎች ጋር፡፡ ፋሲካ ለዓመታት ያፈቀራትን እንዳያጣ ለልቡ ድፍረትን ማስተማር ያዘ፡፡ “አንቺን አፍቅሬ ነው እዚህ የመጣሁት፡፡” ብሎ የማትሪክ ውጤቱንና ይቺ ዓረፍተ ነገር የተፃፈባት ብጣሽ ወረቀት ሠጣት፡፡ ችላ አለችው፡፡ የኔ ብቻ ነች ሲለው የነበረው ዓይኑ ነደደ፡፡ ከሠዎች ጋር ሆና ማየት አስጠላው፡፡ እሷን የሚቀርቧትን ወንዶችን በሙሉ አጠና፡፡ ከሁሉም ጋር ተደባደበ፡፡ ተወጋ፡፡ ወጋ፡፡ ተፈነከተ፡፡ ፈነከተ፡፡

ኮሌጁ በዲሲፕሊን ግድፈት አሠናበተው፡፡ የእናቱና የአባቱ ልፋት አሣዘነውና ራሱን ከቤተሠቦቹ አሠናበተ፡፡ አሁን የአውቶቢስ ተራ ወዛደር ነው፡፡

ሌላ …

የደብረ ብርሀን ልጅ ነው - አልዓዛር፡፡ በጥሩ ውጤት 5 ኪሎ ዩኒቨርስቲ ገባ፡፡ የገና ማዕበል ይዞት ይሄ፡፡ ቤተሠቦች ዲግሪ ሲጠብቁ፤ እሱ ተባሮ መሄዱ አሣፈረው፡፡

ሠው ምን ይለኛል፡፡ ቤተሠቤ ያዝንብኛል፡፡ … በሚል ለትምህርት ወጥቶ ከቀረ 9 ዓመታት ነጐዱ፡፡

ሌላ …

ወያላ ነው፡፡ ጥሩ ብር ያገኛል፡፡ ለቤተሠቦቹ የመጀመሪያ ልጅ ስለሆነ ሀላፊነት ይሠማዋል፡፡ “ለእማዬማ … ለዓውዳመት የሆነ ነገር እልካለሁ” ብሎ ሦስት ወር በባንክ ብር ቀርቅሮ ዓውዳመቱ ሲደርስ ሱስ አሸንፎት እናቱን ሣያስደስት በጊዜያዊ ፈንጠዝያ ብኩን ሆነ፡፡ …

አረቄ ቤት መደበቂያ ነው፡፡ የህይወት ስህተትን ማርከሻ፡፡

ብቸኝነትን መፋቂያ፡፡ የህይወት ኩኩሉን የሚጫወቱ ሠዎች መከማቻ፡፡ ሁሉም ኩኩሉ ባይ፡፡

ህይወታቸውን በአርምሞ የሞሉ፡፡ … በሚኖሩበት ማህበረሠብ ውስጥ ባይተዋር የሆኑ፡፡ … የተስፋ ወጋገን የናፈቃቸው ምስኪኖች … አንጀታቸውን ለቃጠሎ፣ አዕምሮአቸውን ለድንዛዜ፤ ጉበታቸውን ለበሽታ አጋልጠው ውስጣዊ ሠላም እሚፈልጉ…

ጀለሴ፤ ጃምቦና ቢራ መጠጣት ለምደህ አረቄ ቤት ስትገባ እንዳትደናበር … አንድ ምክር ልምከርህ፡፡

አረቄ ቤት ውስጥ ቺርስና ዲጄ የለም፡፡ የሆነ ሙዚቃ ይከፈትልሀል፤ ማዳመጥ ነው፡፡ ጃንቦ ላይ እንደለመድከው ብርጭቆህን አንስተህ ከጓደኛህ ብርጭቆ ጋር አገናኝተህ “ቺርስ ለጤናችን” ብትል ሙድ ይያዝብሀል፡፡ ቆይ ግን ያረቄ ብርጭቆ ቺርስ አይወድለትም?

 

 

Read 2607 times Last modified on Saturday, 11 August 2012 10:45