Saturday, 26 December 2020 09:53

“በመተከል የተፈፀመው ጥቃት በባለስልጣናት የታገዘ ነው” - የጥቃቱ ሰለባዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

 • “ሰውም ሞቶብናል፤ ንብረታችን ወድሞብናል፤ የጫካ ነዋሪዎች ሆነናል”
            • “እኔ ራሴ 250 አስከሬን ቆጥሪያለሁ፤ አሁንም በየጫካው ፍለጋ ላይ ነን”
            • የሟቾች የጅምላ ቀብር ተፈፅሟል

        ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ክልል በመተከል በተፈፀመው አሰቃቂ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ከ100 በላይ ንፁሀን ዜጎች የተገደሉ ሲሆን ጭፍጨፋው የተረፉ ዜጎች ሃብት ንብረታቸው ተዘርፎ በጫካ ተደብቀው እንደሚገኙ ለአዲስ አድማስ የተናገሩ የጥቃቱ ሰለባዎች፤መንግስት በአፋጣኝ እንዲደርስላቸው ተማፅነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በመተከል ዞን በቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ መፈፀሙን እንዳረጋገጠ የጠቆመ ሲሆን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በበኩላቸው በክልሉ በተፈፀመው ጭፍጨፋ በእጅጉ ማዘናቸውን ገልፀው በአጥፊዎቹ ላይ የፀጥታ ሃይሎች የመጨረሻውን
የተቀናጀ እርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ የጥቃቱ ሰለባዎች በስም የሚጠቅሷቸው ሁለት የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት የመተከሉን ጥቃት በዋናነት እንደፈፀሙና እንዳስፈፀሙ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ ሁለቱ በስም ተጠቃሽ ባለ ስልጣናት ሰሞኑን በአካባቢው እንደነበሩና ማክሰኞ ዕለት ወደ መጡበት መመለሳቸውን ተከትሎ የቀበሌው ሊቀ መንበር “ሽፍቶች እየመጡ ነው፤ ተጠንቀቁ የሚል መልዕክት አስተላለፉ”፡፡ የሚሉት የጥቃቱ ሰለባዎች፤ ረቡዕ ንጋት 11 ሰዓት አካባቢ የተኩስ እሩምታ መጀመሩን ያስረዳሉ፡፡ በርካታ ጥይት በመኖሪያ ቤቴ ላይ
ተተኩሷል የሚሉት አቶ ጌታቸው የተባሉ የጥቃቱ ሰለባ፤ ጥቃቱን የፈፀሙት በቁጥር ከ3 መቶ የሚበልጡ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ልዩ ሃይል ልብስ የለበሱ እንደነበሩ ይናገራሉ። ጥቃቱንም በክላሽ፣በቦንብና በሌሎች በታጠቋቸው ከባድ መሳሪያዎች እንደፈፀሙ እሳቸውና ጥቂት ጓዶቻቸውም ባላቸው
መሳሪያ ጥቃቱን ለመከላከል መሞከራቸውን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ የታጠቁት ሃይሎች ጥቃቱን በሚፈፅሙበት ወቅትም ለ 20 እና 3 0 ዓ መት በ ጉርብትና አብረው የኖሩ የጉምዝ ተወላጆች፤ “ቀዮች” ተብለው የተለዩ የአማራ፣ አገው፣ ሽናሻና ኦሮሞ ተወላጆች መኖሪያ ቤቶችን በመጠቆም የጥቃቱ ተባባሪ እንደነበሩ መታዘባቸውን የዓይን እማኞች የጥቃቱ ሰለባዎች አሰረድተዋል፡፡ ጥቃቱ ሰው በመግደል፣ መኖሪያ ቤቶችን በማቃጠል፣ ከብትና ሌሎች ንብረቶችን በመዝረፍ የተፈፀመና አብዛኛዎቹን የአካባቢውን ነዋሪዎች በባዶ ያስቀረ መሆኑን የጥቃቱ ሰለባዎች ያስረዳሉ፡፡ መከላከያና የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ወደ ቦታው ከደረሱ በኋላ ታጣቂዎቹ መሸሻቸውን ጠቁመው፤ ከዚያም የሞቱ ሰዎች አስክሬን መሰብሰብ መጀመሩን ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እንዳረጋገጡ ተናግረዋል፡፡ አስክሬን “እኔ ራሴ 250 ቆጥሪያለሁ፤ አሁንም በየ ጫካው አስክሬን ፍለጋ ላይ ነን” ብለዋል አንድ የጥቃቱ ሰለባ፡፡ እስከ ሀሙስ ዕለትም አስክሬኖች በአንድ አካባቢ ተሰብስበው የመንግስት ባለስልጣናት የጥቃቱን መጠን እንዲታዘቡ ቢፈለግም ወደ አካባቢው ብቅ ያለ ባለስልጣን ባለመኖሩ በአካባቢው ሰዎች ርብርብ በጅምላ መቀበራቸውን የጥቃቱ ሰለባዎች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የሰሞኑን ጥቃት ያነጣጠረባት የበኩጂ ቀበሌ7 ሺ በላይ ነዋሪዎች ያሉባት ስትሆን በብዛት ሽናሻዎች፣ አገዎች፣ አማራዎችና ኦሮሞዎች የሚኖሩባት መሆኗን በጥቃቱም
በብዛት እነዚሁ ብሄረሰቦች ሰለባ መሆናቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች ጠቁመዋል፡፡ ከጥቃቱ በኋላ ህዝብ በሙሉ ከመኖሪያ ቤቱ ሸሽቶ ወደ ጫካ መግባቱን፣ እስከ ሀሙስ ድረስም በጫካ ውስጥ እንደነበሩ የጠቆሙት ነዋሪዎች፤ በአካባቢው አልፎ አልፎ የተኩስ ድምፆች እንደሚሰማና አሁንም ከፍተኛ ስጋት እንዳለ ነው የገለፁት፡፡ ጥቃት አድራሾቹ ጥቃቱን ከፈፀሙ በኋላ ሸሽተው የሚገኙባቸው ቦታዎች ጫጩ፣ ሻር፣ ዶንግዚ፣ የገር አካባቢዎች መሆናቸውን የጠቆሙት የጥቃቱ ሰለባዎች፤ እነዚህ አራት አካባቢዎች የታጣቂዎቹ ዋነኛ መሸሸጊያዎች
እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ “የተደበቁባቸው ቦታዎች በግልፅ ይታወቃል፤ ወጣ ገባውንም በሚገባ እናውቀዋለን” የሚሉት የጥቃቱ ሰለባዎች መንግስት የተሰጠውን መረጃ ይዞ እነዚህን አካላት ካላጠፋ በስተቀር በአካባቢው የመኖር ዋስትና እንደሌላቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በመተከል የተፈፀመውን አሰቃቂ ጥቃት በተመለከተ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ በዞኑ ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ በተፈፀመው ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ ከቡለን ወረዳ 90 ኪ.ሜ በምትርቀው በኩጂ ቀበሌ በብዛት ነዋሪ የሆኑት የሺናሻ፣
የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች መሆናቸውንና ቀበሌዋ የፖሊስ ሃይል እንደሌለት መረዳቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ በአካባቢው በጨለቆና ዶሼ ቀበሌዎች
ቤቶች መቃጠላቸውን፤ በድባጤ ወረዳ ይንበን ቀበሌ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ከታህሳስ 14 ቀን 2013 ጀምሮ ቀያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ጠቁሟል ኮሚሽኑ፡፡ አካባቢውን በቅርበት እንዲጠብቅ የተመደበው የመከላከያ ሰራዊት ታህሳስ 13 ቀን 2013 ለማረጋጋት ተብለው ወደ ቦታው ተልከው የነበሩ አንድ የፌደራልና ሁለት የክልል አመራሮችን ለማጀብ በሚል አካባቢውን ለቅቆ መሄዱን ተከትሎ፣ ጥቃቱ መጀመሩንና ጥቃቱ እስከ እኩለ ቀን አጋማሽ
ድረስ መዝለቁን እንዳረጋገጠ ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡ በዚህ ጥቃትም ከሞቱት መካከል አብዛኛው የሺናሻ ተወላጆች መሆናቸውን ጥቃቱን በዋናነት የፈፀሙትም የአካባቢው ነዋሪዎች መሆናቸውን ኢሰመኮ መረዳቱን አስታውቋል፡፡ ለጥቃቱ ሰለባዎች አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግ ያሳሰበው ኮሚሽኑ፤ መንግስት በአካባቢው የሰዎችን ደህንነት የማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባሩን በትኩረት እንዲወጣ አሳስቧል፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ) በበኩሉ ለችግሩ ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግ የጠየቀ ሲሆን፡፡ በጥቃቱ የደረሰውን ጉዳትም በአግባቡ እንዲመረምርና መንግስት
መሰል ጥቃቶች ከመፈፀማቸው አስቀድሞ እንዲቆጣጠር ኢሠመጉ አሳስቧል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአማራ በሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ
ኢትዮጵያያን ሁሉ የተፈፀመውን የዘር ፍጅት እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በአካባቢው በተደጋጋሚ እየተፈፀመ ያለውን ጥቃት ማስቆም ያልቻለው የፌደራል መንግስቱም ሆነ የክልሉ አስተዳደር በወንጀሉ ተጠያቂ ከመሆን እንደማያመልጡ ያስታወቀው አብን፤ ችግሩ በሰፋ ቁጥር ሀገሪቱን ወደ ማትወጣው ችግር ውስጥ ይከታታል ብሏል፡፡ የሰሞኑን ጥቃት ተከትሎ የፀጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ ባለፈው ረቡዕ 42 ታጣቂዎች መገደላቸውንና በጥቃቱ እጃቸው አለበት የተባሉት ከፍተኛ አመራሮች መታሰራቸው ተገልጿል፡፡

Read 12610 times