Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 11 August 2012 10:17

ሜዳው ላይ እንተያይ!” አትሌት ጥሩዬ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

(ነገር - የገባት ሰጐን)

አንድ የቱርኮች ተረት እንዲህ ይላል፡-

ከእለታት አንድ ቀን የዱር አራዊቶች ተሰብስበው፤

“የዱር የጫካው ገዢ ንጉሳችን አንበሳ ታሟል፡፡ ነብር ደግሞ እኔ ልግዛችሁ እያለ ይፎክራል፡፡ ምን ብናረግ ይሻላል?” የሚል ጥያቄ አነሱ፡፡

አንደኛው - “ለጌታችን እንደቆምን ለማረጋገጥ እንሂድና ጦርነት እንግጠመው!” አለ

ሁለተኛው - “እሱ በጣም አደገኛ አውሬ ስለሆነ ፊት ለፊት ከመግጠም ይልቅ የሱን አይነት ቆዳ ለብሰን ወገኑ መስለን፣ ሳያስበው እናጥቃው!”

ሦስተኛው - “የለም ወደ ጦርነት ከመግባታችን በፊት አርፎ እንዲቀመጥ እናስጠንቅቀው”

ጦጢት - “ይሄ ሁሉ እንዲፈፀም እኮ ንጉሳችን አያ አንበሶ ምን እንደሚሉ አላወቅንም፡፡ መጀመሪያ እሳቸውን ብንጠይቃቸው አይሻልም ወይ?” አለች፡፡

ሁሉም “ይሻላል!” “ይሻላል!” አሉና በጦጣ ሀሳብ ተስማሙ፡፡

ወደ አንበሳ ቤት ሄዱ፡፡

የሚያስገርም ነገር አዩ፡፡

አንበሳና ነብር አብረው ተቀምጠው የጦፈ ወሬ ይዘዋል፡፡

የዱር አራዊቱ ሁሉ ኩም አሉ! አንዳንዶቹ “ምን እያወሩ ይሆን?” አሉ፡፡ አንዳንዶቹ “በማያገባን ገብተን ነው” አሉ፡፡ አንዳንዶቹ “ዙፋኑን ሊያወርሰው ይሆን?” አሉ፡፡

ጦጢት “ጐበዝ! በሁሉም መንገድ ቀልጠናል!” አለች፡፡

*  *  *

የምናስባቸውንም የምንጠረጥራቸውንም ጉዳዮች ሁሉ አስቀድመን በተግባር እናረጋግጥ፡፡ በማናቸውም መልኩ በወሬ አንፈታ! ከመፎከርም ከማውራትም በተግባር ምን እናድርግ? (What is to be done? እንዳለው ሰውየው) ማለት ተመራጭ ነው!!

ከአትሌቶቻችን እንማር!

ቃልን ማክበር ኃላፊነትን መወጣት ነው፡፡ አትሌቶቻችን ያሳዩን ይሄንን ነው፡፡ “የብዙ ሰው አደራ አለብኝ!” የኃላፊነት ስሜት ነው፡፡ “የሰራ ሰው ያሸንፋል” በቆራጥነት ዳር የመድረስ መንፈስ ነው! “ተወዳዳሪዎቻችንን ወጥሬ አደነዝዛቸዋለሁ” የብልህ ጀግንነት አርአያ ነው፡፡ የመቧደንን ጥበብ በማያሻማ መስዋእትነት ያሳየችን አትሌት ወርቅነሽ ናት፡፡ ጊዜ ጠብቆ ማሸነፍን አትሌት ጥሩዬ በሚገባ አረጋግጣልናለች፡፡ ጥርስን ነክሶ ዳር መድረስን ለመረዳት እንችል ዘንድ ቲኬ ገላና እስከመጨረሻ እስትንፋስ ሮጣ በድል አሽራናለች! መንገዳችን ይሄው ነው!

አንድ የድሬዳዋ ገበሬ፤

“በዚህ ዘመን፣ መጀመሪያ ዘርዛራ ወንፊት ይሰጡሃል፡፡ ቀጥለው ጠቅጣቃ ወንፊት ያቀርቡልሃል! በሦስተኛው ምንም መሹለኪያ የሌለው ወንፊት ላይ ያስቀምጡሃል!” ይላል፡፡ ጉዳዩ ተጠንቀቅ፣ እወቅበት ነው!!

መረጃ መስጠት እንዳለ ሁሉ አሳሳች መረጃ መስጠትም አለ፤ ይላሉ ፈረንጆች (As there is information, there is disinformation እንደማለት) አስቦ መጓዝ ይሄኔ ነው!

“ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው!” ይላል ያገራችን ሰው፡፡ በሁሉም ወገን የወሬ ናዳ አለ፡፡ ያ ወሬ እውነትም ይሁን ውሸት ህዝቡን ይፈታዋል፡፡ በመናገር ነፃነት ሳቢያ ወደንም፣ በግድም የወሬ ትውልድ ፈጥረናል፡፡ ከዚህ እነዲገላግለን መፀለይ አለብን፡፡ በታሪክም በአፈ-ታሪክም ብዙ ሲባል ሰምተናል፡፡ በ”አሉ”ና በ”ይባላል” ብዙ ብለናል፡፡ ለምሳሌ፡-

“ጠላት በመጣ ጊዜ ጨጨሆ መድሃኒዓለምን የጠበቁት ዝንጀሮዎች ነበሩ” ይባላል - ይባላል ነው መቼስ!

“በነብር የሚጠበቅ ገዳም ጐንደር አለ ይባላል” - ይባላል ነው መቼስ!

“በዘንዶ የሚጠበቅ ገዳም ደግሞ ትግራይ አለ” ይባላል፡፡ - ይሄም ይባላል ነው!

“የገዳም ጠባቂ ውሻ ጆዬ ይባላል” አሉ፡፡ ነገሩ ሊሆን ቢችል እንኳ እንደ ምዕራባውያኑ ወይ ፊልም አልሰራንበት ወይ መፅሐፍ አልፃፍንበት ስናወራው ኖረን ስናወራው እንሞታለን፡፡

አሁን ደግሞ እድሜ ለቴክኖሎጂ ኢንተርኔት ተጨመረልን፡፡ የማይወራ ወሬ፣ የማይሰደብ ስድብ፣ የማይቀርብ ሃሳብ የለም፡፡ ችግሩ ግን ወሬ የትም አያደርሰንም፡፡ እፎይ ያሰኘናል - ከምን? ከትግል! በወሬ ወጣልና! ልክ ልካቸውን ነገራቸው! ብለን ለጥ ብለን እንተኛለና! ይሄ አንድ እርግማን ነው! በወሬ መፈታት ማለት ይሄ ነው!

ደጋግመን በመሳደብ፣ ደጋግመን በማማት ምንም አላፈራን! መሬት ላይ ያለው ችግር አሁንም መሬት ላይ ነው፡፡ “አለ ደሀ ዘውድ አለገበሬ ማድ” ዛሬም ዕውን ተረት ነው፡፡ ደጋግመን ብናወራ፤ ደጋግመን ብንቋሰል፤ ደጋግመን እዬዬ ብንል ለሀገራችን ጠብ የሚል ነገር የለም! ብንገማገም፣ ስብሰባ ብናበዛ ለሀገራችን ጠብ የሚል ነገር የለም! የሚያስፈልገን ልብ ነው! የሚያስፈልገን ቆራጥነት ነው! በቆራጥነት ጉዳያችንን መወያየትና ልባም መፍትሄ መስጠት ነው፡፡ “በላብ ያልፍልሃል! ተሸፋፍነህ ተኛ!” እንደሚባለው ያበሻ መድሃኒት ላቦት ብቻ መፍትሄ አይሆነንም! አውርተን አውርተን እፎይ ብሎ መተኛት ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም መፍትሄ አይሆነንም! በሁሉም መስክ ነገር - እንደገባት ሰጐን እንደ አትሌት ጥሩዬ “እሜዳው ላይ እንተያይ!” ማለት እንጂ በወሬ መፈታት የለብንም!

ተግባር እንጂ የወሬ ነፋስ የትም፣ መቼም አይበጀንም፡፡ ኦቴሎ በፀጋዬ ገ/መድህን ብዕር እንዲህ ይለናል፡-

“…የሆነውን ሁሉ አይተን

ነበርን ማለት ከንቱ ነው፣ ተውነው መጀነኑ በቅቶን

ጉራ መንዛት፣ መዘባነን፤ የሚያዛልቅ ዘዴ ባይሆን!”

እሜዳው ላይ እንተያይ!!

 

 

 

Read 4012 times Last modified on Saturday, 11 August 2012 10:46

Latest from