Saturday, 19 December 2020 09:51

‘አሸወይና’ ሲሆን... ሁሉም እስክስታ ወራጅ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

  "እኔ የምለው.... ሰዋችን ምን እየሆነ ነው! ሀሳባችን በሙሉ ወደ ሌላ ሄደና ነው እንዴ! ሀላፊነት ይሰማዋል የምትሉት ሁሉ እኮ የአፍና
አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጉን እየተወ ነው፡፡ “ወረርሽኙ እየባሰበት ነው፣” “ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፣” ምናምን እየተባለ በየመንገዱ የምናየው ግዴለሽነት ብቻ ሳይሆን ለሌላው ደህንነት ደንታ ቢስ መሆን አሳሳቢ ብቻ አይደለም፣ አሳፋሪም ነው፡፡"
   
               እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በቀደም አንድ ወዳጃችን ስለሆነ መስሪያ ቤት ሲያወራን ነበር፡፡ እና የሚያወራለት መሥሪያ ቤት በአንድ ሺ አንድ ችግሮች የተተበተበ ነው፡፡ እናላችሁ... ወዳጃችን መሥሪያ ቤቱ በጥቂት ዓመታት ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ እንደሚሆነ ሲነግረን የቀረን ነገር ቢኖር፣ የጨው ዓምድ የሚሉት ነገር መሆን ብቻ ነበር፡፡ ከዚህ በአለፍ አገደም የምንጠቅሳት ነገር አለች... ይህች ከአፍሪካ፣ ከምስራቅ አፍሪካ ምናምነኛ አናደርጋታለን፣” የሚሏት ‘ፌይሪ ቴል’ ነገር፡፡
እናማ.... አሁን ማን ይሙት የአንዲት ሚጢጢዬ ከተማ ህዝብን ፍላጎት አይደለም ማሟላት በጥቂቱ እንኳዋን መነካካት ሳይቻል “በምናምን ዓመት ውስጥ ከምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ ለመሆን እንሠራለን...” ብሎ ነገር ምን የሚሉት ትንቢት ነው! (‘እቅድ’ ለማለት ‘አፍ ስለሚይዝ’ ነው፡፡)   ‘ኬሚስትሪው’ ልክ አይመጣማ! የራስን ጓዳ መልክ ሳያሲዙ ምስራቅ አፍሪካ፣ አፍሪካ ላይ ዘሎ ጉብ ማለት...አለ አይደል...እንደው ትንኮሳ ካልሆነ በቀር አይዋጥልንማ! ዘንድሮ እንደሁ እንኳን ሰበብ ተግኝቶ መቀመጫ የሚያሳጣ መአት ነው!
“ሄሎ ስማ፣ ቅዳሜ ቢራችንን ራሳችን የቢራ ጠርሙስ እስክንመስል ነው የምንጠጣው። ታውቃለህ ከአንተ ጋር የምንጨዋወተው ምን ያህል እንደሚያስደስተኝ ታውቃለህ፡፡ ደግሞ ቢራ ከጋበዝከኝ ስንት ጊዜ እንደሆነህ አትርሳ! (አምስት ቀን አልሞላውም እኮ! ሰባቱን ጠርሙስ ገልብጦ ስምንተኛው ላይ የማያውቀውን፣ ወይም ሲሉ የሰማውን ‘መቦትለክ’ ሲጀምር አይደል እንዴ አባብላችሁ ያስወጣችሁት! ‘ቦትልኮ’ ወይ ከአርሴ፣ ወይ ከማንቼ ሊያስፈርጃችሁ!)
እናማ... ይሄ የሚሆነው ሁሉም ነገር ደህና (‘አሸወይና’ ማለትም ይቻላል) በሆነበት ጊዜ ነው፡፡
“አንተ! እማዬ ትሙት፣ አሁንስ በየቀኑ ሳይሆን በየሰዓቱ ትናፍቀኝ ጀምረሀል፡፡ (ይሄ እኮ መደባበስ አይደለም፣ ስስ ምናምኖችን መነካካት አይደለም...ምን አለፋችሁ፣ ጊዜን አሳደው መያዝ ባቃታቸው የጥንት አራዶች ቋንቋ ‘በጠረባ መምታት’ ነው! (ለነገሩ እነኚህ ኮሌስትሮል፣ ‘ምናምንሮል’ የሚሏቸው ነገሮች ተጠራርተው ከከተሙ በኋላ ምኑን ተሮጠ! ደግሞ በዓመት አንዴ እንኳን መናፈቅ የሚሊዮን ዶላር እጣ በሆነበት፣ እሱዬው በእሷዬዋ ‘ጠረባ’ ዘጭ ካለለ፣ ወይ የመረዳት ችግር አለበት፣ ወይም ‘ሊያመልጠው የሚችለውን’ ነገሬ አላለም! ቂ...ቂ...ቂ...!) ጓደኞቼ ምን እንደሚሉኝ ታውቃለህ... ‘የሆነ ነገር ቢያስነካሽ እንጂ በአሁኑ ዘመን ማንም ሴት ቦይ ፍሬንዷን ያንቺን ያህል አትወድም! በእማዬ ሞት ደስ አይልም! (ኸረ እባክሽ እዘኚለት! ‘በጠረባ’ ካጋደምሽው በኋላ ኦክሲጅን ማሳጣት ምን የሚሉት ላቭ ነው!) ደግሞ እሁድ እንትና ክትፎ ቤት ምሳ ትጋብዘኛለህ፡፡ (እሰይ! “እሰይ እሰይ እግዜር ይስጥሽ!” አለ ሰውዬው!)
እናማ... ይሄ የሚሆነው ሁሉም ነገር ደህና (‘አሸወይና’ ማለትም ይቻላል) በሆነበት ጊዜ ነው፡፡
“አጅሬው፣ እባክህ ቤት ውስጥ ችግር ገጥሞኝ፣ ቤተሰቡ በጠቅላላ ተደብሯል። (በጠቅላላ! እሱና እሷ ብቻ ናቸው እኮ ቤት ውስጥ ያሉት! የተደወለለት ‘በጠቅላላ’ የሚለው ከስንት ቁጥር ጀምሮ ስንት ላይ እንደሚያርፍ ለማወቅ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ፍለጋ ይገባል፡፡) የማደርገው ነገር ግራ ቢገባኝ ነው የማስቸግርህ፡፡ በሳምንት የምመልስልህ አንድ አምስት ሺህ ብር ብታበድረኝ ብዬ ነው!  (ምን! አምስት ሺህ! እና እኮ ለመጨረሻ ጊዜ አምስት ሺህ የምትባል ነገር በእጃችሁ የነካችሁት የዛሬ ምናምን ዓመት ‘ከአማሪካን’ የተላከችውን ትንሽዬ ‘ዶላሬ ያጠቆራችሁ’ ጊዜ ነው! ደግሞ አምስት ሺህ ይላል! ካቻምና ለገና በዓል “እንደው ቤት ማሟሟቂያ...” ብሎ የተበደረውን ሰባት መቶ ሀምሳ ብር አልከፍል ብሎ ከአብሮ አደጉ ጋር ተቆራርጧል እኮ! ልክ እኮ አምስት ሺህ ብር ወድቃ የምትገኝ አስመሰላት! በእርግጥ ‘ወድቃ የምናገኛት’ የለንም ማለት አይደለም፡፡)
እናማ... ይሄ የሚሆነው ሁሉም ነገር ደህና (‘አሸወይና’ ማለትም ይቻላል) በሆነበት ጊዜ ነው፡፡
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ወዳጅና ጠላት የሚለየው በደጉ ጊዜ ሁሉም በሽ፣ በሽ በሆነበት ጊዜ ሳይሆን ክፉ ቀን የምትባለው የመጣች እለት ነው፡፡ በ‘ደህናው’ ጊዜማ ምን ችግር አለ!
“አንተ ምንድነው ኮሶ የምትጠጣ ይመስል ግንባርህን የምትቋጥረው! ጥሬ ስጋ ነው እንጂ ጥይት መሰለህ እንዴ!”
“ስማ አኔ እኮ ያደግሁት ቦክሰኛ ኬክ እየበላሁ ነው፡፡ እንዳንተ ጥርስ ማብቀል ሳልጀምር ኮቾሮ የለመድኩ መሰለህ!” (ይሳሳቃሉ)
“ስሙ፤ መዋጯችን ያነሰች አይመስላችሁም! አንድ ኪሎ እኮ ለሦስት እየተበላች ምኑን ሆድ ጠብ ትላላች!”
“አንተ የራስህን ብቻ ሳይሆን የሚስትና የልጅህን ሆድ ይዘህ ስለምትመጣ ነዋ!” (ይሳሳቃሉ)
እናማ... ይሄ የሚሆነው ሁሉም ነገር ደህና (‘አሸወይና’ ማለትም ይቻላል) በሆነበት ጊዜ ነው፡፡
ታዲያላችሁ...የሆነ ጊዜ ቀን ትጠማለች። ሽንኩርቷም ትወደድና፣ ቲማቲሟ የቪ.አይ.ፒ. ነገር ትሆንና፣ ቢራው የማከፋፈያዎቹ መኪኖች በአጠገብ ሲያልፉ፣ በ“እኛማ አንድ ሰሞን እንጠጣህ ነበር!” አይነት የሚታይ ይሆንና ቀን ታጋድላለች፡፡ ኪስም ‘አፍራሽ ግብረ ሀይሎች’ ይዘምቱበታል፤ ጸጥ! ጭጭ! ኮሽታ አንኳን የለም!
በየሁለት ቀን ይደውል የነበረው ‘ጓደኛ’ ምነው ከአስራ አምስት ቀን በላይ ድምጹ ጠፋ! ‘በደህናውማ እንዲህ አይጠፋም!’ እና ይደወላል፡፡ ይጠራል፣ ይጠራል፣ አይነሳም። ‘አይ በደህናውማ ሊሆን አይችልም!’ ሶስት ቀን፣ አምስት ቀን፣ ሳምንት! ሌላ ጓደኛ ዘንድ ይደወላል፡፡
“ስማ፣ እንትናን ሳምንት ሙሉ ብደውል አጣሁት፡፡ ስልኩ ይጠራል ግን አይነሳም። የሠማኸው ነገር አለ? ችግር ገጥሞት ይሆን እንዴ?”
“የምን ችግር ነው የምታወራው!”
“ይህን ያህል ጠፍቶ አያውቅማ! አጠያይቄ ቤቱ ልሂድ እንዴ!””
“ምን ነክቶሀል! ቅድም አብረን ነው የጀበና ቡና የጠጣነው!”
ታዲያ አንድ ቀን ክው፣ ክው ሲባል መንገድ ላይ ፊት ለፊት ግጥም!
“አንተ ምን ሆነህ ነው ይህን ያህል የጠፋኸው? ስንት ጊዜ ነው እኮ የደወልኩልህ!
“ኦ!...” (‘ኦ!’ አባባሉ መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣ ይመስላል፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...) ያኔ ከተገናኘን በኋላ ፊልድ ወጥቼ አዲስ አበባ አልነበርኩም፡፡ ትናንት ማታ ነው የገባሁት!
‘እርፍ!’ ይሏችኋል እንዲህ ነው፡፡ ያ ጨዋታችሁ ሁሉ ያስደስተው የነበረ ወዳጅ፣ ፈረንጅ እንደሚለው፣ አውጥቶ ለተኩላዎቹ ይወረውራችኋል፡፡ “ለምን!” “ምን ጉድ መጣ! “ስምንተኛው፣ ምናምነኛው ሺህ!” ማለት አያስፈልግም፡፡ ‘የፈተናው ወረቀት ሳይሰረቅ’ መልሱ ቀድሞ ይታወቃል! (‘የፈተናው ወረቀት ሳይሰረቅ’ መልሱን የሚያውቁ ‘ብጹአን’ ባይሆኑም እድለኞች ናቸው፡፡) እናላችሁ፣  እሱ ራሱ የቢራውን ጠርሙስ እስኪመስል የመጋበዝ አቅማችሁ፣ ከዜሮ በታች ስለወረደ የመጠቀሚያ ጊዜያችሁ አልፎባችኋል፡፡
ከ‘ሉካንዳ ቡድን’ አንዱ ወደ ሌላኛው ይደውላል፡፡
“ሃሎ!”
“ሀሎ ማን ልበል?”
“ጭራሽ! ማን ልበል መባባል ጀመርን!”
“አቦ አትጨቅጭቀኝ!
“እንዴ! አንተ ዛሬ ምን ነክቶሃል!”
“ምን ነካኝ አልኩህ?”
“የእኔ ጌታ፣ በል ደህና ሁን፡፡ እኔ ቢያንስ እየተገናኘን ሻይ እንጠጣ ለማለት ነበር የደወልኩት፡፡”
“ብንገናኝ ምን ያደርጋል! እናንተ ሰው ያለማማት ምን ታውቁና ነው!”
ይሄን እኮ የሚለው ዋነኛው የቡድኑ ‘ዘጋቢ’ ነው! ምን ያድርግ...እንኳን ለጥሬ ሥጋ ሊያዋጣ ልጆቹን ከግል ትምህርት ቤት ወደ መንግሥት ት/ቤት ለማዘዋወር መከራውን እያየ “ሻይ” ቅብጥርስዮ ይለዋል እንዴ!
እኔ የምለው.... ሰዋችን ምን እየሆነ ነው! ሀሳባችን በሙሉ ወደ ሌላ ሄደና ነው እንዴ! ሀላፊነት ይሰማዋል የምትሉት ሁሉ እኮ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጉን እየተወ ነው፡፡ “ወረርሽኙ እየባሰበት ነው፣” “ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፣”  ምናምን እየተባለ በየመንገዱ የምናየው ግዴለሽነት ብቻ ሳይሆን ለሌላው ደህንነት ደንታ ቢስነት አሳሳቢ ብቻ አይደለም፣ አሳፋሪም ነው። ደግሞላችሁ... አሁን፣ አሁን በርከት ብሎ የምናየው “ሰዉ እንዴት ነው የሚያስበው?” የሚያሰኘው ነገር ምን መሰላችሁ...ፌስማስኩን ማንጠልጠያ ክሮቹን ጣቱ ላይ አድርጎ እያሽከረከረ የሚሄድ መአት ሰው አለላችሁ፡፡ እኔ የምላው....አሁን ፌስማስኩን ክንዱ አደርጎ የሚሄድ ሰው ምን ትሉታላችሁ! እና ክንድ አካባቢ ያለውን አቧራ ቅሞ እንደገና ወደ አፍ!
ነገሬ ብላችሁ እንደሆነ እርቀትን መጠበቅ የሚሉትን ነገርማ ተዉት፡፡ መጀመሪያውኑም እንዲህ ያለ ነገር ያልነበረ ነው የሚመስለው። ብዙ ቦታዎች በር ላይ ያሉትን የውሀ እቃዎች ወይ አንስተዋቸዋል ወይ ደግሞ ረስተዋቸዋል። በር ላይ “ሳይታጠቡ መግባት ክልክል ነው፣” ይሉ የነበሩ የጥበቃ ሠራተኞች ተሰላቹ መሰለኝ! ትንሹም፣ ትልቁም ባለማወቅ ሳይሆን እያወቀ እንዲህ ሲሆን እሱ ይጠብቀን እንጂ ሌላ ምን ማለት ይቻላል!
እናላችሁ...ሁሉም ነገር ‘አሸወይና’ በሆነ ጊዜ የምናሳየው ባህሪ ምናልባትም እውነተኛው ባህሪያችን ላይሆን ይችላል ለማለት ያህል ነው። ‘አሸወይና’ ሲሆንማ ሁሉም እስክስታ ወራጅ ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1229 times