Sunday, 13 December 2020 00:00

አደገኛው የማህበራዊ ሚዲያ የውሸት አለም!

Written by  በአብይ ሰለሞን
Rate this item
(2 votes)

 "ይህ ቴክኖሎጂያዊ እመርታ የሰው ልጅ ህልውና ላይ የፈጠረው አደጋ፣ ራሱ ቴክኖሎጂው የፈጠረው ሳይሆን ቴክኖሎጂው ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ክፉ አውሬ አደባባይ የማውጣት ችሎታው ነው። ማህበረሰብ ውስጥ ያለው ክፉ አውሬ ደግሞ የሰው ልጅ ህልውና ላይ አይነተኛ አደጋ ይሆናል።"
              
           የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ እ.ኤ.አ ከ1980ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ እስከ አሁን ባደረገው የሶስት አስርት አመታት የእድገት ጉዞ፣ ከፈጠራቸው አገልግሎቶች  የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎትን ያህል ከፍተኛ አለም አቀፋዊ ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ ነገር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ነገር ግን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር አገልግሎት በደረሰበት ወቅታዊ የእድገት ደረጃና አቅም ያዳበረው ወደር የሌለው አለም አቀፋዊ የተፅዕኖ ፈጣሪነት ጡንቻ ወደ አደገኛና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መድረሱና ትኩረት እንደሚገባው የዘርፉ ከፍተኛ ሊቃውንት በማሳሰብ ላይ ይገኛሉ።
የዚህ ፅሁፍ መነሻም ከወራት በፊት በወጣውና እንደ Google, Gmail, Facebook, Instagram, Twitter ድርጅቶች ውስጥ በከፍተኛ አመራርና ሳይቲስትነት ያገለገሉ ባለሙያዎች የተሳተፉበትና የማህበራዊ ሚዲያ የእድገት ጉዞና እየፈጠረ ያለው አለም አቀፋዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል የሚል አመለካከት የሚያንፀባርቁበት The Social Dilemma ጥናታዊ ፊልም ነው። በፊልሙ ውስጥ የሚነሱትን ኃሳቦች በመንተራስም በሀገራችን የማህበራዊ ሚዲያም ሆነ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ዘንድ ሊታወቁ ይገባሉ ተብለው የሚታሰቡ እጅግ ጠቃሚ አንኳር ጉዳዮችን ፅሁፉ ለማብራራት ይሞክራል።
ከራስህ በላይ ያውቁሃል
በአለማችን ታሪክ በከፍተኛ ፍጥነት በጥቂት አመታት ውስጥ በትሪሊየን ዶላሮች የሚገመት ኃብት ማጋበስና ኃያል ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን የቻሉ ድርጅቶች ቢኖሩ ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ የማህበራዊ ሚዲያ ድርጅቶች ናቸው። እዚህ የሀብት ደረጃ ላይ በዋነኝነት የደረሱትም የተጠቃሚዎችን የእለት ተእለት የማይቋረጥ ትኩረት በመጠቀም ብቻ መሆኑ ደግሞ አስገራሚ ያደርገዋል። የነዚህ ድርጅቶች የትርፋማነታቸው መሰረት ሰዎች ወይም ተጠቃሚዎች በስልክና ኮምፒዩተሮቻቸው ላይ ትኩረት አድርገው እንዲቆዩ ማድረግ ነው። ምክንያቱም የማህበራዊ ሚዲያዎቹ የንግድ ደንበኞች ገፆቹን ተጠቅመው ማስታወቂያቸውን የሚያስተላልፉ ድርጅቶች እንደመሆናቸው ማስታወቂያዎቹ ውጤታማ የሚሆኑት ስክሪኖቻቸው ላይ ተተክለው በሚጠብቁ ሰዎች ተመልካችነት ነውና።
እንግዲህ የማህበራዊ ሚዲያዎቹ ደንበኞች ማስታወቂያ የሚያስተላልፉ ድርጅቶች ከሆኑ፣ ነጋዴዎቹ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያዎቹ ናቸው ካልን፣ የሚሸጠው (ለገበያ የሚቀርበው) ምርት ምንድነው ብለን መጠየቃችን አይቀርም። ገበያ ላይ የቀረበን ምርት ለመጠቀም ገንዘብ የማንከፍልበት ከሆነና ተጠቃሚ ተብለን የምንጠራ ከሆነ ለምንጠቀመው ነገር የሚከፍል አካል አለ ማለት ነው። ይህም ማለት በዚህ የንግድ አለም ምርቱን የሚያቀርበው ሻጭ ማህበራዊ ሚድያዎቹ፣ ገዢው ደንበኛ ደግሞ ማስታወቂያቸውን በማህበራዊ ሚድያዎቹ የሚያስተላልፉት ድርጅቶች ሲሆኑ ገበያ ላይ ለሽያጭ የሚቀርበው ምርት ደግሞ፦ እኛ ነን!
የእኛ ትኩረትና ጊዜ ነው የማህበራዊ ሚድያዎቹ ምርትና ለገበያ የሚቀርብ አንጡራ ኃብት። እኛ በስክሪኖቻችን ላይ የበለጠ ጊዜያችንን አጠፋን ማለት የሚተላለፈው ማስታወቂያ ብዙ ሰዎች ተመለከቱት፣ ውጤታማ ሆነ ማለት ነው። የማህበራዊ ሚድያዎቹም የበለጠ ትርፋማ ሆኑ ማለት ነው። እናም ትርፋማነታቸውን ጠብቀው ለመቆየት እኛ በገፆቻቸው ላይ ረጅም ጊዜ እንደምናሳልፍ ማረጋገጥ አለባቸው። የምንሸጠው እኛ ነንና! ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ልዩ ዘዴ አላቸው። በዚህም መሰረት እንደ Google, Facebook, Twitter, Instagram, YouTube, Snapchat, TikTok ያሉት ታላላቆቹ የማህበራዊ ሚድያ ፊታውራሪዎች የኛን ትኩረት ቀድመው ለማግኘት ይወዳደራሉ፤ አዳዲስ ውጤታማ ዘዴዎችን ይቀምራሉ።
የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች የበለጠ ጊዜያቸውን ገፆቹ ላይ እንዲያሳልፉና ትኩረት እንዲያደርጉ የሚወዱትንና የሚፈልጉትን ነገሮች ማቅረብ ያስፈልጋል። የሚወዱትን ነገር ለማወቅ ደግሞ ሰዎቹን ማወቅ ያስፈልጋል። ለዚህም በየሰከንዱ፣ በየሰአቱ፣ በየቀኑ እነዚህ ማህበራዊ ሚድያዎች ላይ የምናስገባው የግል መረጃና ዳታ ቀስ በቀስ ተጠራቅሞና ተሰልቶ ከተለያዩ ነገሮች አንፃር የእኛን ፍላጎት ፍንትው አድርጎ ያሳያቸዋል። ምን አይነት ምግብ፣ ልብስ፣ መኪና፣ ቦታ፣ ፍቅረኛ፣ እንደምንወድ፤ መቼ ደስ እንደሚለን፣ ብቻችንን እንደምንሆን፣ እንደሚደብረን፣ ወዘተ. . . በሚገባ ያውቃሉ። ጓደኞቻችንና ወላጆቻችን እንኳን በማያውቁን መልኩ አብጠርጥረው ያውቁናል። ከዚያም እንደየ ፍላጎቶቻችንና ዝንባሌያችን የምንፈልገውና የምንወደው መረጃ ወደ የግል ገፆቻችን መጉረፍ ይጀምራል። እኛም ከማህበራዊ ሚድያዎቹ ጋር ያለንን ወዳጅነት እያጠበቅን እንሄዳለን። በቀላሉ መማረክና ቁጥጥር ስር መውደቅ ይሉሃል ይሄ ነው።
ይህንን ስርአትና ሲስተም ባለሙያዎቹ Surveillance Capitalism በማለት ይጠሩታል። የሰዎችን የግል መረጃ በመሰለልና በማነፍነፍ ላይ ስኬታማነቱ የተመሰረተ የንግድ ስርአት ነው። ይህ ስርአት የሰዎችን መረጃ ቀስ በቀስ በማጠራቀም ፍላጎታቸውንና ማንነታቸውን እንዲሁም ስነ ልቦናቸውን በመረዳት እነርሱን የሚማርክ መረጃ ሳያቋርጥ የሚያቀርብ ቴክኖሎጂ መፍጠርን አላማው ያደረገ ነው። በዚህ መንገድ ከእኛ የሚወሰደው የእለት ተእለት የግል መረጃና ዳታ እየተጠራቀመና የበለጠ እየተሻሻለ ቀጥሎ ሊፈጠር የሚችለውን ነገር የመተንበይና የማወቅ አቅም ላይ መድረስ ችሏል። ማህበራዊ ሚድያዎቹ የሚያቀርቡልን እነዚህ እንደየ ፍላጎቶቻችን የተሰፉ መረጃዎች ቀስ በቀስ ፍፁም ሳናውቀውና ሳናስተውለው ባህሪያችንን የመለወጥ ጉልበት አዳብረዋል። ሳናስተውለው ቀስ በቀስ እነርሱ ወደሚፈልጉት ውጤት እንድናመራ ፕሮግራም እየተደረግን ነው።
በየማህበራዊ ሚድያ ገፆች ያደረግናቸው ነገሮች፤ የተጫንናቸው ክሊኮች፣ የተመለከትናቸው ቪድዮዎች፣ የሰጠናቸው like እና አስተያየቶች ተጠራቅመው እኛን የበለጠ ወደየሚማርክና ወደሚመስጥ የፕሮግራም ሞዴልነት ይቀየራሉ። አንዴ ይህ ሞዴል ከተገነባ ያ ሰው በቀጣይነት ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ተግባራት በሙሉ ቀድሞ የማወቅና የመተንበይ ችሎታ ይኖረዋል። ከማህበራዊ ሚድያዎቹ ገፆች ጀርባ የሚሰራው የኮድ ቀመር (algorithm) ከኛ የሚያገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ፣ በያንዳንዳችን ገፅ ላይ ሊያሳየን የሚገባውን መረጃዎች በማዘጋጀትና በማቀናበር እንደ አውቶማቲክ ሞተር ተግባሩን ሳያሰልስ ያከውናል። ይህንንም ተከትሎ ማህበራዊ ሚድያዎቹ እኛ ገፆቻቸው ላይ የመቆየት ልምዳችን እያደገ ስለመሆኑ፣ ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች እንደምንጋብዝላቸው እንዲሁም ማስታወቂያቸውን በገፆቻቸው ላይ ከሚያስተላልፉ ድርጅቶች የሚያገኙት ገቢ እንደሚያድግ ያረጋግጣሉ።
ስመ ጥሩው የሳይንስ ልብወለድ ደራሲ አርተር ሲ ክላርክ፤ “በከፍተኛ ሁኔታ ልቀት ላይ የደረሰ ቴክኖሎጂን ከአስማት መለየት ይከብዳል” ይላል። አንድ የአስማት ትዕይንት ባለሙያ የሚያውቀው አንድ ልዩ ነገር ቢኖር፣ ሰዎች የተወሰነ የአዕምሯቸው ክፍል ስላለው ባህሪና ተፈጥሮ መረጃውና ግንዛቤው እንደሌላቸው ነው። ይህን አለማወቃችንን በመጠቀም ነው እሱ በአይናችን ልንለየው የማንችለውን የአስማት ጥበቡን የሚያሳየን። ቴክኖሎጂም በተመሳሳይ ሁኔታ ይህንን ነው የሚያደርገው፤ እኛ ባህሪውን የማናውቀውን የስነ ልቦናችንን ክፍተት በመጠቀም አስማቱን ይሰራብናል። እናም የማህበራዊ ሚድያዎቹ ጠበብት ፍፁም ልናውቀና ልናስተውለው በማንችለው ረቂቅ በሆነ መልኩ ባህሪያችንንና ስብዕናችንን ይለውጡታል። ይህ ሁሉ በዙሪያችን ሲከናወን ግን ፈፅሞ ምልክቱን እንኳን ማየት አንችልም። በአጭሩ የማህበራዊ ሚድያዎቹ ከኛ የሚፈልጉትና የሚጠይቁት፣ “ከህይወትህና ከጊዜህ ምን ያህሉን ለኛ መስጠት ትችላለህ?” የሚለውን ነው።
ረቂቅ ሱስ
ኤድዋርድ ተፍት የተባለ የኮምፒዩተርና ፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሳይበሩን አለም ሱስ ሲገልፀው፣ “ደንበኞቻቸውን ተጠቃሚ ብለው የሚጠሩ ሁለት ኢንዱስትሪዎች ብቻ ናቸው፤ የህገወጥ አደንዛዥ ዕፅ እና የሶፍትዌር ኢንዱስትሪ” ይላል።
በአለማችን የሰው ልጅ ስራውን የሚያከናውንበትና የሚያቀላጥፍበት የተለያዩ መሳሪያዎች (Tools) ተፈጥረዋል። እነዚህ ሰውን አጋዥ የሆኑ መሳሪያዎች ሰው ሊገለገልባቸው እስኪፈልጋቸው ድረስ ባሉበት ተቀምጠው ይጠብቃሉ፤ ስንፈልጋቸው ብቻ ነው የምናነሳቸው። አንድ ግዑዝ ነገር ከኛ የሚፈልገው ነገር ካለ፣ እንድንጠቀምበት ካማለለንና ካግባባን መገልገያ መሳሪያ እንዳልሆነ መረዳት ይኖርብናል። የቴክኖሎጂው አለምም ሰው በሚገለገልባቸው መሳሪያዎች ላይ የተመሰረተ አለም ከመሆን በሱሰኝነትና በማማለል ላይ የተመሰረተ አለም ወደመሆን ተዘጋግሯል። ማህበራዊ ሚድያም ባለበት ተቀምጦ ሰው እስኪገለገልበት የሚጠብቅ ሰውን አጋዥ መሳሪያ እንዳልሆነ መመልከት እንችላለን። ማህበራዊ ሚድያ አደንዛዥ እፅ ነው። የሰው ልጅ ከመሰሎቹ ጋር የመገናኘት፣ የመዛመድና ተግባቦት የመፍጠር ባዮሎጂያዊ/ ተፈጥሯዊ ፍላጎት ያለው ሲሆን ይህ ፍላጎቱ ሲሳካም የደስታ ስሜትን የሚፈጥረው የዶፓሚን ኢንዛይም በአንጎላችን ይመነጫል። በዚህም አብሮነታችንንና ማህበራዊ ግንኙነታችንን እያዳበርን አንድ ላይ በህብረት እንድንኖር፣ ወዳጆች እንድናፈራ እንዲሁም ዘራችንን እያበዛን እንድንቀጥል በሚሊዮን አመታት የዝግመተ ለውጥ ሂደት ተሰርተናል። እናም ማህበራዊ ሚድያን የመሰለ ይህን የሰዎችን አብሮነትና ግንኙነት የሚያበለፅግ መድረክ ሱስ የማስያዝ አቅሙ ከፍተኛ ነው። ከመሰሎቻችን ጋር አብሮነት የመገንባትና የነሱን ተቀባይነት፣ ፍቅርና አድናቆት የማግኘት ፍላጎት እንዲኖረን በዝግመተ ለውጥ ሂደት የተሰራን ቢሆንም፣ አስር ሺህ ሰዎች በየቀኑ ስለኛ ያላቸውን አመለካከት እንድናውቅ፣ በየ 5 ደቂቃው ማህበራዊ ተቀባይነትና አድናቆት ወደኛ እንዲጎርፍ የሚያደርግ ፍላጎትና ግፊት እንዲኖረን የሚያደርግ ተፈጥሮ ግን በውስጣችን አልተቀመጠም።
በፌስቡክ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ደረጃ ላይ ይሰራ የነበረው የኮምፒዩተር ሳይንቲስቱ ቻማዝ ፓሊሃፒትያ የተጠናወተንን ሱስ እንዲህ ያብራራዋል፣ “ህይወታችንን ተጨባጭ ባልሆነ ፍፁማዊ ማንነት ዙሪያ መገንባት እንጀምራለን። ምክንያቱም በየአፍታው ቆይታ የምናገኛቸውን የአድናቆት ምልክቶችን (likes, hearts, thumbs up…) ገጣጥመን በፈንጠዝያ በመልካም እሴትና በእውነት ላይ የተመሰረተ የሚመስል አለም እንፈጥራለን። እውነታው ግን የውሸትና ቶሎ ተሰባሪ ዝነኝነት እንደሆነ አንረዳውም። ያ ለአፍታ የሚቆይ ከንቱ ስሜት ነው። እናም ገና ስሜቱ ሳይገባንና ሳናጣጥመው ወደ ስሜት የለሽ ባዶነት ይመልሰናል። ምክንያቱም፣ “ያን ፈንጠዝያ መልሼ ማጣጣም ስለምፈልግ አሁን ደግሞ ምንድነው ማድረግ ያለብኝ” ወደሚያስብለን የማያቋርጥ ክብ እሽክርክሮሽ ውስጥ ይከተናል። ይህ ሁኔታ በ 2 ቢሊየን ሰዎች ውስጥ የሚፈጥረውን ስሜት ስናስበው አስከፊነቱ ቁልጭ ብሎ ይታየናል።”
እንደ ኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ጥናት መሰረት፣ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ በአስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በሚገኙ አሜሪካውያን ላይ የተከሰተ የድብርትና ጭንቀት በሽታ እንዲሁም ራስን የማጥፋት ዝንባሌ በሶስት እጥፍ ጨምሯል፣ አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ላይ ይገኛል። ጥናቱ እንደሚያሳየው፤ የማህበራዊ ሚድያ ከፍተኛ የተጠቃሚነት ዝንባሌ ያላቸው እነዚህ ወጣቶች በጋራ ከሚያሳዩአቸው ተመሳሳይ ባህርያት ውስጥ ማንኛውንም ችግር/አደጋ መጋፈጥ ያለመፈለግ፣ መንጃ ፍቃድ የሚያወጡት ወጣቶች ቁጥር መቀነስ፣ ፍቅረኛ ለመያዝ አልያም ከተቃራኒ ፆታ ጋር ግንኙነት የመመስረት ፍላጎት ማጣት ሲሆኑ ራሳቸውን ተጨባጭ ባልሆነ ምናባዊ የውበት/ቁንጅና ሚዛን የመለካት ባህሪም ይታይባቸዋል።
በታላላቆቹ የማህበራዊ ሚድያዎች ውስጥ ከፍተኛ አመራር ላይ የነበሩት ልሂቃን በጋራ የሚስማሙበት አንድ ኃሳብ በነዚህ ሚድያዎች አማካኝነት ማንኛውም ችግርና ተግዳሮት፣ ብቸኝነት፣ ፍርሃትና ጥርጣሬ ሲገጥመው ሰላምና መረጋጋት ፍለጋ ወደ ዲጂታሉ አለም የሚሮጥ ትውልድ እየተፈጠረ ነው። ይህም ሰዎች ችግርን የሚፈቱበትን ልዩ የተፈጥሮ ሰብአዊ ችሎታቸውን እያዳከመውና እያጠፋው በመሄድ ላይ ነው።
የተዛባ መረጃና ውሸት የበለጠ ይሸጣሉ
የማህበራዊ ሚድያ የቢዝነስ ሞዴል የተዛባ መረጃን ወደ ትርፍ የመቀየር ስትራቴጂ ያነገበና ለሐሰተኛ መረጃ የሚያዳላ ነው። ውሸት መሸጥን ፈልገውት ሳይሆን ከእውነታው ይልቅ የበለጠ ገንዘብ ስለሚያስገኝ ነው። እውነት አሰልቺ ነውና! (The Truth is Boring!)
የመረጃ መዛባቱ በዋነኝነት የሚከሰተውም የማህበራዊ ሚድያዎቹ ለየተጠቃሚዎቻቸው የሚያቀርቡት መረጃ ከላይ እንደጠቀስነው እንደየተጠቃሚው ፍላጎትና ዝንባሌ የተለያየ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባ የምኖረው እኔና አምስተርዳም የሚኖረው አበበ፤ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ቃል በተመሳሳይ ሁኔታ ጉግል ላይ አስገብተን ብንፈልግ የምናገኛቸው መረጃዎች እንደምንገኝባቸው ጂኦግራፊያዊ ቦታዎች፣ ጉግል ስለ ሁለታችን ፍላጎት በተናጥል በሚያውቃቸው እውነቶችና ሌሎች ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ነው። እናም እኔ ጋ የሚመጡት ውጤቶች ስለ “የኢትዮጵያ ብልፅግና”፣ “የኢኮኖሚ እድገት” ወዘተ የሚናገሩ ቢሆኑ አበበ ጋ የሚመጡት መረጃዎች ደግሞ ስለ “የኢትዮጵያ አሰቃቂ ድርቅ”፣ “ዝቅተኛ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ሽፋን” ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ።
በተመሳሳይ ሁኔታም፤ ፌስቡክ ላይ እያንዳንዳችን በተናጥል የምናያቸው የመረጃ ዜናዎች (News Feeds) ፈፅሞ እንደሚለያዩ ብዙዎቻችን ላናውቅ እንችላለን። አንዳችን የምናየውን ዜና ሌሎችም እያዩት እንዳለ በማሰብ እንሳሳታለን። ፌስቡክ ግን ከያንዳንዳችን የተለያየ ፍላጎት አንፃር በየገፆቻችን የሚልክልንን መረጃዎችን የጋራ ባህርያት መሰረት በማድረግ፣ በተመሳሳይ ፍላጎት ዙሪያ የተሰባሰቡ የተለያየ የተጠቃሚዎች ጎራ ይፈጥራል። ይህም ማስታወቂያቸውን ገፁ ላይ ለሚያስተላልፉት ድርጅቶች ሰፊና አያሌ የተመልካች አማራጭ ያለው ምህዳር ይፈጥርላቸዋል።  
እኛም በገፆቻችን ላይ የምናገኛቸው ሰዎችና የምናየው መረጃ ከፍላጎቶቻችን ጋር በደንብ ሰምሮና ተስማምቶ ስናየው መሸወድ እንጀምራለን። ልክ በአስማት ትዕይንት ባለሙያው እንደምንሸወደው! አስማተኛው በእጁ ከያዛቸው ካርታዎች አንድ የፈለግነውን ካርታ እንድንስብ ሲነግረን፣ የትኛውን ካርታ እንደምንስብ ቀድሞ አዘጋጅቷልና የምንስበው እሱ የፈለገውን ካርታ ነው። ፌስቡክም እንደዚያ ነው የሚሰራው። ፌስቡክ በመንበሩ ተቀምጦ፣ “እነ እከሌን ጓደኞችህ አድርጋቸው፣ እነዚህን ሊንኮች ተጫን፣ ወዘተ. . . ይልሃል፤ ልክ እንደ አስማተኛው። በዚህም መንገድ ፌስቡክ ላይ ያሉት ተጠቃሚዎች በሙሉ የተለያየ የእውቀት፣ የፍላጎትና የአመለካከት ደረጃ ባላቸው ጎራዎች የተከፈሉ እንደሆኑ አብዛኞቻችን አንረዳውም። እናም እያንዳንዱ ጎራ የራሱ እውነት በሚለው ዛቢያ ይሽከረከራል። በሂደትም ባለህበት ጎራ በሚቀነቀነው ኃሳብ ውስጥ ሰጥሞ በመቅረት ቀስ በቀስ የራሴ እውነትና አቋም ብለህ ከያዝከው ነገር መለየት ትጀምራለህ።
የፌስቡክ የኮድ ቀመር (algorithm) የምንፈልጋቸውን ነገሮች በየገፆቻችን የሚያቀርብልን ሊመስለን ይችላል። እውነታው ግን ይህ ቀመር የሚያደርገው ነገር አቅራቢያችን ያለ ልንመሰጥባቸው የምንችልባቸውና እኛን ያለጥርጥር የሚማርኩ ነገሮች አሉበት ብሎ የሚያምነውን ጉድጓድ ነው የሚፈልገው። ጉድጓዱን ካገኘ በኋላ አንድ ጊዜ ብቻ ጉድጓዱ ውስጥ ያለ ቪድዮ እንድንመለከት ያደርጋል። ከዚያም መልሶ መላልሶ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ቪድዮዎች እንድመለከት ይመክረናል፣ ይጋብዘናል። ይህ ቴክኒክ Recommendation Engine ይባላል። በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥነውን ይህን ቪድዮ አንዴ ተመልክተን like, share አደረግን ማለት ተመሳሳይ ሌሎች ቪድዮዎችን እንድንመለከት የሚዥጎደጎደውን ግብዣና ምክር (Recommendation) መገመት ነው።
ታዋቂው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ካይሊ ኧርቪንግ የገጠመው ሁኔታ ለዚህ ሁኔታ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ይህ ስፖርተኛ መሬት ጠፍጣፋ ናት በማለት በ ዩ ቲዩብ ላይ ሲናገር ይሰማል። ይህ ቪድዮም ታዋቂነቱ በመጨመር ተከታዮቹ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰፉና እየተቧደኑም ይመጣሉ። ከጊዜያት በኋላም ኧርቪንግ በሚድያ ቀርቦ፣ “ይቅርታ ተሳስቻለሁ፤ ሌሎችንም ወደተሳሳተ አቅጣጫ መምራት አልፈልግም አለ። ነገር ግን ቀድመው አስተሳሰቡን አምነው የተቀበሉ ፈፅሞ አቋማቸውን ሊቀይሩ አልፈለጉም። በጉዳዩ ዙሪያ አንድ ት/ቤት ውስጥ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ተማሪዎችም፣ “ኧርቪንግን መሬት፟ ክብ ናት የሚሉት አግባብተውት ነው”። ሲሉ ተደምጠዋል።
የ‘መሬት ጠፍጣፋ ናት’ የሴራ ቲዮሪው በማህበራዊ ሚድያው የኮድ  ቀመር (algorithm) በሚሊዮን ጊዜዎች ተደጋግሞ ሌሎች እንዲያዩት ተጋብዟል፣ ተመክሯል። ጥቂት ዝቅተኛ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች ናቸው በሴራው ሊያምኑ የሚችሉት ልንል እንችል ይሆናል። ነገር ግን የኮድ ቀመሩ (algorithm) በየዕለቱ ብቃቱንና ፍጥነቱን እየጨመረ መሬት ጠፍጣፋ እንደሆነች ማሳመን ችሏል። ነገ ደግሞ ሌላ ውሸት እንድናምን ሊያደርግ ይችላል ማለት ነው።
የጎግል የዲዛይን ባለሙያ የነበረውና ማህበራዊ ሚድያው እየፈጠረ ያለው አደጋ አሳሳቢነት ላይ ማህበራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር እየሰራ የሚገኘው ትሪስታን ሃሪስ እንደሚለው፣ “ፌስቡክ በትሪሊየኖች ከሚቆጠሩት የመረጃ ዜናዎች (News Feeds) የትኛው እውነት የትኛው ውሸት እንደሆነ ራሱ አያውቅም። ይህን ስናስብ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለብንና ውይይት እንደሚያስፈልግ ይገባናል። ትኩረት በምናደርግበት የትኛውም ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ እውነቱና ውሸቱን መለየት እስኪያቅተን ድረስ ማህበራዊ ሚድያ በንፋስ ፍጥነት የሚጓዝ አሉባልታን አግዝፎ ያቀርባል”።
የህልውና አደጋ
አሁን ባለው የቴክኖሎጂ እድገት ግስጋሴ በቀጣይነት የምንጠብቀው ቴክኖሎጂው ከሰው ልጆች ጥንካሬና አስተሳሰብ በላይ በመሆን ሰዎች የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ማሽኖች ሊተኩ የሚችሉበትን ጊዜ ነው። ይህ ቢሆንም ቅሉ፣ ቴክኖሎጂው እዚህ ጥንካሬያችንን የሚበልጥበት ጊዜ ላይ ገና ሳይደርስ ድክመታችንን በልጦ እየተቆጣጠረን ይገኛል። ቴክኖሎጂው የድክመታችንን ቀይ መስመር የሚሻገረውም ሱሰኝነት፣ ወገንተኝነት፣ ፅንፈኝነት፣ ቁጣና ትዕቢት ስር ያለውን ክፉ ኃይል በመቀስቀስ ነው። ይህም ለሰው ልጅ ኃያል ጉልበት በመስጠት ህልውናችን ፊት የተጋረጠ ከባድ እርግማን ሆኗል። ስመ ጥሩ የግሪክ ደራሲ ሶፎክልስ ሲናገር፣ “እንደ እርግማን የሟቾች ህይወት ውስጥ ገብቶ በሰፊው የሚሰራጭ ነገር የለም” ይላል።
ከባድ ነገር ሲገጥመን ዘወትር እንደምንለው ቀድሞ እንዳለፉት ከባድ ነገሮች ‘ይህንንም እንለምደዋለን፤ ከቴክኖሎጂው ጋር እንዴት መኖር እንዳለብን መላ መፈለጋችን አይቀርም’ እንል ይሆናል። ቢሆንም መዘንጋት የሌለብን ነገር ቢኖር፣ ይህ የተጋረጠብን አደጋ እየተመራ ያለው የብርሃን ፍጥነት እያደገ በመሄድ ላይ ባለ ቴክኖሎጂ መሆኑን ነው። በግርድፉ ብናስበው እ.ኤ.አ ከ1960 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የኮምፒዩተር ፕሮሰሰር ቴክኒካዊ አቅም ትሪሊየን እጥፍ አድጓል። በዚህ ደረጃ የተሻሻለና ያደገ ምንም እጃችን ላይ ያለ ነገር የለም።
“አዲስ አይነት ምጡቅ የሰው ልጆች ለመፍጠር ምናልባት የጄኔቲክ ኢንጂነሪንግን እንጠቀም ይሆናል። እውነታውን ስንመለከተው ግን ይህ የራስ ቅላችን ውስጥ ያለው አንጎል የሚሊየን አመታት እርጅና የተጫጫነው ነው። በአንፃሩ ከፊታችን ካለው ስክሪን ጀርባ ደግሞ ከእኛ የተለየ አላማ ያላቸው በሺዎች በሚቆጠሩ ኢንጅነሮችና ሱፐር ኮምፒተሮች ቅንጅት የሚሰራ አለም ይገኛል። እና ጨዋታውን ማን የሚያሸንፍ ይመስላችኋል?” በማለት የውድድሩን ተስፋ አስቆራጭነት ሀሪስ ያስረዳል።
እነዚህ ኃያል ኮምፒዩተሮች ተግባራቸውን የሚያከናውኑት ደግሞ ረቂቅና ውስብስብ በሆኑ የኮድ ቀመሮች (algorithms) ሲሆን ልክ የሰው ልጅ እንዳለው አእምሯዊ ብቃት አላቸው። በእነዚህ የኮድ  ቀመሮች (algorithms) አማካኝነት ኮምፒዩተሩ “ይህንን አድርግ” የሚል ትዕዛዝ ይሰጠዋል። ኮምፒዩተሩም ትዕዛዙን እንዴት ማከናወን እንዳለበት ራሱን በራሱ ያስተምራል። ይህንን ነው Machine Learning ብለን የምንጠራው። እናም በየዕለቱ ምን አይነት መረጃ ያዘሉ ፖስቶች በምን አይነት ቅደም ተከተል ለየተጠቃሚዎቹ ማቅረብ ያለበትን መንገድ በየቀኑ እያሻሻለና እያበለፀገ ይመጣል። በምላሹም የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎቹ በየገፆቻቸው ላይ የበለጠ ጊዜ እያጠፉ ይመጣሉ። የኮድ ቀመሮቹ ይህን ለማከናወን ምን እንደሚያደርጉ ግን ማንም አያውቅም። እነዚህ የኮድ  ቀመሮች (algorithms) የራሳቸው አእምሮ አላቸው። የኮድ ትዕዛዛቸውን የፃፈው የሰው ልጅ ቢሆንም ትዕዛዙ የሚከናወንበት መንገድ ግን ትዕዛዙን ከፃፈው ሰው እውቀት ውጪ ነው። የሰራነው ማሽን በኋላ ላይ ከኛ መረዳት ውጪ ራሱን ለውጦ እንደማግኘት ማለት ነው።
በዚህም መሰረት በፌስቡክም ሆነ በሌሎቹ የማህበራዊ ሚድያ ተቋማት ይህ ሲስተም እንዴት እንደሚሰራ የሚያውቁ ጥቂት ሰዎች ብቻ ያሉ ሲሆን እነርሱም አንድ በማህበራዊ ሚድያዎቹ ገፆች የሚሰራጭ መረጃ በቀጣይነት ምን እንደሚሆን ሙሉ መረጃ የላቸውም። እናም እንደ የሰው ልጆች እነዚህ ሲስተሞች ከቁጥጥራችን ውጪ ሆነዋል።
“በሌላ መልኩ እስካሁን ከተፈጠሩ የተግባቦት ዘዴዎች ሁሉ ለውይይት፣ ኃሳብን ለማስተላለፍና ለማስረፅ ፌስቡክ ምርጡ ነው ማለት ይቻላል። ይህ መሳሪያ በአምባገነን መሪዎች መጠቀሚያ መሆን ሲችል ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ መገመት አይከብድም። የአንድ ሀገር ህዝብ አዕምሮና አመለካከትን በቀላሉ ለመቆጣጠር እንደ ፌስቡክ አይነት መሳሪያ ኖሮ አያውቅም” ይላሉ ፌስቡክ ላይ የኢንቨስትመንት ድርሻ ከነበራቸው ግለሰቦች አንዱ የሆኑት ሮገር ማክናሚ።
ከዚህ ቀደም ንቁ ፕሮፓጋንዲስቶች ስላልነበሩ ሳይሆን ይህ የማህበራዊ ሚድያው መድረክ የሰዎችን አዕምሮና አመለካከት ሊጠመዝዙ የሚችሉ ትርክቶችን እጅግ ቀላል በሆነ መልኩ ያለምንም ከፍተኛ ወጪ ለማሰራጨት ስላስቻለ ነው።
የአንድ ሀገር የምርጫ ሂደትን ለመጠምዘዝ ከፈለግን ፌስቡክ ላይ አንድ የሴራ ቲዮሪ ግሩፕ ላይ በመግባት በመሬት ጠፍጣፋነትና በተመሳሳይ ሴራዎች የሚያምኑ 100 ሰዎች ማግኘት ቀላል ነው። ከዚያም ለፌስቡክ 100 ዎቹን ወደመሰሉ ሌሎች 100፟0 ሰዎች እንዲመራን ማድረግ ነው። ከዚያም ከነዚህ ተከታዮች ጋር በመሆን ሌሎች አያሌ የሴራ ቲዮሪዎች መጎንጎን ቀላል እየሆነ ይመጣል።
በፌስቡክና ጉግል የቀድሞ ኢንጅነር የነበረው ጀስቲን ሮዘንተይን እንደሚለው፣ “የማህበራዊ ሚድያ የኮድ ቀመሮች (algorithms) እና ፖለቲከኞች እኛን በመተንኮስና በማነሳሳት ችሎታቸው፣ እውነት ነው ብለን ልንቀበለው የምንችለው የውሸት ዜና (Fake News) በመፍጠር፣ ውሸቶቹንም በቀላሉ እንድንቀበል በማደናገር ረገድ እየተካኑ መጥተዋል። በጊዜያት የገነባነውን የግል ስብዕና እና አቋማችንን ጠብቀን መቆየትና መቆጣጠር እየተሳነን መጥቷል”።
በማህበራዊ ሚድያው እየተፈጠረ ባለው አለም ማንም እውነት የሆነን መረጃ አያምንም፣ ሁሉም መንግስት እየዋሸው እንደሆነ ያስባል፣ መረጃዎቹ በሙሉ የሴራ ቲዮሪ ናቸው፣ አንደኛው ሌላኛውን ማመን አይፈልግም። እየተፈጠረ ያለው ቀውስ በመንግስታት የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ባሉ ሰዎችና በባለ ሚሊዮን ዶላር ባለሃብቶች ይዘወራል። የቴክኖሎጂው ኢንዱስትሪ በአለም ዙሪያ፣ በየትኛውም ሀገር በአንድ ጊዜ የማህበረሰብ ትስስር ገመድን መበጣጠስ የሚያስችል መሳሪያዎች ፈጥሯል። አንድ ሀገር የሌላኛውን ጂኦግራፊያዊ ድንበር ሳይሻገር እንደፈለገው ማድረግ የሚችልበት ልክ በሪሞት ኮንትሮል እንደሚደረግ ጦርነት ሆኗል።
ሁኔታው ይህ ሆኖ ሳለ ይህ ቴክኖሎጂያዊ እመርታ የሰው ልጅ ህልውና ላይ የፈጠረው አደጋ፣ ራሱ ቴክኖሎጂው የፈጠረው ሳይሆን ቴክኖሎጂው ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ክፉ አውሬ አደባባይ የማውጣት ችሎታው ነው። ማህበረሰብ ውስጥ ያለው ክፉ አውሬ ደግሞ የሰው ልጅ ህልውና ላይ አይነተኛ አደጋ ይሆናል።

Read 3145 times