Sunday, 13 December 2020 00:00

የአለማችን ተፈናቃዮች ቁጥር ከ80 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የልብ ህመም ባለፉት 20 አመታት በገዳይነት አቻ አልተገኘለትም


           እስካለፈው ሰኔ ወር ድረስ በመላው አለም ግጭት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና ውንጀላን ጨምሮ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ80 ሚሊዮን በላይ ማለፉን ተመድ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን በማስጠለል ቀዳሚዋ አገር ቱርክ ስትሆን በአገሪቱ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ 3.6 ሚሊዮን ያህል ስደተኞች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ በመላው አለም በአስገዳጅ ሁኔታ ከተፈናቀሉት ሰዎች መካከል 45.7 ሚሊዮን ያህሉ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ አገራቸውን ጥለው የተሰደዱት 29.6 ሚሊዮን፣ ጥገኝነት የጠየቁ ደግሞ 4.2 ሚሊዮን እንደሚደርሱ አመልክቷል፡፡
በአንድ አገር ዜግነት ያልተመዘገቡ ወይም የአገር አልባ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይታወቅም፣ በመላው አለም የሚገኙ 79 ያህል አገራት በግዛታቸው ውስጥ በድምሩ 4.2 ሚሊዮን ያህል አገር አልባ ሰዎች እንደሚገኙ ማስታወቃቸውንም ሪፖርቱ አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ በመላው አለም ባለፉት 2 አስርት አመታት በርካታ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት በመዳረግ ረገድ የልብ ህመም ቀዳሚነቱን ይዞ መዝለቁንና ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 ብቻ በአለማችን 9 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በልብ ህመም ለሞት መዳረጋቸውን የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በርካታ ሰዎችን ለሞት በመዳረግ ከአንደኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ከያዙት የሞት ምክንያቶች መካከል 7ቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መሆናቸውን የጠቆመው መግለጫው፣ 10 ምክንያቶች በ2019 ብቻ በመላው አለም 55.4 ሚሊዮን ሰዎችን ለሞት መዳረጋቸውንም አመልክቷል፡፡ የመተንፈሻ አካላት ህመሞች በገዳይነት የሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ ከወሊድ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡


Read 942 times