Tuesday, 08 December 2020 00:00

እርግማንና ምርቃት፣ …… እንደምሳሌ፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

(ቅጣትና መዘዝ፣ በሙሴና በፈርዖን፣ በግሪክና በትሮይ ጦርነት)።
                   
              ወደፊት፣ ጦርነትን በሩቁ ለማስቀረት መበርታት አለብን ብለዋል ጠ/ሚ ዐቢይ። ለምን? የጦርነት መዘዝ ብዙ ነው። ማሸነፍ እንኳ በኪሳራ ነው።
ጦርነትን ለማስቀረት፣ ኑሮን የማያሻሽል፣ ኢኮኖሚን የሚያሳድግ የግል ጥረትን፣ እና የገበያ ስርዓትን ማስፋት፣ የግድ ነው። ሥራ አጥነትና ድህነት፣ ለጦርነት ያጋልጣልና።
ከውሸትና ከአሉባልታ፣ ከብሽሽቅና ከትንኮሳ ሱስ እየራቅን፣ ጭፍን አስተሳሰብን እየጣልን፣ እውነትና እውቀትን ወደሚያከብር አስተሳሰብ መሻገር ይኖርብናል።
ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ መላቀቅ ያስፈልጋል። የግል ማንነትንና የግል ነፃነትን ወደሚያከብር፣ የሕግ የበላይነትን ወደሚያሰፍን ስልጡን ፖለቲካ መራመድ አለብን።
አባት፣ አስተዋይና አዋቂ፣ ጥበበኛና ታታሪ፣ እውነትንና እውቀትን የወደደ ፃድቅ፣ ሰውን እንደስራው የሚያደንቅ፣ የጥፋቱን ያህል የሚዳኝ፣ የቅንነትና የፅናት አርአያ ነው። በአእምሮና በአካል፣ በኑሮና በመንፈስ፣ እጅጉን ቢበለጽግ፣ ተገቢ ነው። የስራ ፍሬው ነው።
እናትም፣ ትበልጥ እንደሆነ እንጂ አታንስም። መልካም ፍሬ ዘርታ፣ መቶ እጥፍ መልካም አዝመራ ታፈራለች። የፅድቋ ያህል ነው በረከቷ። ደግሞም፣ ይገባታል። ፍትህ ነው። ግን፣ ይህ ብቻ አይደለም።
በርከትና ትሩፋቱ፣ የአባትና የእናትን ህይወት ከማለምለም አልፎ፣ ለብዙ ትውልድ ይተርፋል። የልጅ ልጆቻቸውም ሕይወት፣ በድምቀት እያበበ እንደሚያፈራ፣ ኑሮአቸውም እንደሚበለፅግና በረከታቸው እንደሚበዛ ይጠረጠራል? የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ የወላጅ ፅድቅ ለልጆች በረከት እንደሆነ ያስተምራሉ። በሃይማኖት መጻህፍት ውስጥ፣ ይህንን ሃሳብ የሚሰብኩ ትረካዎች ብዙ ናቸው። ይሄ ትረካ ቃል በቃል እውነት ነው? ወይስ ሌላ ምሳሌያዊ ትርጉም አለው?
በወላጅ ፅድቅ የተነሳ፣ ቤተሰብ ሁሉ፣ ከትውልድ ትውልድ፣ የልጅ ልጆች፣ በኑሮ የተባረኩ፣ የዘላለም ህይወትን የሚወርሱ ይሆናሉ በማለት፣ የምርቃት ታሪክንና የፈጣሪ ቃል ኪዳንን ይተርካሉ።
በተቃራኒው፣ ዝንጉና ውሸታም ሰዎች፣ ሸፍጥና በደል፣ ጥፋትና ክፋት የሰሩ እንደሆነ፣ ቅጣትና መከራ፣ ስቃይና ሞት ይደርስባቸዋል። ይህም ብቻ አይደለም። በወላጆች ጥፋት ሳቢያ፣ ሰባት ትውልድ፣ የልጅ ልጆችም ፍዳ ይወርድባቸዋል በማለት፣ የእርግማን ታሪክንና የፈጣሪ ቁጣን ያስነብባሉ። ይሄ ትረካ ቃል በቃል እውነት ነው? ወይስ ሌላ ምሳሌያዊ ትርጉም አለው?
ቅጣትና መዘዝ ይለያያል። ቅጣት ለጥፋተኛ፣ መዘዝ ግን ለሌላውም ነው።
በአይሁድ፣ በክርስትናና በእስልምና ሐይማኖቶች የሚታመንበት፣ የፈርዖንና የሙሴን ትረካ አስታወሱ። የእልህና የእብሪት ባህሪይ የተጠናወተው ፈርዖን፤ በየጊዜው እየዋሸና ቃሉን እያጠፈ፣ በንዴት ስሜትም እየተገፋፋ፣ ተደጋጋሚ ጥፋት እንደፈፀመ ተዘርዝሯል - በትረካው። እያንዳንዱ ጥፋትም ቅጣትን ያስከትላል፤ መዘዝንም ያመጣል። ቅጣትና መዘዙን ሲያይ፣ ከስህተቱ ይታረማል? ከጥፋት መንገዱ ይመለሳል? በጭራሽ!
አዎ፤ ኦለአፍታ ይደነግጣል። ፀፀት ያድርበታል። ግን ለአንድ አዳር ብቻ ነው። በማግስቱ ወደ አጥፊ መንገድ ይመለሳል።
መዘዙን ይዘነጋዋል። ሩቅ ሆኖ ይታየዋል። የማይደርስ ይመስለዋል። በብልጣብልጥነት እንደሚያመልጥ ያስባል። በአንዳች ተዓምር፣ ከመዘዝ እንዲድን ይጠብቃል።
ግን፣ ከጥፋት ሰበብ ጋር፣ የጥፋት መዘዝ መምጣቱ እንዴት ይቀራል? “የተፈጥሮ ህግ”፣ በአንዳች ተአምር፣ ይለወጣል? ፈርዖንን ወይም ሌላ ሰውን ለማስደሰት፣ አልያም ለማስቀየም፣ “የተፈጥሮ ህግ” አይቀር ነገር! ፏፏቴው ሽቅብ አይጎርፍ ነገር!
ስህተትና ጥፋት እንደገና ሲደገም፤ የመከራና የስቃይ መዘዙ ይጨምራል እንጂ አይቀንስም። ሁለት ሶስቴ ይሄንን እውነታ ሲያይ፤ ስህተቱን ለማረም፣ ጥፋትን “እርም” ብሎ መንገዱን ለማቃናት የማይጥር ሰው መኖሩ አይገርምም? የፈርዖን ነገረ ስራ እንደዚያ ነው። ግን፤ አሰቡት።
በበርካታ አገራት እንደምናየው፣ ከጎረቤቱና ከገዛ መከራው ሳይማር፣ ነባር ስህተቶችንና ጥፋቶችን እንደ አዲስ እየደጋገመ፣ ስንቱ እንደሚሰቃይና እንደሚተራማመስ ተመልከቱ። ይህ ሁሉ፣ ምክር ሆኖናል? ከየራሳችን ኑሮና ከአገራች ድርብርብ መከራስ መች ተማርን?
የዘንድሮ፣ የዓምናና የካቻምና እልፍ ጥፋቶችን ከነመዘዛቸው አይተናል። የአስርና የሃያ ዓመት፣ የአርባ የሃማሳ ዓመት፣ ከዚያም በፊት የመቶና የሺህ ዓመት ታሪክስ? ተመሳሳይ ስህተቶችና ጥፋቶች እንደ አዲስ እየተደጋገሙ፣ ተመሳሳይ የመከራ መዘዞች እየተደራረቡ፣ ስንት ዘመን ተቆጠረ? ግን፣ አልተማርንበትም።
ከስህተትና ከመከራ አለመማር፣ የፈርዖን ልዩ ባህርይ አይደለም። በጣም የተለመደና የተዘወተረ የብዙ ሰዎች ባህርይ ነው። የበርካታ አገራት ባህል ነው። ከሱስ አይተናነስም። ይህን እውነት አጥርቶና አንጥሮ፣ “በምሳሌያዊ ዘይቤ” ያስጨብጣል - የፈርዖን ትረካ። የጥፋት መንገድን የለመደ እግር፣ ስህተትን የሙጥኝ ይዞ በጭፍንነት የደነደነ ልብ፣ የመዘዝ መዓትን እንዳስከተለ የሚገልፅ ነው ትረካው።
የወላጅ ጥፋት፣ ለልጆችም መዘዝ ይሆናል።
በእርግጥ፣ ጥፋቱና ስህተቱ የፈርዖን ብቻ ቢሆንም እንኳ፣ በዚሁ ሰበብ የመጣው መዘዝ ግን፣ እንደ ጦርነት ነው። የመዘዝ መዓትና መከራ እንደ ሰደድ እሳት አገሬውን አዳርሷል፤ ወደ እያንዳንዱ ቤት ገብቷል።
ጦርነት ኢኮኖሚን ማድቀቁ አይቀሬ ሆነና፣ አገር ምድሩ ደህይቷል። ማሳው ወድሞ፣ ምግብ ጠፍቶ ረሃብ በርትቷል። በፈርዖን ሳቢያ፣ አገር ታሟል። ያልተፈለፈለ፣ ያልተራባ፣ ያልተዛመተ፣ የበሽታና የመከራ ዓይነት የለም።
በየቤቱ ሀዘን ገባ። ወላጆች አለቀሱ። ልጅ ያልሞተበት ቤት የለም። የፈርዖን ልጅም፣ በሕፃንነቱ ተቀጠፈ። “አያድርስ” የሚያሰኝ ዘግናኝ እልቂትና ከባድ መከራ፣ በህጻን በአዛውንት፣ በወንድ በሴት፣ በከተማ በገጠር ሁሉ፣ በአገሬው ላይ ወርደ። ብዙ ሕይወት ረገፈ። ምን አጠፉ? ጥያቄው ከባድ ነው። ህፃናት ምን በደሉ?
አተራረኩ፣ ግራ ያጋባል፤ ያስጨንቃል። ስህተቱና ጥፋቱ የፈርዖን ነው። መዘዙ ግን፣ አገሬውን የሚለበልብ ጦርነት ሆነ። ከየቤቱ፣ በኩር ልጆችና ህፃናት ተቀጠፉ። ለምን? ለምን? በእርግጥም፣ ትረካው “ቃል በቃል” ከተተረጎመ፣ እልቂቱ እንደ ቅጣት ከተቆጠረ፣ ያስጨንቃል። የጥፋትና የክፋት ተሳታፊ ያልነበሩ ህፃናት ላይ፣ ለምን ቅጣት ይወርድባቸዋል? መሆን የለበትም።
በሌላ በኩል ግን፤ ህፃናት፣ ከጦርነት መዘዝ እንደማያመልጡ አይካድም። እንደ ቅጣት ሳይሆን እንደመዘዝ፣ ሰለባ ይሆናሉ። በአጥፊዎች የወንጀል ተግባር ሳቢያ፣ ንፁሃን ሰዎችና ሕጻናት ጉዳት እንደሚደርስባቸው የሚገልጽ ትረካ ነው - የሙሴና የፈርዖን ታሪክ።
ጦርነትን የሚያህል ፀብ ይቅርና፣ የሁለት ሰዎች ጊዜያዊ አምባጓሮና ግብግብ እንኳ፣ አካባቢን ያውካል፤ ቁሳቁስን ይሰብራል። በዚህ መሃል፣ ከስር ዳዴ የሚሉ ህጻናት፣ ማን እንደሚረግጣቸው አይታወቅም። ክፋቱ እዚህ ላይ ነው። በተንኳሽ ጸበኛ ሳቢያ የሚመጣ መዘዝ፣ ለሌላውም ይተርፋል።
በአጭሩ፣ ስህተትና ጥፋት፣ በሌላ ዓለም፣ በጁፒተር ወይም በማርስ አይደለም የሚፈጸመው። ሰዎች በሚኖሩበት ምድር ላይ ነው፤ ብሽሽቅና ስድብ፣ ለከፋና ትንኮሳ፣ ፀብና ጠርነት የሚከሰተው።
በዚህም፣ ስራና ኑሮ ይናጋል። ኢኮኖሚ ይቃወሳል። ሃብት፣ ለጦርነት ይውላል። መልሶም፣ ሃብትንና ንብረትን ያወድማል። ችግርና ረሃብ ይበረታል። ጦርነት፣ ሕይወትን ያረግፋል። አካልን ያጎድላል። ይህም፣ ለጨካኝና ለክፉ ሰዎች ይመቻል። ስነ-ምግባር ይባሱኑ እየላሸቀ፣ የሰው ሕይወት ይረክሳል። ፀብ ውስጥ ያልነበሩ ወላጆችም፣ በኩር ልጆቻቸውን ለጦርነት ይገብራሉ።
የጦርነት ባሕርይ ነው። መዘዝ የማያመጣ ጦርነት የለም። ከየቤቱ፣ በፈርዖን ቤትም ጭምር፣ በኩር ልጆች እንደተቀጠፉ የተተረከውም፤ “በምሳሌያዊ ዘይቤ”፣ የጦርነትን መዘዝ ለመግለፅ ነው። አለበለዚያማ፣ ቅጣት ለአጥፊዎች እንጂ ለህጻናትና ለንፁህ ሰዎች እንዴት ይሆናል?
ፈርዖን በፈጸመው ጥፋት፤ ልጆችና ህጻናት ላይ የቅጣት መዓት ለምን ለምን ይወርዳል? ሽንፈትና ቅጣት፣ በአጥፊው ላይ ብቻ ሲሆን ነው፤ ፍትሃዊ የሚሆነው። በዚህ መሃል ግን፣ መዘዙ ለሌላውም ይተርፋል። ትረካው ይህንን እውነት ያሳያል። የተጎዳው ፈርዖን ብቻ አይደለም። አገሬው ሁሉ ለጉዳት ተዳረገ። የሕጻናት ሕይወት ረገፈ። ከትረካው፣ ይህን ምሳሌያዊ ቁም ነገር እናገኛለን።
እንዲህ አይነት የትንኮሳና የጦርነት አስከፊ ገጽታ፣ ከነአሳዛኝ መዘዙ የተገለፀው፣ በፈርዖንና በሙሴ ትረካ ላይ ብቻ አይደለም።
ጀግና፣ ለጦርነት አይቸኩልም።
ጊዜ ሳይሽራቸው፣ ለረዥም ዘመን የዘለቁና በመላው ዓለም የተስፋፉ ትረካዎች ቢቆጠሩ፣ ከፈርዖንና ከሙሴ ትረካ ጎን ለጎን፣ የትሮይ ጦርነት ሳይጠቀስ አይታለፍም። የጦርነቱን ታሪክ ያልሰማ ሰው፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ “የትሮይ ፈረስ” (Trojan horse) ተብሎ ሲነገር መስማቱ አይቀርም። በማስመሰያ መሳሪያ አማካኝነት፣ የጠላትን ኬላ የማስከፈትና ሰርጎ የመግባት፣ ምሽግ የማፍረስና የማሸነፍ ዘዴ ነው ነገሩ።
ከጦርነቱ አስከፊነትና ዘግናኝነት ጋር ሲነጻጸር፣ የጦርነቱ መነሻ ምክንያት፣ “ኢምንት ነው” ሊባል ይችላል። የትሮይ ልዑል፣ በእንግድነት ወደ ስፓርታ ምድር ሲገባ፣ መልካም የቤተመንግስት መስተንግዶ አግኝቷል። ግን መልከመልካሟን የንጉሥ ሚስት አስኮብልሎ ወደ ትሮይ ሄደ።
ይሄ ድርጊት፣ ለጦርነት መነሻ እንደሆነ ይተርካል - የሆሜር ድርሰት። “ቃል በቃል” ከታየ፣ ህልቆ መሳፍርት ከሌለው የጦርነቱ መዘዝ ጋር ሲነጻጸር፣ የጦርነቱ መንስዔ እዚህ ግባ የማይገባ፣ መናኛ ሰበብ ነው የሚሉ ይኖራሉ።
ተዋቂው ግሪካዊ የታሪክ ፀሐፊ ሄሮዶትስም፣ የጦርነቱ ሰበብ፣ የሚስት ኩብለላ ወይ ጠለፋ ብቻ ሊሆን እንደማይችል ለማስረዳት ሞክሯል። ነገር ግን፣ በሆሜር የቀረበው ትረካ፣ የታሪክ ዘገባ አይደለም። ታሪክ ላይ የተመሰረተ ኪነ-ጥበባዊ ድርሰት ነው።
በዚያ ላይ፣ ከቃል በቃል ትርጉም በተጨማሪ፣ ምሳሌያዊ ቁም ነገር እንደያዘ ልብ ማለት ያስፈልጋል። አገርን እና መንግስትን በምሳሌያዊ ዘይቤ ለመግለጽ፣ ንግስትን እና ሚስትን መጠቀም፣ በጥንት የተለመደ አተራረክ ነው። የሆነ ሆኖ፣ በግሪክ ግዛቶችና በከተሞች ሁሉ፣ የጦርነት ቅስቀሳ ተቀጣጠለ። ዝግጅትና ዘመቻ ተጀመረ። በትሮይ ግዛትም ትጥቅ ተዘጋጀ፣ ምሽግ ተጠናከረ።
ከባባድ ጦርነቶች ተካሄዱ። ብዙ ሰው አለቀ። ጦርነቱ ግን ቶሎ አልተቋጨም። አንዱ ሲያጠቃ፣ ሌላው ሲከላከል፣ መልሶ ሲበረታ፣ ሌላው ሲያፈገፍግ፣ አመታት ተቆጠሩ። ይዘገንናል። ሃዘኑ በዛ። ቋቅ ይላል። ያንገፈግፋል። አስረኛው ዓመት ላይ ነው፣ የትሮይ ምሽግ የተሰበረው። አገር ምድሩ ተቃጠለ።
ጨርሶ ከመውደሙ የተነሳ፣ ትሮይ የሚባል ከተማ፣ እንዳልነበር ሆኖ ጠፋ። እስከመፈጠሩ ከምድረ ገፅ ተደመሰሰ። የትሮይ ጦርነትም፣ “ምናባዊ ፈጠራና ማስረጃ የሌለው አፈ ታሪክ ነው” ተባለ። ከ3 ሺህ ዓመት በኋላ ነው፣ የትሮይ ከተማ በምርምርና በቁፋሮ የተገኘው።
ሰበበኛውና ጥፋተኛው፣ አንድ ሰው ብቻ ወይም ጥቂት ሰዎች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ። መዘዙ ግን፣ ሁሉንም ጨርሶ ሊያጠፋ ይችላል። ለህፃን ለአዛውንቱ ሁሉ ይተርፋል። የወላጅ የሥራ ፍሬ፣ ለልጅ ልጆች ምርቃትና በረከት የመሆኑ ያህል፤ የዛሬ ስንፍናና ጥፋትም፣ ለልጅ ልጆች የድህነት ውርስ፣ የችግር ሸክም ይሆናል - እንደ እርግማን።
አማራጭ እየጠፋ እንጂ፣ ጦርነት፣ ለአሸናፊም ኪሳራ ነው።
ጥቃትን ለመመከትና ለማስቆም፣ ህልውናን ለማዳንና ከጥፋት ለመትረፍ፣ ሌላ አማራጭ ስለሚጠፋና ጦርነት ግዴታ ስለሚሆን እንጂ፣ በጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም። ማሸነፍም በኪሳራ ነው።
ጦርነት፣ እንደ ውድድር አይደለም። የተሸነፈ ያለ ኪሳራ ከነክብሩ እየተሸኘ፣ ያሸነፈ ደግሞ በሽልማት ደምቆ፣ ተጨማሪ ክብር ተጎናጽፎ፣ ማዕረግ አትርፎ ይመለሳል - በውድድር። ኪሳራ የለም። ጦርነት ከዚህ ይለያል። ከቁማርም ይከፋል። በቁማር ዓለም፣ በተሸናፊ ኪሳራ አሸናፊ ያተርፋል። ጦርነት ግን፣ ለሁሉም ኪሳራ ነው።
በትንኮሳና በጥቃት አማካኝነት ጦርነት የሚቀሰቅስ ጥፋተኛ ሰው፣ በዚያው ልክ ቢሸነፍ፣ ቢከስር፣ ቅጣትና መከራ ቢደርስበት፣ … ይገባዋል። ችግሩ ግን፣ በመዘዙ ህፃናትና ንፁሃን ሰዎችም፣ ለጉዳት ይዳርጋሉ።
ጥቃትን ለመመከትና ለማስቆም ወደ ጦርነት የሚገባስ? አዎ፤ ጦርነት ኪሳራንና መከራን እንደሚያስከትል አያጠራጥርም። ነገር ግን፣ ጥቃትን ባይከላከል፣ እጥፍ ድርብ ኪሳራ ይመጣበታል፤ ህልውናን የሚያሳጣ ይሆንበታል። ወደ ጦርነት ከመግባት ውጭ፣ ሌላ አማራጭ መፍትሄ ያጣል።
ከጦርነት ሽልማት እንደማያገኝ፣ ማሸነፍ በኪሳራ እንደሆነ እያወቀ ነው፤ ወደ ጦርነት የሚገባው። ከእጥፍ ድርብ ኪሳራ ለመዳን ሲል፣ ወደ ጦርነት መግባት የግድ ይሆንበታል። ጦርነት ጨዋታ እንዳልሆነ ይገነዘባልና።
የትሮይ ጦርነት፣ እንዲሁም የፈርዖንና የሙሴ ትረካዎች፣ ይህንን እውነት አጉልተው ያሳያሉ። ሙሴ፣ ለዚያ ሁሉ ጦርነት፣ ለዚያ ሁሉ እልቂትና መከራ ቅጣት ጉጉት አልነበረውም። አዎ፤ አሸንፏል። ግን ያለ ኪሳራ አይደለም። የጦርነት መዘዝ፣ በሙሴ መንደር የእያንዳንዱን ሰው በር አንኳክቷል።
ደም ያልነካው ቤት እንደሌለ ይጠቅሳል ትረካው። በእርግጥ የመቅሰፍት መዘዝ ሳይሆን፣ የመስዋዕት ደም እንደሆነ ትረካው ይገልጻል። በብዙ ትረካዎች እንደሚታየው ግን፣ በምሳሌያዊ ዘይቤ፣ የእንስሳት መስዋዕት፣ የሰውን ሞት የሚያመለክት ነው።
ለነገሩ ሙሴ ካሸነፈ በኋላም፣ መንገዱ አልጋባልጋ አልሆነለትም። እልፍ መዘዞችን መጋፈጥ ነበረበት። ለ40 ዓመታት በረሃ ለበረሃ መንከራተት፣ በረሃብና በጥም መሰቃየት፣ ከባድ መከራ ነው። በዚያ ላይ፣ እዚህና ከዚያ የሚነሳ ቅሬታና ሽኩቻ፣ ፋታ አይሰጥም። በዚህም በርካታ ሺ ሰዎች፣ በአንድ ሌሊት አልቀዋል። ሙሴም በስደት ላይ ነው የሞተው።
ጦርነት አይምጣ እንጂ፣ ከመጣ፣ …. ማሸነፍም በኪሳራ ነው።
የትሮይ ጦርነትም ይህን ይመሰክራል። ወደ ትሮይ ያልዘመተ የግሪክ መሪና ጀግና የለም ማለት ይቻላል። ግን፣ ጀግኖቹ ለጦርነት ጉጉት አልነበራቸውም። በተለይ ሁለቱ ዋና ጀግኖች፣ አኪሊስ እና ኦዲሲስ፣ ጦርነቱ የግድ ቢሆንም፣ ያለ ኪሳራ ማሸነፍ ብሎ ነገር እንደሌለ ገብቷቸዋል። እነሱን የሚስተካከል ጀግና የለም። ግን ለጦርነት አልቸኮሉም። ባይሄዱ በወደዱ። ግን ሌላ አማራጭ አልነበረም።
በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ጀግንነት፣ በአእምሮና በአካል ብቃት፣ በጥበብና በብርታት ለመዋጋት ዘመቱ። ለዚያውም የ10 ዓመት ጦርነት። ከአገራቸውና ከቤታው፣ ከእለት ስራቸውና ከቤተሰባቸው ተለይተው። ጦርነት፣ ያለ ኪሳራ ያለመዘዝ የሚደረግ አይደለማ። ጥቃትን መከላከል የግድ ነውና ወደ ጦርነት ገቡ። በጥበብና በብርታት፣ በፅኑ ጀግንነት ተዋግተዋልና አሸነፉ። ይገባቸዋል። ግን በኪሳራ ነው።
የ10 ዓመት ጦርነት ቀላል አይደለም። ብዙ ሰው አልቋል። ዋናው ጀግና አኪሊስ ሞቷል። የግሪክ ግዛቶችንና ንጉሶችን ወደ ጦርነቱ እንዲመራ የተመረጠው አጋሜኖን፣ ለጦርነቱ ሲል ሴት ልጁን ሰውቷል።
የእናትነት አንጀቷ ያረረው የአጋሜኖን ሚስት፣ ባሏን ጠላችው። ሌላ አፈቀረች። ባሏ በድል ሲመለስ ገደለችው።
የሳላሚስ ንጉሥ ግዙፉ አያክስ፣ በጦርነቱ መጨረሻ ላይ፣ ከዋናዎቹ መሪዎች ጋር ተጣላ። አእምሮው ተቃውሶ፣ በደመነፍስ የራሱ ጎራዴ ላይ ወድቆ ሞተ።
ትንሹ አያክስ የሚሉት ሌላው ጀግና መሪና ተዋጊ፣ በድል ማግስት፣ በስሜት ሲታበይ፣ መርከቡ ተሰብሮ፣ ባህር በላው።
ሌላው ተዋጊ ንጉስ፣ ወንድ ልጁን ሰውቷል። የበሽታ ወረርሽኝ አመጣህብን ተብሎም፣ ከአገሩ ተባሯል። መከራ ያላገኘው ጀግና የለም። ማን ቀረ? የስፓርታ ንጉስ ሜነሉስ፣ የኮበለለችውን ወይም የተጠለፈችውን ሚስቱን መልሶ አግኝቷል። ግን፣ በቀላሉ ወደ አገሩ አልደረሰም። የባህር ነፋስና ማዕበል፣ ወዲህና ወዲያ ሲያናጋው፤ እስከ ግብፅ ድረስ ተንከራትቷል። በዚያ ላይ፣ ውድ ወንድሙን አጋሜኖንን አጥቷል።
ሌላው ኦዴሲስ ነው። ከሚያፈቅራት ሚስቱና ከህፃን ልጁ ተለይቶ፣ በጦርነት ላይ 10 ዓመት ሙሉ ተሰቃየ። ከድል በኋላ ደግሞ፣ በባህር በዱር ብዙ መከራ አይቶ፣ ወደ አገሩ ወደ ቤተሰቡ ለመመለስ 10 ዓመት ፈጅቶበታል። ሚስቱንና ንብረቱን ለመውረስ ከ100 በላይ መሳፍንት ቤቱን አጨናንቀውና፣ አራቁተው ሲያውካኩ ነው የደረሰባቸው።
ጦርነትን ከሩቁ ማስቀረት ብንችል፤ ለትውልዶች የሚርፍ በረከት ነው።
ጦርነት ክፉ ነው። ማሸነፍ እንኳ በኪሳራ ነው። ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ፣ ወደፊት ጦርነትን ለማስቀረት በርትተን መስራት አለብን ማለታቸው ትክክል ነው። ድህነት፣ “ራሱን የቻለ” መከራ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ለጦርነት የሚያጋልጥ ጠንቅ እንደሆነ መናገራቸውም ትክክል ነው። ድሃ አገራት፣ በአማካይ በየአስር ዓመቱ፣ ጦርነት ይገጥማቸዋል ብለዋል-ጠ/ሚ ዐቢይ። ኑሮን ማሻሻል፣ ኢኮኖሚን ማሳደግ፣ ወደ ብልፅግና መራመድ፣ “ራሱን የቻለ” ትልቅ አላማ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ፣ ጦርነትን ለማስቀረት ያግዛል። ይሄ አንድ ቁም ነገር ነው።
ከጭፍንነትና ከዘፈቀደ አስተሳሰብ፣ ወደ እውነትና ወደ አእምሮ መጓዝ፤ ያስፈልጋል። አለበለዚያ፣ ውሸትንና አሉባታን መፈልፈል፣ እንደ ጥበብ እንደ ብልጠት እየተቆጠረ፣ በፌስቡክና በዩቲዩብ ብሽሽቅም እየተራገበ፣ እንዴት ይዘለቃል? ጭፍን አስተሳሰብን እየጣልን፣ እውነትና እውቀትን ወደሚያከብር አስተሳሰብ መሻገር ይኖርብናል። ይሄ ሁለተኛ ቁም ነገር ነው።
ከብሄር ብሄረሰቦች ፖለቲካ መውጣትና በግለሰብ ነፃነት ላይ ወደ ተመሰረተ ስልጡ ፖለቲካ፣ የህግ የበላይነት ወደ ሚስፋፋበት ስርዓት መራመድም ያስፈልጋል። በብሔርብሔረሰብ ከሚያቧድን የፓርቲ አደረጃጀት፣ ወደ አገራዊ አደረጃጀት መሻገር፣ ጥሩ ጅምር ነው። ይሄ፣ ትልቅ የፍትህ አላማ ነው። በዚያ ላይ ጦርነትን ለማስቀረት ይረዳል። ይሄ ሶስተኛው ቁም ነገር ነው።
እነዚህ ላይ በርትተን ብንጥርና ቢሳካልን፣ በረከቱ፣ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን፣ ለወደፊት ትውልድም ምርቃት ይሆናል።

Read 12054 times