Wednesday, 09 December 2020 00:00

ኢንተርፖል፤ አለም “የኮሮና ወንጀሎች ወረርሽኝን” ለመዋጋት ታጥቃ እንድትነሳ ጠየቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 መላው አለም ውጤታማነታቸው ከተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ጋር ተመሳስለው የተሰሩና ለጤና ጎጂ የሆኑ ሃሰተኛ ክትባቶችን በህገወጥ መንገድ በድብቅ ለመሸጥና ትክክለኛ ክትባቶችን መዝረፍን ጨምሮ በርካታ “ኮሮና ነክ ወንጀሎችን” ለመፈጸም ያቆበቆቡ የተደራጁ ወንጀለኞችን ነቅቶ እንዲጠብቅ አለማቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል አስጠንቅቋል፡፡
የተለያዩ አገራት ኩባንያዎችና የምርምር ተቋማት ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በደረሱበትና አገራት ክትባቶችን ቀድመው ለማግኘት በሚሯሯጡበት እንዲሁም የግዢ ስምምነት በመፈጸም ላይ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት፣ የተደራጁ ወንጀለኛ ቡድኖች ሃሰተኛ ክትባቶችን ለመቸብቸብ እንዲሁም ትክክለኛ ክትባቶችን ለመዝረፍ እየተዘጋጁ እንደሚገኙ መረጃ ደርሶኛል ብሏል ኢንተርፖል ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ።
ተቀማጭነቱ በፈረንሳይ የሆነው አለማቀፉ የፖሊስ ትብብር ተቋም ኢንተርፖል፣ በአባልነት ላቀፋቸው 194 የአለማችን አገራት በላከው የማስጠንቀቂያ መልዕክት፣ የተደራጁና ረጅም የወንጀል ሰንሰለት የፈጠሩ ወንጀለኞች ከኮሮና ክትባቶች ጋር በተያያዘ አካላዊም ሆነ በኢንተርኔት በኩል የሚካሄድ የወንጀል ድርጊት ሊፈጽሙ ስለሚችሉ የህግ አስከባሪ አካላት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተለያዩ የአለማችን አገራት ባልተጠበቀ ሁኔታ ለስግብግብ ወንጀለኞች መጠቀሚያ መልካም እድል ከሆነ መሰነባበቱን ያስታወሰው ተቋሙ፣ በቀጣይም ከጥራት በታች የሆኑ ሃሰተኛ ክትባቶችን በድብቅ አምርቶ መሸጥ፣ የክትባቶች ዝርፊያና ህገወጥ የክትባት ማስታወቂያዎችን ጨምሮ ኮሮና ተኮር የወንጀል ወረርሽኝ በስፋት ሊሰራጭ እንደሚችል ያለውን ስጋትም ገልጧል፡፡
ወንጀለኛ ቡድኖቹ ከዚህ ባለፈም ሃሰተኛ የኮሮና መመርመሪያ መሳሪያዎችን በህገወጥ መንገድ አምርተው ለገበያ የማቅረብ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆመው ተቋሙ፣ የአለም አገራት መንግስታት፣ የጸጥታ ሃይሎች፣ ህግ አስፈጻሚና የደህንነት ተቋማት እነዚህን ወንጀለኞች ለመከላከልና በቁጥጥር ስር ለማዋል በንቃት እንዲሰሩና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል፡፡
መድሃኒቶችን በመሸጥ ስራ ላይ ከተሰማሩ 3 ሺህ ያህል ድረገጾች ላይ ባደረገው ምርመራ፣ ከ1 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑት ለወንጀል የተቋቋሙ ወይም በቫይረስ አማካይነት የኢንተርኔት ጥቃት የሚያደርሱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን የሚናገረው ተቋሙ፣ ህብረተሰቡ በድረገጾች አማካይነት ከሚከናወኑና ሰዎችን ለሞት አደጋ ብሎም ለከፋ የጤና ችግሮች ከሚያጋልጡ የሃሰተኛ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሽያጮች ራሱን እንዲያርቅም ምክሩን ለግሷል፡፡
የአሜሪካው የአገር ውስጥ ደህንነት ምርመራ ቢሮ በበኩሉ፣ ከሰሞኑ በአገሪቱ ሁለት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች እውቅና አግኝተው በስራ ላይ ይውላሉ ተብሎ ከመጠበቁ ጋር በተያያዘ አጭበርባሪዎች ይበራከታሉ ተብሎ በመገመቱ አዲስ ዘመቻ እንደሚጀምር ማስታወቁን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ከዚህ በፊት ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው ዘመቻ ከጥራት በታች የሆኑ የፊት መከላከያ ጭንብሎችንና ለኮሮና ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠውን ክሎሮኪን የተባለ የወባ መድሃኒት አስመስለው ማምረትና ማከፋፈልን ጨምሮ ከ700 በላይ ኮሮና ነክ ወንጀሎችን መመርመሩን ያስታወሰው ቢሮው፣ ከመሰል ህገወጥ ንግድ የተገኘ 27 ሚሊዮን ዶላር መያዙንና በመሰል ድርጊቶች ላይ ተሰማርተው የተገኙ ከ70 ሺህ በላይ ህገወጥ ድረገጾችን መዝጋቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌሎች የኮሮና ቫይረስ ዜናዎች ደግሞ፣ ብሪታኒያ ፋይዘርና ባዮንቴክ የተባሉት ኩባንያዎች ያመረቱትና ከኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ 95 በመቶ አስተማማኝ እንደሆነ የተረጋገጠው የኮሮና ቫይረስ ክትባት በግዛቷ ውስጥ በጥቅም ላይ እንዲውል በመፍቀድ ከአለማችን አገራት ቀዳሚ መሆኗን የዘገበው ቢቢሲ፣ አገሪቱ ከኩባንያዎቹ 40 ሚሊዮን ክትባቶችን ማዘዟንና የአገሪቱ የመድሃኒት ቁጥጥር ተቋም ክትባቱ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ጥቅም ላይ መዋል ይችላል ሲል ፈቃድ መስጠቱንም ገልጧል፡፡ የጃፓን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግስት በበኩሉ፤ ባለፈው ረቡዕ ባሳለፈው ውሳኔ፣ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ለሚኖሩት 126 ሚሊዮን ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በነጻ እንዲያዳርስ መወሰኑን ያሁ ኒውስ የዘገበ  ሲሆን፣ የአገሪቱ መንግስት ሞዴርና ከተባለው የክትባት አምራች ኩባንያ ለ85 ሚሊዮን ሰዎች፣ አስትራዜንካ ከተባለው ክትባት ደግሞ ለ120 ሚሊዮን ሰዎች የሚሆን ክትባት ማዘዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቢዝነስ ኢንሳይደር በበኩሉ፤ የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጁንግ ኡን በቻይና የተመረተና ውጤታማነቱ ያልተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መከተባቸውን የዘገበ ሲሆን፣ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ቤተሰቦቻቸውም ክትባቱን ወስደዋል መባሉን አክሎ ገልጧል፡፡



Read 9682 times