Saturday, 05 December 2020 18:29

ትግራይ ከህወኃት ውድቀት በኋላ……

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 • የትግራይ ህዝብ አሁንም ቢሆን ህወኃትን እንደ ልጁ ነው የሚመለከተው
              • ጦርነቱ ያበቃ አይመስልም
             • የማይካድራውን ጭፍጨፋ ማን እንደፈፀመው አልተጣራም

          ባለፉት 30 ዓመታት ትግራይን ሲያስተዳድር የነበረው ህወኃት ራሱ በጫረው ጦርነት ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም በመጣበት መንገድ ወደ መጣበት ተመልሷል፡፡ ከህወኃት 30 ዓመታት አገዛዝ በኋላ ትግራይ ምን ዓይነት ተስፋ ሰንቃለች? የዚሁ የለውጥ ስጋትስ ምንድን ነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቀደም ሲል በህወኃት ላይ ሲካሄድ የነበረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ተገትቶ ድርድር  መደረግ አለበት የሚል አቋም ሲያንፀባርቅ  ከነበረው የኢሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዶሪ አስገዶም ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡


             ጠ/ሚኒስትሩ ለፓርላማ ይፋ ያደረጉትን ያልተነገረ መረጃ በተመለከተ ምን ይላሉ?
አዎ በሚገባ ተከታትየዋለሁ፤ ጥሩ ነበር። ብዙ ያላወቅናቸውን ነገሮች ነው የነገሩን፡፡ በተለይ ህወኃት ሲያደርስባቸው የነበረውን ጫና ተንኮል በሚገባ አስረድተውናል፡፡ እሳቸው የሚሏቸውን ነገሮች እውነትነት እኛም እንረዳለን፤ ተመሳሳይ አፈናዎች በእኛም በሌሎች ላይም ይደርሳሉ፡፡
ነገር ግን በጭራሽ በእንዲህ ያለ አፈና ውስጥ ይገኛሉ የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስተር ደረጃ እንዲህ ያለ አፈና እንደነበር መስማት ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ግን ምናልባት የእነሱ አፈና ከአፈጣጠራቸውና ከአስተሳሰባቸው የመነጨ ነው  ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ሪፖርት የተረዳነው አንደዚህ ሰዎች ምን ያህል ከሚነገረው በላይ በሴራ ፖለቲካ የተካኑ እንደነበር ነው፡፡ የእነ ስብሃት ቡድን ከእነሱ ውጪ ሌላ ሰው ያለ እንደማይመስላቸውና እጅግ በሃይል የሚያምኑ መሆናቸውን ነው መረዳት የሚቻለው የእነዚህ ሰዎች ድርጊት በሃገራችንና በክልላችን ዴሞክራሲ እንዳይኖር ትልቅ ማነቆ ሆኖ የቆየ ጉዳይ ነው። እኔ ግን እንዲህ ያለ አፈና ጠ/ሚስትሩ  ላይ ይፈፀማል ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላውቅም ነበር፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ  ፌደራል መንግስት ወደ ጦርነት ተገዶ እንደገባ አስረድተዋል እናንተ ቀደም ሲል ጦርነቱ አያስፈልግም መደራደር አለባቸው የሚል አቋም ነበራቸው  አሁንስ አቋማቹሁ ምንድን ነው?
አሁንም እኛ ጦርነቱን አንደግፈውም ግን ግን የጦርነቱ መንስኤ ላይ የጋራ የተወሰነ ውሳኔ ነው ለጦርነቱ መንስኤ ያኔም ህወኃት የወሰነው የምርጫ ውሳኔ ተገቢ አይደለም ብለን እኛ ተቃውመናል፡፡ ነገር ግን እኔ ያልኳችሁን  ብቻ ስሙ የሚል ነገር በመምጣቱ ህዝባችን ለመወከል በማሰብ በምርጫው ተሳትፈናል በዚህም መካከል ግን ወደ መቀሌ የተላኩ ሸማግሌዎች ምን ምላሽ እንዳገኙ ምን ሌላ አማራጭ እንደነበራቸው አላወቅንም ነበር ምን አይነት የሰላም ጥሪ እንደተደረገ ብዙም መረጃ የለንም፡፡ ወዲያው ወደ ጦርነት ተገብቶ ብዙ ሰው  ሞቷል ይሄ ትልቅ የታሪክ ጠባሳ ነው፡፡ አሁን በእርግጥ ጦርነቱ አልቋል፡፡ መንግስት በህዝብ ህይወት ላይ ጉዳት አልደረሰም ብሏል፡፡ ነገር ግን ገና ከገለልተኛ አካል መረጃ አላገኘንም፡፡ ህዝቡ አሁንም መብራት፣ ውሃ፣ የስልክ አገልግሎት የለውም እነዚህ መሰረተ ልማቶች በአፋጣን ስራ መጀመር አለባቸው፡፡ በምዕራብ ትግራይ አካባቢ ደግሞ አሁንም ችግሮች አሉ፡፡ ሰዎች እየሞቱ ነው የሚሉ መረጃዎች እየደረሰን ነው፡፡ ይሄ በአፋጣኝ ተጣርቶ መፍትሄ ማግኘት አለበት፡፡ ድርጊቱም በአፋጣኝ መቆም መቻል  አለበት መሬቱም የኛ ነው የሚል አምባጓሮ ለመፍጠር የሚሞክሩም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡ ድርጊቱም ቆሞ ህዝቡ ተረጋግቶ የተፈናቀለውም ወደ ቤቱ ተመልሶ ሰላማዊ ህይወት የሚኖርበትም ሁኔታ መፈጠር አለበት
የህወኃት መጨረሻ በዚሁ መልኩ ይደመደማል የሚል ግምት ነበራችሁ?
ህወኃት ወደ መጨረሻ አካባቢ ሲያሳያቸው ከነበሩት ባህሪዎች ተነስተን ስንመለከተው ወደ ጦርነት እንደሚገባ ግልፅ ነበር፡፡ ባህሪው በጣም እየተቀየረ ነበር። ህዝቡም እኛም ይሔ አካሄዳቸው ጥሩ አይደለም መቀየር አለበት ስንላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን አልሰሙንም፡፡ የፈራነው አልቀረም አሁን ያጋጠመን ይኸው  ነገር ነው፡፡ ሁልጊዜ እኔ ብቻ የበላይ ነኝ እኔ የምላችሁን ብቻ ስሙ የሚባል ከሆነ ተከትሎ የሚመጣው ውርደት ነው፡፡ ስለዚህ የጠበቅነው ነው የሆነው፡፡ እነ ዶ/ር ደብረጽዮን ደጋግመው ለህዝቡ ጥሪ ሲያደርጉ ነበር ግን ህዝቡ ተባባሪ አልሆነም፡፡
ለምን ይሆን ህዝቡ ተባባሪ ያልሆነው?
ህዝቡ ጦርነት አይፈልግም፡፡ እኛም ብንሆን አንፈልግም፡፡ ወደ ጦርነትም ይገባል የሚል እምነት አልነበረንም፡፡ በእርግጥ ህዝቡ ቀድሞ ህወኃት ሲል የነበረውን ነገር እየሠማ እየተገበረ ነበር፡፡ ይህም የሆነው ህወኃት ካለው የካድሬ ብዛት አንጻር ነው። ህዝቡ በካድሬዎች እጅ ነበር፡፡ ነገር ግን በሚገርም መልኩ አሁን ሊተገብራቸው አልፈለጉም፡፡ ህዝቡም ድርጅቱን መስዋዕትነትን የከፈልንበት ነው ብሎ አሁንም ድረስ እንደሚያምን ግን መዘንጋት የለብንም፡፡ አሁንም ድርጅቱን ስሙን ይወደዋል፡፡ ነገር ግን ከግለሰቦች ጋር ፀበኛ ነው፡፡ ግለሰቦችን አስወግዶ የድርጅቱን መስመር እናስተካክላለን የሚል እምነት ነው ያለው፡፡ ነገር ግን አሁን ያሉት ሰዎች እንደማይፈልጋቸው ግልፅ ነው። ለዚህ ነው እነሱን ለመተባበር ፍቃደኛ ያልሆነው የትግራይ ህዝብ አሁንም ቢሆን ህወኃት እንደ ልጅ ነው የሚመለከታቸው። እንግዲህ ጦርነቱ አልቆ ተፈላጊዎቹ ለህግ የማቅረብ ስራ ይቀራል ተብሏል፡፡ አዲሱ ጊዜ ጀምሯል።
ይሄን የእናንተን ድርጅት እንዴት ይመለከተዋል?
አሁንም ጦርነቱ ያበቃ አይመስልም ጦርነቱ ይቀጥላል ብሏል። ይሄ ጉዳይ በአጭሩ ቢቋጭ ጥሩ ነበር። አሁን ግን በሚባለው እና መሬት ላይ ያለው ከባድ ነው ወይ ብለን ብንጠይቅ ብዙም ምላሽ አናገኝም። ለማጣራት እድሉ የለም። በትግራይም እንዳለ ለማወቅ አልቻልንም። ስለዚህ አካባቢውን ግፍ በማድረግ ህዝቡ መሰረታዊ አገልግሎት እንዳያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል። መረጃዎች ማግኘት አለበት። ህዝቡ ወደ የተረጋጋ ነጻነቱ ወደ መደበኛ እለት ተእለት እንቅስቃሴው መመለስ አለበት። ከዚያ በኋላ የሚቋቋም ጊዜያዊ አስተዳደር መስርቶ ያለበትን ስራ ሰርቶ ማስቀመጥ ይቻላል። አሁን በቅድሚያ ህዝብን የማረጋጋት ስራ ነው መሰራት ያለበት። ለምሳሌ ወደ ሱዳን ብዙ ህዝብ ተሰዷል። ይሄ ህዝብ ስነ-ልቦናው ተጠግኖ ወደ ቀዬው መመለስ አለበት። ሁሉም ህዝብ ስነ-ልቦናው መጠገን አለበት። ህዝቡ ወደ ትክክለኛ ህወሃት ከተመለሰ በኋላ በራሱ ጉዳይ ራሱም ለመወሰን እድል ያገኛል። ህዝባዊ ወዳጃችን ማድረግም ይቻላል። በቅድሚያ የህዝቡ ስነ-ልቦና ነው መስተካከል ያለበት።
ማን ነው ይሄን ስራ ሊሰራ የሚችለው ይሄ የአዲሱ አስተዳደር ሃላፊነት አይደለም? እናንተ በዚህ አስተዳደር ውስጥ ተሳታፊ አይደላችሁም?
በእርግጥ ስራውን መስራት ያለበት ይህ አካል ነው። እኛም አንድ ቀን ተጠርተን ተሰብስበን እነሱ ጋር ተነጋግረናል። ጊዜያዊ አስተዳደር ምን መልክ እንዳለው እነማን እንደሚሳተፉ ግን ብዙም የታወቀ ነገር የለም። ለኛም አልተነገረንም። ነገር ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች መልካም አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች፣ ምሁራን ቢሳተፉበት ጥሩ ነው። ህዝቡንም ወደ መደበኛ ህይወቱና መረጋጋት መመለስ የሚችለውም የዚህ ሂደት ቀናነት ነው። የተሰደዱ፣ የቆሰሉ፣ የሞቱ ለሶስት ሳምንት አካባቢው ዝግ መሆኑን ተከትሎ ለከፍተኛ ችግር እና ረሃብ የተዳረጉም ይኖራሉ። ህዝቡ ውስጥ አሁን ሊኖር የሚችለው በአመዛኙ ብሶት ነው። ለዚህ ብሶት የሚመጣው ምላሽ ቦታ የተጠና መሆን አለበት። ሙያዊ መሆን አለበት። ይሄ ከተስተካከለ የትግራይ ህዝብ ለራሱ ያውቅበታል።
የህወሃት ከስልጣን መውረድን ተከትሎ በትግራይ የሚኖረው ተስፋና ስጋት በእናንተ በኩል እንዴት ይታያል?
አሁን በተጀመረው መንገድ ህዝቡ እየተረጋጋ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹን ተቀርፎ ወደ መልካም አስተዳደር ከተገባ ህዝቡ የሚፈልገው ያንን ስለሆነ ለትግራይ ህዝብ ትልቅ እድልና ተስፋ ይሆናል። ነገር ግን አሁን በተለይ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች በሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው አድልዎና በጥርጣሬ የመታየት ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ ነው። ይሄ በአፋጣኝ መቆም አለበት። ሰዎች ትግረኛ ስለተናገሩ ብቻ ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ እኛም መረጃዎች አሉን። ይሄ በአፋጣኝ መቆም አለበት።
ይሄ የሚቆምና ትግራይ ክልል ላይ የተቋረጠው የስልክ፣ ኢንተርኔት፣ መብራት እና የመንገድ ግንኙነት በሙሉ የሚመለስበት ፍጥነት ነው የህዝቡን ተስፋ የሚያለመልመው። በሌላ በኩል ህውሃት ሙሉ ለሙሉ ተወግዶ ወይም ደግሞ አማራጭ ያለው የለውጥ አካል ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ የህዝቡ ተስፋ ይለመልማል።
ከዚህ በተቃራኒ ህወሃት አማጺ ሆኖ ጫካ ገብቶ እንደ ኦነግ ሸኔ የሚዋጋ ከሆነ በክልሉም በሃገሩም ችግር ሊሆን ይችላል። ይሄ እንግዲህ ትልቁ ስጋታችን ይሆናል። ስጋቱም ከዚሁ የህወሃት እጣ ፋንታ  የሚመራ ነው።
የበለጠ ተስፋው እንዲያብብ ምንድን ነው ማድረግ ያለበት  የእናንተ ፓርቲ ምን ሃሳብ ያቀርባል?
አንደኛ የህወሃት እጣ ፈንታ መታወቅ አለበት። ሁሉም ነገር በፍጥነት መጠናቀቅ አለበት።  በሌላ በኩል የህዝቡ ቀልብ ወደ ሌላ የሚወስዱ ለምሳሌ የመሬት ጥያቄ ጉዳይ አንድ መልክ መያዝ አለበት። በርካቶች በዚህ ምክንት እየተሰደዱ መሆን መረጃዎች አሉ። ይሄ ሁኔታ የተራዘመ የፖለቲካ ችግር ይፈጥራል። የትግራይ ሕዝብም በቸልታ የሚያየው አይሆንም። ይሄን በሃይል ለመፍታት መሞከር አስቸጋሪ ነው። በሃይል የሚፈታ በተለይ የመሬት ጉዳይ አይኖርም ኖሮም አያውቅም። በአካባቢው ላይ ይኖር የነበረው ህዝብም በማንነቱ እየተጠቃ እንዲሰደድ እየሆነ ነው። ይሄ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።
በእነዚህ አካባቢዎች ፌደራል መንግስት ህግ ማስከበር አለበት።
ፓርቲያቸሁ የማይካድራውን ጭፍጨፋ ለምን አላወገዘም?
ድርጊቱን እናወግዛለን፤ ነገር ግን ማን ነው የፈጸመው የሚለውን አጥርተን ስላላወቅን …….እገሌ ነው ለማለት እንቸገራለን።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና ሌሎችም የሰብአዊ መብት ተቋማት የህወሃት ቡድን መሆኑን አረጋግጠዋል…..
እነዚህ ተቋማት ሪፖርታቸውን ቢያወጡም በኛ በኩል አሁንም የጠራ መረጃ ወይም ድምዳሜ ላይ የሚያደርሰንን ነገር አላገኘንም። እነዚህ ተቋማቱ ማንን ነው የጠየቁት? መረጃ እንዴት ነው የሰበሰቡት፣ የሚለውን ነገር እኛ በራሳችን መመዘን እንፈልጋለን። ድርጊቱን ግን ማንም ያድርገው ማን፣ ሙሉ ለሙሉ እናወግዛለን። በዚህ ላይ ድርድርም የለም።


Read 14817 times