Saturday, 05 December 2020 18:27

“ሰዎች ነገሩኛ!” እንደ ‘መረጃና ማስረጃ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“እሷ እኮ ነገር መደባበቅ አትወድም። እንዳመጣላት ነው የምትዘረግፈው፣” የሚባል ነገር አለ፡፡ ሴትየዋ እኮ ትንሽ የሆነ ነገር ደስ ካላት “አናውቃትምና ነው...” ብላ በቡናም ሆነ በሌሎች ስፍራዎች ምስጢር ተብለው የተነገሯትን ነገሮች የምትዘረግፍ ነች፡፡
“እንዲህ ተኳኩላ ስትታይ እኮ ሰው ትመስላለች፡፡”
“ደግሞ ምን ሆነች ልትያት ነው፡፡ እሷ ሰው ቀና ብላ አታይ!”
“እንዴት  ቀና ብላ ትይ! ባሏ በቀን በቀን አይደል እንዴ እንደ ኳስ ሲያንከባልላት የሚያመሸው!”
“አቤት! አቤት! ብለሽ ብለሽ ደግሞ ምኑን አመጣሽው!”
“እኔ ራሴ በቅርብ አይደል እንዴ የሰማሁት!”
“ለአንቺ ማን ነገረሽ?”
“ሰዎች ነገሩኛ!”    
አያችሁልኝ... አያችሁ አይደል! ነገርዬዋ እዚህ ላይ ነች... “ሰዎች ነገሩኛ!” የምትለዋ ላይ፡፡
እናላችሁ... አለ አይደል... ይህን መሰል ወሬ ሲነሳ እኛም ብንሆን... “እንዲህ አይነት ነገር እውነት ቢሆን እንኳን ለሌላ ሰው ይነገራል እንዴ!” እንደ ማለት ምን ይሆናል መሰላችሁ... መዳፋችንን እንዘረጋና... “እስቲ ሙት በዪኝ!” እንላለን፡፡
እናማ... ወይዘሮ እከሊት በባለቤቷ አቶ እከሌ ‘መነረቷ’ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ቁጭ፡፡
በፊት ጊዜ አንድ የሚዲያ ተቋም ውስጥ ኃላፊ የነበረ ሰው ነበር፡፡ እናላችሁ አንዱ ሠራተኛ ይሄድና እከሌ እኮ እንዲህ፣ እንዲህ አይነት ነገር ያደርጋል ብሎ እንደ ማሳበቅ ይናገራል፡፡ ይህን ተናግሮ ውልቅ ሊል ሲል ኃላፊው “ቆይ ና ቁጭ በል፣” ይለውና ኢንፎርሜሽን አድራሹም ቁጭ ይላል፡፡ ከዛ የተወራበትን ሰው ያስጠራዋል፡፡ “ስማ ይሄ ሰውዬ እንዲህ፣ እንዲህ አደረግህ ይላል፣” ይለዋል፡፡ ይህን የሚያደርገው ለማውጣጣት ምናምን ሳይሆን አሳባቂው እንዳይለምደው ነበር፡፡ ከዛ በኋላ የሰውየውን ባህሪይ የማያውቅ እስካልሆነ ድረስ ማንም ሰው ለማሳበቅ አይሞክርም፡፡
እናላችሁ... ኮሚክ እኮ ነው፡፡ እንደው ለመንገድ ያህል እዛ ሚዲያ ውስጥ የሆነች ‘ፈኒ’ ነገር አለች፡፡ በድርጅቱ አንጋፋ የነበሩ ሰው ዋነኛው ኃላፊ ይሄዱና የሆነ ሠራተኛን ስም ጠርተው ምን ብለው ቢከሱት ጥሩ ነው... “እንግሊዝኛ መጽሀፍ ያነባል፡፡” አሪፍ አይደል፡፡ ኃላፊውም ሰውየውን ሊገስጻቸው ከብዶት “እጠይቀዋለሁ...” ይላቸዋል። የተባለውን ሰው ያስጠራውና እየቀለደ “ስማ፣ ሌላ ጊዜ እንግሊዝኛ መጽሀፍ ስታነብ የቢሮህን በር እየቆለፍክ፣” አለው፡፡
እናላችሁ... ይሄ መሳበቅ ነገር በርካቶች ምስኪኖችን ስም ያበላሻል፡፡
እናላችሁ... ከእያንዳንዱ ሰው ጋር ስታወሩ በጣም ካልተጠነቀቃችሁ ቆይቶ ጭንቅላታችሁ ነው የሚዞረው፡፡
“ስማ ይቺ የሥራ አስኪያጁ ጸሀፊ እንዴት ደስ ትለኝ መሰለህ፡፡ ድርብብ ያለች ጨዋ ሰው ነች፣” ምናምን ካላችሁ በኋላ ምን የተፈጠረ መሰላችሁ... ‘ጭንቅሌ’ አካባቢ ‘ቫይረስ ዲቴክትድ’ በሚል ማስጠንቀቂያ ያጨናንቃችኋል፡፡ እናም... ‘አንቲ ቫይረስ’ አስፈላጊ ነው፡፡ ስማ እንደዛ ያልኩህ እንዲሁ በእኔና በአንተ መሀል ለጨዋታ ብዬ አንጂ በሌላ እንዳትተረጉመው፣” ትላላችሁ፡፡
እናማ... ምን ቢል ጥሩ ነው፣ ቆጣ ብሎ “ወሬኛ አደረግኸኝ እንዴ!” ብሎ ያፈጣል፡፡
“አይ እንዲሁ ድንገት በጨዋታ ጨዋታ እንዳትሳሳት ብዬ ነው”
ስሙኝማ... “ወሬኛ አደረግኸኝ እንዴ!” የምትል ነገር... አለ አይደል... ብዙ ጥያቄ የምታጭር ነች፡፡ ‘ወሬኛ አደረግኸኝ ወይ!’ ማለትን ምን አመጣው፡፡ ገና በጥናት የሚደረስበት ቢሆንም በባዶ ሜዳ “ወሬኛ አደረግኸኝ ወይ!” ብሎ የሚነሳ ካለ ሌላ ‘ቫይረስ ዲቴክትድ’ ይሆናል፡፡
ታዲያላችሁ... በሁለተኛው ቀን ነገርዬው በ‘ፕላስቲክ ሰርጀሪ’ ይነካካና ያቺ “ደስ ትለኛለች...” የምትለው ገራ ገር ጨዋታ ሰፍታ፣ ተስፋፋታ፣ ‘ፕላስቲክ ሰርጀሪ’ ተካሂዶባት መሽከርከር ትጀምራለች፤፡
“አጅሬው እኮ በዛች በሥራ አስኪያጁ ጸሀፊ ፍቅር ሊያብድ ምንም አልቀረው!”
“ይሄን አላምንህም፡፡ እሱ እንዲህ አይነት ነገር ውስጥ አይገባም”
“ራሱ ነው ለእኔ የነገረኝ”
“እስቲ ሙት በለኝ!...” መዳፍ ወደፊት፡፡ ግጥም አድርጎ ይመታለታል፡፡
“ምን አይነት የጉድ ዘመን ውስጥ መጣን! አሀ... ቆይማ ቁልቁለት ላይ በአምስተኛ አትንደርደሩ እንጂ፡፡ ባለትዳሩ አቶ እንትናና ከባለትዳሯ እትየ እንትና ጋር ፍቅር ቢይዘው ያው ‘ናቹራል’ አይደለም እንዴ!” (ቂ...ቂ...ቂ...)
“አራት ልጆች አሉት አይደል እንዴ!”
“ያውም እነሱ በህግ የሚታወቁለት ናቸው፡፡”
“ሌላ ቦታ ወልዷል እንዳትለኝና አገር ጥዬ እንዳልጠፋ! (ጥርግ ነዋ! የምን ማስፈራራት ነው! ‘መንገዱን ሻሽ ያድርግልህ፡፡’ ‘ጨርቅ ያድርግልህ፣’ የሚለውን እንዳንጠቀም ኮፒራይት ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል በማለት ነው፡፡)
“እኔ እንኳን የእሱ ናቸው ብዬ የምጠርጥራቸው ሁለት አሉ፡፡”
እናማ... ምን ለማለት ነው... ለጨዋታ ብላችሁ ያነሳችሁት ነገር የራሳችሁን ስም መጫወቻ ያደርገዋል፡፡ ‘ገበያም’ ይዘጋላ! በቀደም በስንት ዘመን የሆነ ወጣት ሀርሞኒካ ይዞ አይሁና፣ ሜሞሪ ምናምን ከች አይል መሰላችሁ! (ቂ...ቂ...ቂ...)
እግረ መንገድ.... በሀርሞኒካ በቀላሉ በአውላላ ሜዳ ላይ ሁሉም ነገር ይገባደድ የነበረበት ዘመን ‘ኖስታሊጂያ’ ምናምን ነገር አልለቅ ያላችሁ ሁሉ... ስሙኝማ... ከዘመኑ ጋር ተዋወቁማ፡፡ ሁሉም ነገር ‘ዲጂታል’ የሆነበት ዘመን ነዋ፡፡ የምር ግን በሀርሞኒካ ዘመን የስንቱ ጎረምሳ ከንፈር ነበር ለእርከን የተዘጋጀ መሬት ይመስል የነበረው! የእሷዬዋ ልቢቱ... በሙዚቃው ‘የስሙኒ ቅቤ’ ምናምን ብትሆን እንኳን ቶሎ ብሎ ወደሚቀጥለው ደረጃ (‘ኪሶሎጂ’ ላለማለት ያህል) ለመሸጋገር ‘ባዮሎጂካሊ ኢምፖሲብል’ ነበር፡፡ (ቂ...ቂ...ቂ...)
“ስማ... ከእንትና ጋር እኮ የሆነ ፕሮጀክት ልንጀምር ነው”
“ምን! ምንድነው ያልከው?”
“ከእንትና ጋር አሪፍ ፕሮጀክት ልንጀምር ነው፡፡ የሚገኝበት ገንዘብ ገንዘብ እንዳይመስልህ! ታያለህ ከጥቂት ወራት በኋላ እኔ ወንድምህ በቶዮታ ኤክስኪዩቲቭ ባላንፈላስስህ፡፡
“እኮ ፕሮጀክቱን የምትሠራው ከእሱ ጋር ነው?”
“አዎ፣  ምነው?  እኔ ዘለህ  ትጠመጠምብኛለህ ስል ጭራሽ ትኮሳተራለህ!”
“የሚጠመጠም ይጠምጠምብህ፡፡”
“አንተ ሰውዬ፣ ዛሬ ምን ነክቶሀል? ታበረታታኛለህ ስል ጭራሹን ቁጣ!”
“የነካህስ አንተ! መጀመሪያውኑስ ምን ብለህ ነው ከእሱ ጋር የምትገጥመው! ያውም ፕሮጀክት አብራችሁ ለመሥራት! ያውም ብዙ ገንዘብ ያለበት ፕሮጀክት!"
“ምንድነው ችግሩ? በስንት መፋለጥ ያገኘነው ፕሮጀክት ነው እኮ!”
“ስማ እሱ ኮትህን እንደለበስከው ላይህ ላይ ማስማማት የሚችል ነው፡፡ ባዶህን ነው የሚያስቀርህ፡፡ ስንቱን ሰው አይደል እንዴ ደም እንባ ያስለቀሰው!”
“አንተ ግን ይሄን ሁሉ እንዴት አወቅህ?”
“ሰዎች ነገሩኛ!”
አያችሁልኝ... አያችሁ አይደል! ነገርዬዋ እዚህ ላይ ነች... “ሰዎች ነገሩኛ!” የምትለዋ ላይ፡፡ “እኔን ጉድ አድርጎኛል፣ ብሎ ነገር የለ! “የቅርቤ የሆነውን ባዶውን አስቀርቶታል፣” ብሎ ‘መረጃ ሳይሆን ማስረጃ’ የለ! “ከፈለግህ አጭበርብሮ ቤቱንና መኪናውን ያሸጠውን ሰው አገናኝሀለሁ፣” ብሎ ‘ተጨባጭ’ ምናምን ነገር የለ! “ሰዎች ነገሩኛ!” ብቻ፡፡
እናላችሁ... በ“ሰዎች ነገሩኛ!” የስንቱ ምስኪን ስምና ታሪክ ተበላሽቷል መሰላችሁ!
“ሰዎች ነገሩኛ!” እንደ ‘መረጃና ማስረጃ’ የማይቀርብበትን ዘመን ያቅርብልንማ!  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2068 times