Saturday, 05 December 2020 18:27

ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ እንደሚወዳደሩ አስታወቁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በአወዛጋቢው የ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የገጠማቸውን ያልተጠበቀ መራራ ሽንፈት አሜን ብለው ለመቀበል አሻፈረኝ ሲሉ የሰነበቱት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከ4 አመታት በኋላ በሚካሄደው የ2024 ምርጫ ዳግም እንደሚወዳደሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ መናገራቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የምርጫ ማጭበርበር ተፈጽሞብኛል በሚል ያቀረቧቸው ተደጋጋሚ ክሶች ሰሚ ያላገኙላቸውና እስካሁንም ድረስ  ሽንፈታቸውን መቀበላቸውን በይፋ ያላስታወቁት ትራምፕ፣ ባለፈው ማክሰኞ በዋይት ሃውስ ባደረጉት ንግግር በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት የቻሉትን እያደረጉ እንደሚገኙና ካልሆነ ግን በቀጣዩ ምርጫ ተወዳድረው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት እንደሚመለሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር ሃሳብ እንዳላቸው ለአንዳንድ ደጋፊዎቻቸውና አማካሪዎቻቸው በሚስጥር መናገራቸውን አልፎ ተርፎም የምርጫ ቅስቀሳቸውን የሚጀምሩት ተመራጩ ጆ ባይደን በዓለ ሲመታቸውን በሚያከናውኑበት ቀን እንደሆነ መግለጻቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በምርጫው እንደሚወዳደሩ በይፋ ሲናገሩ ግን ይህ የመጀመሪያቸው መሆኑንም አክሎ ገልጧል።
በአሜሪካ ታሪክ በምርጫ ተሸንፈው ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ዳግም በሌላ ምርጫ ተወዳድረው ወደ ስልጣን የተመለሱ ብቸኛው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ግሮቨር ክሊቭላንድ መሆናቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ እ.ኤ.አ በ1884 አሸንፈው ስልጣን የያዙት ግለሰቡ በምርጫ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ እ.ኤ.አ በ1892 ዳግም በምርጫ አሸንፈው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት መመለሳቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
ከአወዛጋቢው ምርጫ ጋር በተያያዘ ቢቢሲ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ዜና እንዳለው፣ የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር፣ የአገሪቱ ፍትህ መስሪያ ቤት ምርጫው ተጭበርብሯል ብሎ እንደማያምንና የትራምፕን ተጭበርብሪያለሁ ክስ የሚደግፍ ማስረጃ እንዳላገኘ ቢያስታውቁም፣ ትራምፕ ግን ዐቃቤ ሕጉ ይህን ባሉ በሰዓታት ልዩነት “ድምጼን ተሰርቄአለሁ” የሚሉ ፅሁፎችን በትዊተር ገጻቸው ላይ መለጠፋቸውን ገልጧል፡፡



Read 1299 times