Saturday, 05 December 2020 18:19

የመከላከያ ሰራዊት የህወኃት ታጣቂ ቡድንን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የመጨረሻውን እርምጃ እየወሰደ ነው ተብሏል

Written by 
Rate this item
(32 votes)

 "ምርጫቸው ሁለት ነው፤ እጃቸውን መስጠት ወይም መደምሰስ"

              የመከላከያ ሰራዊት እስከ ትናንት ድረስ በትግራይ ተንቤን አካባቢ የህወኃት ታጣቂ ቡድንን ለህግ ለማቅረብ የመጨረሻውን እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አመራር አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል አስታውቀዋል፡፡
ህግ የማስከበርና ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብ ስራችን የጀግኖች የአገር ባለውለታዎች መፍለቂያ በሆነው የተንቤን አካባቢ ላይ ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት አቶ ነብዩ፤ በዚህ የህግ ማስከበር እርምጃ በአካባቢው ለሚደርስ ማናቸውም ችግሮች ተጠያቂው የህወሃት ታጣቂዎች ቡድን ይሆናል ብለዋል፡፡
ከመንግስት ወደ ታጣቂነት በድንገት የተቀየረው የህወሃት ቡድን መሪ ዶ/ር ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤል፤ ጦርነቱ አሁንም መቀጠሉንና ሰራዊታቸው ድል እያደረገ መሆኑን ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡
"የኤርትራ ወታደር ወደ ትግራይ ገብቶ እየተዋጋና የህዝቡን ንብረት እየዘረፈ ነው" ሲሉ የወነጀሉት ዶ/ር ድብረጽየን፤ በዚህም የተነሳ ትናንት በመቀሌ ከተማም አመፅ መነሳቱን ለሮይተርስ የተናገሩ ሲሆን የፌደራል መንግስት በበኩሉ፤ ግለሰቡ የሚናገሩት ሁሉ ሃሰት ነው ብሏል፡፡  
መከላከያ ህዳር 19 ቀን 2013  መቀሌን መቆጣጠሩን ተከትሎ፣ የህወኃት ታጣቂ ቡድን ወደ ተንቤን ሃገረ ሰላም መሸሹ የተገለፀ ሲሆን በአሁን ወቅት በመከላከያ ሰራዊት ሙሉ ከበባ ውስጥ ይገኛል ተብሏል። ከትላንት በስቲያ ሃገረ ሰላም የገባው የመከላከያ ሰራዊት፤ ሁለቱን ትላልቅ ምሽጎች በዚያው ምሽት ማፍረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በትላንትናው ዕለትም ሦስተኛውን ምሽግ ያፈረሰ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ ሚሊሻዎችም እጅ መስጠታቸው ታውቋል፡፡  


Read 17452 times