Print this page
Saturday, 05 December 2020 17:45

በማይካድራ ጭፍጨፋ ፈፅመው ወደ ሱዳን የሸሹ ታድነው ለህግ ይቀርባሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በማይካድራ በንፁሃን ላይ ጭፍጨፋ ፈፅመው ወደ ሱዳን የተሰደዱ ወንጀለኞችን መንግስት ተከታትሎ ለህግ እንደሚያቀርብ  ያስታወቀ ሲሆን  በክልሉ በጦርነት ለተጎዱ ዜጎች በረድኤት ድርጅቶች  ድጋፍ እየተደረገ ነው ብሏል።
የተባበሩት መንግስታትና የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል አፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፍ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ መስማማታቸውን ተከትሎ፣ የረድኤት ድርጅቶች ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውንም ተገልጿል።
ጦርነቱን ሽሽት ወደ ሱዳን የተሰደዱ ከ43 ሺህ በላይ የክልሉ ተወላጆችም ወደ ሃገራቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ የማድረግ ተግባር መከናወን መጀመሩን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሪፖርት አስገንዝቧል። በክልሉ የምግብና የህክምና አገልግሎትን ጨምሮ መንግስት መሰረታዊ የሆኑ የመገናኛ አውታሮችን እየከፈተ መሆኑ የሚበረታታ ነው ያለው ሪፖርቱ፤ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ መደበኛ የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው እየተመለሱ መሆኑን የረድኤት ተቋማት አረጋግጠዋል ተብሏል።
በሱዳን በስደተኛ መጠለያ ካምፕ ያሉ የክልሉ ተወላጆች ወደ ነበሩበት ተመልሰው የሚቋቋሙበት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ ነገር ግን በማይካድራው አሰቃቂ የዘር ተኮር ጭፍጨፋ የተሳተፉ አካላት በስደተኛ ካምፑ እንዳሉ ጥቆማዎች በመቅረባቸው መንግስት አጣርቶ ጥፋተኞቹን ለህግ እንደሚያቀርብ ተጠቁሟል፡፡
ስደተኞቹን መልሶ የማቋቋም ተግባሩም በስደተኞቹ ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የሚካሄድ መሆኑን መንግስት ማስታወቁ ተመልክቷል። በትግራይ ለተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስና ስደተኞችን መልሶ ለማቋቋም ይውል ዘንድ የአውሮፓ ህብረት 4 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑንም ተመልክቷል፡፡ በትግራይ ከሚከናወነው የሰብአዊ ድጋፍ ጋር በተያያዘ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በበኩሉ፤ከአለማቀፍ የቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር ከ1ሺህ በላይ የተጠፋፉ ቤተሰቦችን ደህንነት የማሳወቅ ተግባር ማከናወኑን አስታውቋል። ቀድሞ የተጎዱትን በማቋቋም ተግባር ላይ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማህበሩ ጠቁሟል፡፡



Read 877 times
Administrator

Latest from Administrator