Monday, 30 November 2020 00:00

ሀኒባል (አልቦ ፍቅር)

Written by  መኮንን ማንደፍሮ
Rate this item
(2 votes)

 ከአስቴር ጋር ተለያይቼ ከቆየሁ ከጥቂት ወራት በኋላ በአንዱ ምሽት ዳግም ዐይንዋን ለማየት ሽቼ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ተዋወቅንበት ቬነስ ሆቴል አመራሁ። ግና ከእዚያ ሆቴል ለቃ ስለነበር አላገኘዋትም።  አስቴርን ዳግም የማግኘት ጥረቴ ከሽፎ፣ ቀቢፀ-ተስፋ ከቦኝ ጥቂት ወራት እንዳለፉ፣ በአንዱ ቀን ግን ዳግም አገኘኋዋት። እህል ውሃ መልሶ ከእስዋ ጋር አቆራኘን።
ከአስቴር ጋር ወራትን በሞቀ ፍቅር ከቆየን በኋላ ኑሮአችንን በአንድ ጎጆ አደረግን።  ከዛ፣ በእንድ የቅርብ እርዳታ (እርዳታዉን ቀድሞ ለዋልኩለት ዉለታ እንደ ድርጎ ቆጥሮት) አስቴር በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ እንድትቀጠር አደረግኩ። በእዛን ወቅት የነበረው የአብሮነት ሕይወታችን በታላቅ ደስታ የተሞላ ነበር።  ኑሮዬ የአዲሱ ሕይወቴ ምእራፍ መባቻ ነበር።  
አስቴር የፍቅር ሀሁን ያስቆጠረችኝ ልዩ ሴት ናት። ክፍትና ግብዝነት የሞላው ልቤ፣ በፍቅር የተጥለቀለቀው በእስዋ ነው። ሕይወት ከመራራ ጣዕሟ  በዘለለ መልካም በረከትም እንዳላት የተረዳሁት እስዋ ወደ ልቤ ሰርጋ ከገባች በኋላ ነዉ።  እስዋን ከመዉደዴ በፊት ከራሴ ጋር የተኳረፍኩ ጨለምተኛ ነበርኩ ። የአስቴር ፍቅር ኃያል ነበር ። እስዋ ጠማማ ልብን የማቅናት ታላቅ ጥበብን የተቸረች ልዩ ሴት ናት፤ መልካም ሰብዕናዋ ወደር የማይገኝለት።  ግና፣ ሕላዌ በተቃርኖ ሕግ የተቀነበበ ነዉና፣ በአንድ እርጉም ቀን ምሽት በመሃላችን የተፈጠረ ተራ ግጭት፣ የእኔ እና የአስቴር አብሮነት እንዲቋጭ ሰበብ ሆነ። ቤታችን ሰፍኖ የኖረዉ የትእግስትና የመተሳሰብ ቆሌ ርቆ እርስ በእርስ ክፉኛ ስንነታረክ አመሸን።  
በወቅቱ ያጋጨንን ጉዳይ በቸልታ ማለፍ የሚቻል ቢሆንም፣ እሷ ግን ክብሬን አዋረድክ፤ የማንነቴን ድንበር ጣስክ በሚል አጉል ክስ አምርራ ወቀሰችኝ፤ ወትሮ የማውቀው እርጋታዋ ተሰልቦ አራስ ነብር ሆነች።  እኔም ትችቷ መሰረተ ቢስ መሆኑን በመግለፅ፣ ሽንጤን ገትሬ ተከራከርኩ፣ ጥረቴ ሁሉ ከንቱ ድካም ቢሆንም።
በቀጣዩ ቀን ገና ጎህ ሲቀድ ፣ እንቅልፍ እንደጣላት ወጥቼ ወደ ሥራ አመራሁ። ሥራ ውዬ ማታ ወደ ቤት ስመለስ ግን አስቴር አልነበረችም። ወዴትም እንደ ሄደች ሳላውቅ ፍቅሬ ጥላኝ ተሰደደች። አገኛታለሁ የሚል አጉል ተስፋን ሰንቄ ከተማው ውስጥ እሷን ሳስስ ከረምኩ፣ እሷ ግን ደብዛዋ ጠፋ።
*   *   *
የልጅነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት አራት ኪሎ ውስጥ ነው። ግሩም የልጅነት ጊዜ ነበረኝ፤ ነገር ግን የእናቴን ሞት ተከትሎ እትብቴ የተቀበረበትን መንደር ለቅቄ ለቅቄ ወጣሁ። ከዛም፣ ወደ ሌላ አካባቢ አቅንቼ አስመራሪውን የጎዳና ኑሮ መግፋት ጀመርኩ። የኑሮን ውስብስብነት የተገነዘብኩት በዛ ወቅት ነበር።
የእናቴ ድንገተኛ ሞት ዛሬም ድረስ የሀዘን ጥላውን ልቤ ላይ እንዳጠላ ነው። እጅግ የተለየች እናት ነበረችኝ፣ ደግነት ገንዘቧ የሆነ። የወትሮውን ስራዬን የጀመርኩት ከሷ ሞት በኋላ ነው። ያኔ እኖር የነበረው ፒያሳ አካባቢ ነበር። እናም፣ እዛው እውልበትና አድርበት የነበረው ሰፈር የሚያውቀኝ ካሳሁን የተባለ ዲታ፤ በዘበኝነት ሥራ ቀጠረኝ፣ በቂ ደሞዝ እየከፈለኝ። በዚህም ምክንያት ኑሮዬ መሻሻል ጀመረ። ምን ዋጋ አለው፣ አንድ እለት፣ ካሳሁን ከዚያች መሰሪ እህቱ ሮማን ጋር አብሮ የእንጀራ ገመዴን አሳጠረው፤ያለ አንዳች ጥፋት ከሥራ አሰናበተኝ።
ለሁለት አመታት ነበረ ለካሳሁን አሽከር ሆኜ ያሳለፍኩት። በዝነኛ ቡና ቤቱ ውስጥ  በዘበኝነት ለአንድ ዓመት ከሠራሁ በኋላ ሳሪስ አካባቢ የሚገኘውን የእህቱን የሮማንን ትልቅ መኖሪያ ቤት እንድጠብቅ ተዛወርኩ። የሮማን ቤት የሚገኝበት መንደር ከሸገር የዘወትር ጫጫታ እንደተነጠለ ንዑስ ከተማ ታላቅ ፀጥታ የሰፈነበት መንደር ነው። እዛ መንደር ውስጥ ረዥም ጊዜያትን በብቸኝንነት ብኖርም አልተማረርኩም።
የዘበኝነት ሥራዬን እየሰራሁ ሳሪስ መኖር በጀመርኩ በአመቱ የቤቱ ባለቤት ሮማን፣ ከባህር ማዶ ጓዟን ጠቅልላ መጣች። ይቺ ሴት(በአሉባልታ እንደሰማሁት) ትዳሯን የፈታች ሴት ናት። የፈታችው ባሏ ፈረንጅ ነበር አሉ። ይኸኛው ወሬ እውነተኛ መሆኑን አረጋግጫለሁ፤ ትልቅ ሳሎኗ ውስጥ የሰቀለችው የሙሽርነቷ ፎቶ ከዚሁ ፈረንጅ ጋር የተነሳችው ነው።
በቀድሞ አለቃዬ (በአሁኗ ጠላቴ ))ሮማን እና በእኔ መካከል የነበረው ግንኙነት ፈፅሞ የእመቤትና የሎሌ አይነት አልነበረም። የእኔና የእሷ ግንኙነት በወዳጅነት መንፈስ የተገነባ ነበር። ሮማን እንደ ሌሎቹ ባለፀጋ ሀበሾች በሀብቷ የምትኮራ አይነት አልነበረችም (ድሃን አታርቅም)።  እኔም ጥብቅ ቅርበቷን በበጎነት ደምሬ ፍፁም ታዛዧ ሆንኩ። በመሀላችን የነበረው መልካም ግንኙነት የሻከረው አንድ ቀን በተፈፀመ ኩነት ነው። ያ ኩነት እኔና ሮማንን አቃቅሮን ለማለያየት አበቃን።
እኔ እና ሮማንን ያቃቃረን ኩነት አንድ ምሽት በመኝታ ቤቷ ውስጥ የተፈፀመ ኩነት ነው። የዛን እለት ምሽት፣ ያለ ወትሮዋ እራት ሰርታ ጠራችኝ። ሳሎን ቤቷ ውስጥ ተቀምጠን የሰራችውን እራት ከቀማመስን በኋላ ረዥም ሰዓት አወጋን። በገፍ የጠጣሁት አልኮል እጅግ አግሎኛል። ጠረጴዛው ላይ ያልተደረደረ የመጠጥ አይነት አልነበረም። ሮማን ከሌሎቹ ሴቶች በላቀ መጠጥ ወዳጅ መሆኗን በሃሜት ሰምቻለሁ። ፊት ለፊቷ የቀረበውን መጠጥ በላይ በላዩ መለጋት ጀመረች። የወሬዋ ጭብጥ በመርቀቁ የቀድሞው አትኩሮቴን ነፍጌያታለሁ፣ ለይስሙላ ትኩረቴን እሷ ላይ አድርጌያለሁ። ሲጋራዋን መተርኮሻዉ ላይ ተርኩሳ ከተቀመጥችበት ሶፋ ተነሳችና ብርጭቆዋን ውስኪ ሞልታ አጠገቤ ሶፋው ደርዝ ላይ ተቀመጠች። ቀሚሷ ያልሸፈነው ቀይ ጭኗ በከፊል እላዬ ላይ አርፏል። ባድራጎቷ እጅግ ተደናግጫለሁ። በቀኝ እጇ የያዘችዉን ብርጭቆዋን ተጎንጭታ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠችና ከሶፋው ደርዝ ተነስታ ጭኖቼ ላይ ተቀመጠች፣ እጆቿ አንገቴን ዞረዋል። በድንጋጤና በይሉኝታ መሃል ሆኜ በዝምታ ግራ አጋቢ አድራጎቷን እመለከታለሁ። ይሉኝታ ዋናው የሰብእናዬ አካል ነው፣ ቀንደኛ ጠላቴም ነው። አድራጎቷ ምቾት እንደነሳኝ የተገነዘበች አይመስልም። በከፊል ተጋልጠው የሚታዩት የልጃገረድ የመሰሉት ጡቶቿ ውብ ቢሆኑም፣ አላስጎመዡኝም። ሮማን ሁሉ ነገሯ ውበት የሆነች ሴት ናት፣ ሲጋራ አጣጤሷና አረማመዷ እራሱ በቄንጥ የተሞላ ነው። ያ ፈረንጅ ባሏ ይህን ውብ ገላ ያጣው ምናልባትም ተረግሞ ሊሆን ይችላል። ሮማን ይሉኝታን ድሪያ ከመፈለግ ቆጥራው፣ ሁለመናዬን መዳሰስና መሳም ጀመረች። ከንፈሮቿ እንቡጥ ፅጌ፣ ማር የሚተፉ ቢመስሉም፣ ሲስሙኝ ገላዬን አላጋሙትም።
በመጠጥ አቅሏን የሳተችው ሮማን፤ እጄን እየጎተተች መኝታ ቤቷ ድረስ ይዛኝ ዘለቀች። በይሉኝታ እግር ብረት የተጠፈርኩ እድለ ቢስ ነኝ፣ እሷ ደሞ ለስጋዋ ተድላ እራሷን የምታረክስ ምሁር፣ በውበቷ የምትመካ ከበርቴ፣ ፍቅርን ያልታደለች ባይተዋር። እኔ ትልቅ አልጋዋ ደርዝ ላይ ተቀምጫለሁ፣ አድራጎቷን ለመቃወም ወኔ አጥቼ። እሷ ፊት ለፊቴ ቆማ አፍጥጣ እያየቺኝ ልብሶቿን በስልት ታወልቃለች። ከዛ፣ ወደ እኔ ተጠግታ በምልክት ልብሴን እንዳወልቅ አዘዘችኝ። ልብሴን አንድ በአንድ አውልቄ ፊት ለፊቷ ተገተርኩ። ገላዋ ላይ ቀርቶ የነበረውን እራፊ ጨርቅ አውልቃ፣ አልጋው ደርዝ ላይ ተቀመጠችና ቀበቶዬን አውልቄ በኃይል እንድገርፋት አዘዘችኝ። ትእዛዟ ፍፁም ግራ አጋባኝ፣ እጅጉን አስደነገጠኝ። የተናገረችውን እንዳልሰማ ሰው ፈዝዤ ተገትሬ ቀረሁ። ኃይልን ባዘዘ ቃና ደግማ ቀበቶዬን አንስቼ እንድገርፋት አዘዘችኝ። ያዘዘችውን ማድረግ ነበረብኝ፤ ቀይ ገላዋ ደም እስከሚቋጥር ድረስ ከገረፍኳት በኋላ ልብሴን ሸክፌ በችኮላ መኝታ ቤቷን ለቅቄ ወጣሁ። ይህን ምሥጢር ዛሬም ድረስ በልቤ እንደቀበርኩት ነው።
ይህ ኩነት በተካሄደ በሳምንቱ ካሳሁን መሰረተ ቢስ የሆነ ምክንያት አቅርቦ ከስራ ገበታዬ አሰናበተኝ። ለቀና ግልጋሎቴ እውቅና ሳይሰጥ በጎ ስሜን በሀሰት አጉድፎ አባረረኝ። አንዳች ጥፋት ሳይገኝብኝ ከስራ ገበታዬ የተባረርኩበትን ምክንያት ልቦናዬ ያውቀዋል። ይህ ሴራ በሮማን የተሸረበ መሆኑን አውቃለሁ። የሮማን አብይ ህልም ገመናዋ አደባባይ እንዳይወጣ (አድራጎቷ ተሰምቶ ወፈፌ ተሰኝታ ክብሯ እንዳይቀነስ፣ ምሁርነቷ ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ) እኔን ማሸሿ ነው።
*   *   *
አስቴር ጥላኝ ከሄደች በኋላ ታላቅ ባይተዋርነት ከቦኝ ደስታ የራቀው ኑሮ መግፋት ቀጠልኩ፤ የሽሽቷ ሰበብ እኔ ነበርኩና፣ በፀፀት ጅራት እየተገረፍኩ። ቶሎ መፅናናት አቃተኝ፣ እሷን በሌላ ሴት መርሳት ተሳነኝ፣ እሷን በሌላ ሴት መርሳት አልችልም። የልቤ ንግስት እሷ ብቻ ነች።
የተጣባኝ ድህነት ምሬትና የከበበኝ ባይተዋርነት ተዳምሮ፣ አንድ ሐሳብ በልቤ እንዲወለድ ሰበብ ሆነ፤ አገሬን ለቅቄ ለመሰደድ ቆረጥኩ። ከዛም ይህን ውጥኔን ከግብ ለማድረስ የሚረዳኝን ገንዘብ የማገኝበትን አቋራጭ መንገድ አሰላሁ። ምን ዋጋ አለው፣ የተለምኩትን ሴራ እውን ለማድረግ ስንቀሳቀስ ሁኔታዎች ባልታሰበ መልኩ ሄዱ፤ ፈፅሞ ያላቀድኩትን ወንጀል ፈፅሜ ዘብጥያ ወረድኩ። የተከሰስኩበት የወንጀል አይነት የግድያ ሙከራና የዝርፊያ ወንጀል ነው። ወንጀሉን በፈፀምኩበት ወቅት የተያዝኩት እጅ ከፍንጅ ስለነበር አራት አመት ተፈረደብኝ። የእያንዳንዱ ግለሰብ አብይ የህይወት ጎዳና ብዙ ጊዜ በተራና ብሽቅ አጋጣሚዎች ምክንያት የተቀየሰ ነው። ሕይወትን በራሱ ቅያስ ሊያስኬድ አቅም ያለው ፍጡር የለም። የሰው ሚና እድል ፈንታውን በይሁንታ ተቀብሎ መኖር ብቻ ነው።
በእስር ሁለት እጅግ አስመራሪ አመታትን እንዳሳለፍኩ፣አንድ እለት ፈፅሞ ያልጠበኩት ነገር ተከሰተ፣ ጥላኝ የሄደችው አስቴር ድንገት ልትጠይቀኝ መጣች። ለሁለት አመታት ትዝታዋ በሐሳቤ እየተግተለተለ አበሳዬን ሳይ ነበር የከረምኩት። ዳግም ዐይኖቿን አያለሁ ብዬ ተስፋ አላደረኩም ነበር፤ ግን ሆነ፣ የእኔ እርግብ የገጠመኝን ዕጣ ስትሰማ ገስግሳ ልትጎበኘኝ የታሰርኩበት ድረስ መጣች። ስታገኘኝ ቃላት ከአንደበቷ ሳይወጣ የፀፀት እንባዋን ብቻ ዘራች። ምናልባትም እዛ ስፍራ ዛሬም ድረስ የእንባዋ ደለል ዳና ይኖር ይሆናል። በሚወዱት ሰው ልብ ውስጥ ኩርማንም እንኳ ቢሆን ስፍራ ማግኘት ያስደስታል። እኔም፣ እጄን ዘርግቼ ተቀበልኳት እንጂ በሥራዋ  አልወቀስኳትም።
አስቴር እስር ቤት መጥታ ከጎበኘችኝ በኋላ ድጋሚ ብቅ አላለችም፣ የውሃ ሽታ ሆነች። የት እንደምትኖርም ሆነ ስለሌላ የግል ኑሮዋ አንዳችም ነገር አላውቅም። ልትጎበኘኝ የመጣች ወቅት ከእስር እስክፈታ ድረስ ብቅ እያለች እንደምትጎበኘኝ ቃል ገብታልኝ ነበር።
ከአመታት አስከፊ የእስር ህይወት በኋላ ቅጣቴን ጨርሼ በአንዱ የበጋ ወር ተፈታው። የአስቴርን ያልደበዘዘ የፍቅሯን ትዝታ በልቤ ተሸክሜ በተስፋ ወደ ቀድሞ መንደሬ አቀናሁ፣ ዕጣ ፈንታ ዳግም  ያገናኘናል የሚል እምነት በልቤ ሰንቄ። እንደገመትኩትም ረዥም ጊዜ ወደ ኖርኩበት መንደር ሳቀና የቀድሞ ሁኔታዎች ሁሉ ፍፁም ተለውጠው ጠበቁኝ፤ አልተገረምኩም፣ ምክንያቱም በነበረበት የሚዘልቅ አንዳችም ነገር የለም።
ሸገር እንደገባሁ በቀጥታ ወዳጆቼን ፍለጋ ወደ ለገሀር አመራሁ። ከቅርብ ወዳጄ መሳፍንት በቀር አብዛኞቹ ወዳጆቼ አገር ጥለው ተሰደው ስለነበር አላገኘኋቸውም።
*   *   *
ከእስር ከተፈታሁ ከወራት በኋላ አንድ እጅግ አሳዛኝ ዜና ሰማሁ፣ ልቤን በሀዘን ወጀብ የናጠ። የልቤ ንግስት ውቧ አስቴር ከሁለት አመት በፊት ማለፏን ሰማሁ፣ በሆዷ የተሸከመችውን ፅንስ በመገላገል ላይ ሳለች ለሞት መብቃቷን። ወትሮም የሕይወት በትር በእኔ ላይ እንደጨከነ ነው። በዚህ የተነሳም ይኸው  ከሕይወት ጋር እንደ ተኳረፍኩ አለሁ።


Read 1635 times