Tuesday, 01 December 2020 00:00

ፖለቲካውን እንዴት እናርቀው? እንዴትስ እናዘምነው?

Written by  ፊደል ችሎ
Rate this item
(1 Vote)

 "በህዝብና ህዝብ መሀል፣ በመንግስትና ህዝብ መሀል፣ በፖለቲካ ሰዎችና ህዝብ መሀል መተማመን እንዲሁም መግባባት እንዲኖር ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ሰዎች ከህዝቡ ፍላጎት እንዲታረቁ፣ መንግስትና ህዝብ እንዲተማመኑና እንዲከባበሩ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል፡፡---"
          
           ኢትዮጵያ በታሪክ አንጻር ረጅም እድሜ ያላት ሀገር ናት፡፡ ቀደምት ስልጣኔ ያላት፣ ፊደልን፣ ኪነ-ህንፃን፣ የሰረገላ ጥበብን ወዘተ እንደየ ዘመኑ ለአለም ያስተዋወቀቻቸው እውነቶቿ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን እንደየ ዘመኑ ተፈጥሮን ለማወቅ፣ ለመተርጎም ጥረዋል፡፡ ለዚህም አክሱምን ወይም ላሊባላን ልብ ይሏል፡፡ በሰው ልጅ የመኖር ታሪክ ውስጥ ትግል አለ፤  ዘመንን ለማወቅ፣ ልጅነትን በታሪክ አምድ ለመፃፍ፣ የኋላው ትውልድ ሊመዝነው የሚችል አሻራ ትቶ ለማለፍ፡፡ ሰው በተፈጥሮው ውስጥ ጉጉት አለው፤ የመለወጥ፣ የመሻሻል፣ ቀደምቶቹ ያልደረሱትን ለመድረሰ ቢቻል ሊተረጉመው፣ ቢያቅተው በተረት አልያም በአባባል ሊያስቀምጥ ይጥራል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪኳ፣ የስልጣኔ ከፍታዋ፣ ትናንት ያለፈችው  ውጣ ውረድ፣  የነገ ማንነቷ ጭምር ለሰፊ የፖለቲካና ታሪክ ልዩነት ምክንያት ነው፡፡
 በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ሁለት ጫፍና ጫፍ የቆሙ አተያዮች አሉ፡፡ በአንድ በኩል የዜግነት ፖለቲካን የመካከለኛ መታጋያቸው አድርገው የተሰለፉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብሄርን ወሳኝ የፖለቲካቸው ድምፅ አድርገው የሚታገሉ፡፡  የመጀመሪያው የፖለቲካ መረዳት የሀገሪቱን ችግሮች የሚፈታበት፣ መፍትሔውም የሚገኝበት መንገድ የኢትዮጵያውያንን የማህበራዊ መስተጋብር፣ የፖለቲካ ንቃት፣ የኢኮኖሚ እድገት ያገናዘበ መሆን እንዳለበት ያምናል። በዚህ መሰረት፤ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ የማህበራዊ ፍትህ መጓደልና መሰል ችግሮች በኢትዮጵያ ማእቀፍ ውስጥ መስተካከል እንደሚችሉ ይሞግታል፡፡ በተቃራኒው፤ ብሄርን መሰረት አድርገው ለሚንቀሳቀሱት፣ የሀገሪቱን የፖለቲካ ቁመና የሚያዩበት፣ ታሪክን የሚረዱበት መንገድ በእጅጉ ከመጀመሪያው የተለየ ነው፡፡ የእነዚህ መኖር በራሳቸው ችግር አይደለም፤ እንዲያውም የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመቅረፅ ይበጃሉ፡፡ በተጨማሪም አማራጭ የፖለቲካ አተያይ ናቸው፡፡ ችግር የሚሆኑት ሲፈራሩ፣ ሲፈራረጁ፣ ከርዕዮት ይልቅ ክርክራቸው ሀሜትና ህፀፅ መፈላለግ ላይ ሲሆን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለሌሎችም እንደ ምሳሌ መሆን የሚችሉ ባህሎች አሏት፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት አላት፡፡ ኢትዮጵያ  ፖለቲካዊ መልክ ያለው የሽምግልና ስርአት፣ የፍትህና ስርአት መጓደልን የሚያስተካክል ባህል አላት፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች አሉባት፡፡ ዛሬም በድንጋይ ወፍጮ የምትፈጭ እናት አለች፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ ኑሯችን የተመሰረተው በገበሬና በሬ ጫንቃ ላይ ነው፡፡ እንደ ባህል፣ እንደ ተጋድሎ የሚቆጠሩት አማፂነትና ጦርነት በታሪካችን ዛሬም አለሁ የሚሉን ሀቆች ናቸው፡፡
እንደ ሀገር ስልጣኔን እውነት ለማድረግ፣ ፖለቲካችንን መልክ ለመስጠት፣ ጦርነትና መሰል አጉል ባህሎቻችንን ለመሞረድ እንዲሁም ከችግርና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ አንዴ የሰራተኛውን ስርአት ለማቆም ማርክሲዝምን፣ ሌላ ጊዜ ፌደራሊዝምን እውነት ለማድረግ ብሄርን መታገያ አድርገናል፡፡ ይሁን እንጂ ህዝብና መንግስት የሚከባበርበት ደንብ፤ ህዝብና ህዝብ የሚደማመጥበት ስርአት እውን ማድረግ አልቻልንም፡፡ በየዘመኑ ይበጃሉ ያልናቸው ርዕዮቶች አንድም ለበሽታችን ፈውስ መሆን ተስኗቸው፣ ሁለትም የሚያርፉበት ምቹ ቦታ ሳያገኙ የታቀደውን ያህል አላራመዱንም፡፡ ትናንት መልስ አግኝተዋል ያልናቸው ዛሬም የመልስ ያለህ እያሉ ለባህል እሰጣ ገባ፣ ለፖለቲካ መጣረስ አለፍ ሲልም ለታሪካችን መጉደፍ ምክንያት መሆናቸው የአደባባይ  ሀቅ ነው፡፡      
በኢትዮጵያ የምሁራን ታሪክ ከፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም  እስከ ልደቱ አያሌው፣  ከየኔታ አስረስ የኔሰው እስከ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ ከዶክተር እጓለ ገ/ዮሐንስ እስከ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ችግራችን ለመለየት እንዲሁም መፍትሔ ለማፍለቅ ብዙ ለፍተዋል፡፡ እንደ ችግር በየልባችን የያዝንው ቂም፣ የታሪክ መረዳታችን መለያየት፣ እንደ ባህል የያዝንው ሴራና መጠላለፍ…ወዘተ ብዙ መቁጠር እንችላለን፡፡ ብሔራዊ እርቅ፣ ከቂምና በቀል መላቀቅ፣ ለዘመኑ መንፈስ መመቸት እንደ መፍትሔ የሚነሱ ናቸው፡፡
የፖለቲካ አመለካከታችን፣ የባህል እውነታችን እንዲሁም ስለ ታሪክ ያለን አተያይ በእጅጉ የተለያያ ነው፡፡ ለሽምግልና የሚመችም አይደል፡፡ በየባህሉ ስርአት አልበኝነትን የሚቆነጥጥ ሀቅ የመኖሩን ያህል ገዳይን የሚያወድስ፣ አማፂነትን የሚያበረታ፣ ጦርነትን የሚናፍቅ ቀረርቶና ውዳሴ አለ፡፡ በየማህረሰቡ ታይታን፣ ይሉኝታ ማጣትን፣ ስግብግብነትን፣ ሌብነትን የሚቃወም እውነት የመኖሩን ያህል፣ ለጥፋተኛ ከለላ የሚሰጥ፣ ወንጀለኛን የሚደብቅ አለፍ ሲልም አጥፊን ወግኖ የሚቆም እዚያም እዚህም አለ፡፡
በህዝብና ህዝብ መሀል፣ በመንግስትና ህዝብ መሀል፣ በፖለቲካ ሰዎችና ህዝብ መሀል መተማመን እንዲሁም መግባባት እንዲኖር ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ሰዎች ከህዝቡ ፍላጎት እንዲታረቁ፣ መንግስትና ህዝብ እንዲተማመኑና እንዲከባበሩ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል፡፡  
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ መልከ ብዙ ነው፡፡ በዘመናት መካከል ዲሞክራሲያዊ ለመሆን፣ ህዝባዊ ቅቡልነት ለማግኘት የፖለቲካ ፍልስፍናዎችን ከምስራቁም ከምዕራቡም ቀመስ ማድረጉ አልቀረም። ምናልባት ከማህረሰባዊ እውነታችን ጋር ሳይገናኙ ቀርተው ወይም ደግሞ በልካችን ሳይሆኑ ቀርተው አልያም ችግሩ ወዲያ እነሱ ወዲህ ሆነው በታሰቡት ልክ ያልሆኑ ብዙ ናቸው፡፡ አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው፤ ስለ ፖለቲካ ባህላችን፣ መከተል ስላለብን ርዕዮት፣ ስለ ማህበረሰቡ ያጠኑትንና የታዘቡትን በመፅሐፍ መልክ አቅርበው ነበር። መድሎት በተሰኘ ድርሳናቸው፤ ፖለቲካችን መልክ እንዲኖረው፣ ህዝቡና ፖለቲካው እንዲገናኙ፣ መንግስትና ህዝብ እንዲቀራረቡ ሞጋች ሃሳቦችን አቅርበዋል። የሚያግባቡን የታሪክና የፖለቲካ ህፀፆች፣ የሚያጣሉን የይገባኛል ጥያቄዎች፣ በየልባችን ስለምንስላት ኢትዮጵያ፣ ስለ ሀገር መቀጠልና  ስለ ህዝብ ኑሮ መስተካከል አንስተዋል፤ አቶ ልደቱ፡፡ ለአገራችን የሚበጀውም ሶስተኛ አማራጭ መሆኑን አውስተዋል፡፡ በእኔ እምነት፤ የልደቱ መድሎት ለመነቸከው ፖለቲካችን እንደ ማጣፈጫ የተሰናዳች ቅመም ናት። ፖለቲካችን ከሀሜት ይልቅ ርዕዮት ላይ፣ ከመሰዳደብ ይልቅ ምክንያታዊ ክርክር ባህሌ እንዲል ብዙ ታግዛለች፡፡ የኢትዮጵያን የኑሮ እውነት እውቅና የሚሰጥ፣ የማህረሰቡን ልክ የሚያውቅ፣ የኢኮኖሚ አቅማችንን ያገናዘበ ስርአት እያደር የሚሰራ እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡
የፖለቲካና የማህበረሰብ ጥናቶች እንደሚጠቁሙን፤ የሰው ልጅ ፖለቲካዊ እንስሳ ነው፡፡ በየዘመኑ ብልሀቱ ይለያይ እንጂ የሰው ልጅ አንዱ አንዱን ለማስገበር ከቀስት ብልሀት እስከ አቶሚክ ድረስ ተጠቅሟል፡፡ ፖለቲካ እንደየ ዘመኑ  መከበሪያ፣ መፈሪያ፣ ሀብት መሰብሰቢያ እንደነበር ታሪክ የሚያስረዳን ሀቅ ነው፡፡ ፖለቲካ እንደየ ዘመኑ፣ እንደ ህዝቡ ንቃተ ህሊናም  የሚሰፋና የሚሻሻል ስርአትም ነው፡፡ በአንድ ወቅት የገደለ ይገደል የሚል ህግ ነበር፤ በአንድ ወቅት ለመሪዎች መስገድ ባህል ነበር፣ በአንድ ዘመን አምባገነን መሆን የመሪዎች ባህሪ ነበር፡፡ ዛሬ ገዳይ የሚወደስበት፣ መሪ የሚሰገድበት፣ አምባገነን የሚደነቅበት ሥርዓትና ማእቀፍ የለም፡፡
የፖለቲካ ባህላችንን ለመሞረድ፣ በየማህበረሰቡ የሚስተዋሉ ክፉ መንፈሶችን ቆንጠጥ ለማድረግ፣ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ ---ቀድመን ከየራሳችን ጋር መታረቅ ይኖርብናል፡፡ በተጨማሪም፣ ሌላው ዓለም የደረሰበትን ለመካፈል፣ ከዘመኑ  ጋር እኩል ለመራመድ  ችግራችንን መመርመር አለብን፡፡ የሰለጠነ የፖለቲካ ስርአት መነሻው የሰለጠነ ባህል ነውና በእንዲህ ያለ ኋላ ቀር ባህል ውስጥ ሆነን፣ በእርስ በርስ ሽኩቻ ውስጥ ተዘፍቀን፤ ዲሞክራሲን እንመኘው ይሆናል እንጂ ገንዘብ አናደርገውም፡፡ ለማንኛውም ለሀገራችን ሰላም ለማምጣት መጀመሪያ ለየራሳችን ሰላም እናምጣ፡፡


Read 8291 times