Print this page
Sunday, 29 November 2020 16:27

ብሔራዊ የጀግኖችና የህፃናት አምባ ዳግም ተቋቋመ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


              የአገርን ሉአላዊትና ህግን ለማስከበር ሲሉ የአካል ጉዳት የሚደርስባቸው ጀግኖችን በዘላቂነት የመንከባከብና የጀግና ሰማዕታት ልጆችና ቤተሰቦች ቀሪ ዘመናቸውን ያለ እንግልትና ችግር እንዲገፉ የማገዝ አላማ ያለው ብሔራዊ የጀግኖችና የህፃናት አምባ እውቅናና ህጋዊ ፈቃድ አግኝቶ በአዲስ መልክ ተቋቁሟል፡፡
በአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና በዲያስፖራ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር የተለያዩ በጎ ተግባራትን በሚያከናውነው “የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት CEDA” የተሰኘ ተቋም ትብብር፣ በአዲስ መልክ የተቋቋመውን የብሔራዊ የጀግኖችና የህፃናት አምባ ህጋዊ የምዝገባና የእውቅና የምስክር ወረቀት የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዳሙ አንለይ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እጅ ተቀብለዋል፡፡
አምባውን በአዲስ መልኩ ለማቋቋም የተካሄደውን እንቅስቃሴ በተመለከተ መረጃ ለመስጠት ባለፈው ሰኞ በጦር ሃይሎች ሆስፒታል በተካሄደው ስነስርዓት ላይ የተቋሙ መስራቾች እንደተናገሩት፣ አምባው በአዲስ መልኩ መቋቋሙ ለአገር ባለውለታ ጀግኖችና ቤተሰቦቻቸው ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
የቀድሞው የጀግኖች አምባ በመፍረሱ ምክንያት ለአገራቸው ሲታገሉ የአካልና የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችና ቤተሰቦቻቸው ለችግር መጋለጣቸውን በወቅቱ የተናገሩት የአምባው ጽህፈት ቤት ሃላፊ ብ/ጄ ካሳዬ ጨመዳ፣ አምባውን በአዲስ መልኩ በማቋቋም፣ የራሱ የሆነ የገቢ ምንጮች እንዲኖሩትና ጀግኖችና የሰማዕታት ልጆችን በቋሚነት ለማገዝ እንዲችል የተጀመረውን ጥረት መደገፍ፣ የሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጎች ታሪካዊ ሀላፊነት በመሆኑ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሚኖሩ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የጦር ሀይሎች ሆስፒታል አዛዥ ብ/ጄ ሀይሉ እንዳሻው፣ በቅርቡ በአዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታውጆ መንግስትም የጀግኖችና የህፃናት አምባን ለማቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ እንደነበር ጠቁመው፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በተለይም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ከተቋሙ ጋር በመሆን ድርጅቱን በመመስረታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ለአገር ክብርና ለሉአላዊነት ሲሉ በጦር ሜዳ ጉዳት የሚደርስባቸው ወታደሮችንና  ቤተሰቦችን በዘላቂነት ለማገዝ የሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የገለፁት ጄኔራል መኮንኑ፤ ለዓላማው መሳካት መከላከያ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።



Read 1740 times
Administrator

Latest from Administrator