መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት የተሰራውን ልጁ የተወነበትን ፊልም አይተን ለፊልማችን አጭተነዋል ያለችው ሥራ አስኪያጇ፤ ፒያሳ አካባቢ የሚያድረው ታዳጊ በቀረፃም ወቅት ማግኘት ያስቸግር ስለነበር በቀረፃ ቡድኑ ቤት ያድር እንደነበር በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ ለታዳጊ ወጣት ዳንኤል ከ”ሎሚ ሽታ” ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር እንደተከፈለውና ያባክነዋል በሚል ሥጋት በአንዴ እንዳልተከፈለው የገለፀችው ወይዘሪት ፌቨን፤ መቀሌ ላለችው እናቴ እልካለሁ በማለቱ ግን ክፍያው እንደተከናወነ ገልፃለች፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለፃ በምርቃቱ ምሽት ከቤት ኪራዩ ሌላ የትምህርት ቤት እና የምግብ ወጪዎቹን የፊልሙ ቡድን እና ሌሎች ለመሸፈን ቃል ቢገቡም ልጁ ባለመገኘቱ ራሱ ስልክ እስኪደውል እየተጠበቀ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ታዳጊ ወጣቱን ባነጋገርንበት ወቅት ከምርቃቱ ምሽት እንግዶች አንዱ ከቤተሰባቸው ጋር በማኖር ሊያስተምሩት ቃል መግባታቸውንና ይህንኑ አማራጭ እንደሚቀበል ነግሮናል፡፡