Saturday, 04 August 2012 12:42

ለጐዳና ተዳዳሪው ተዋናይ ቤት ተገኘለት

Written by  መልካሙ ተክሌ melkamutekle@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

ለጐዳና ተዳዳሪው ተዋናይ ቤት ተገኘለት

በአዳም ረታ “ልቦለድ ላይ ተመስርቶ የተሰራው “የሎሚ ሽታ” ፊልም ላይ ከእናቱ ጋር ከቤቱ የተፈናቀለ ታዳጊን ሆኖ የተወነው ጐዳና አዳሪ ታዳጊ ወጣት ዳንኤል ቴዎድሮስ ቤት ተገኘለት፡፡ፊልሙ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ሲመረቅ ታዳጊውን አስመልክቶ መድረክ መሪው ጋዜጠኛ ደረጄ ኃይሌ፤ ጐዳና አዳሪነቱን ከገለፀ በኋላ በምርቃቱ ላይ የተገኙት የአራት ኪሎው ሃበሻ ሲኒማ ባለቤቶች በየወሩ ሦስት መቶ ብር ለአንድ አመት እንከራይለታለን በማለት ቃል ገብተዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ቤቱ አራት ኪሎ አካባቢ መገኘቱን የገለፀችልን “የሎሚ ሽታ” ፊልም ፕሮዱዩሰር ማቭሪክ ፊልም ፕሮዳክሽን ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ፌቨን ታደሰ፤ ልጁ ቋሚ አድራሻ ስለሌለው እስከ ሐሙስ ምሽት ድረስ መረከብ እንዳልቻለ ገልፃልናለች፡፡

መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት የተሰራውን ልጁ የተወነበትን ፊልም አይተን ለፊልማችን አጭተነዋል ያለችው ሥራ አስኪያጇ፤ ፒያሳ አካባቢ የሚያድረው ታዳጊ በቀረፃም ወቅት ማግኘት ያስቸግር ስለነበር በቀረፃ ቡድኑ ቤት ያድር እንደነበር በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ ለታዳጊ ወጣት ዳንኤል ከ”ሎሚ ሽታ” ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር እንደተከፈለውና ያባክነዋል በሚል ሥጋት በአንዴ እንዳልተከፈለው የገለፀችው ወይዘሪት ፌቨን፤ መቀሌ ላለችው እናቴ እልካለሁ በማለቱ ግን ክፍያው እንደተከናወነ ገልፃለች፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለፃ በምርቃቱ ምሽት ከቤት ኪራዩ ሌላ የትምህርት ቤት እና የምግብ ወጪዎቹን የፊልሙ ቡድን እና ሌሎች ለመሸፈን ቃል ቢገቡም ልጁ ባለመገኘቱ ራሱ ስልክ እስኪደውል እየተጠበቀ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ታዳጊ ወጣቱን ባነጋገርንበት ወቅት ከምርቃቱ ምሽት እንግዶች አንዱ ከቤተሰባቸው ጋር በማኖር ሊያስተምሩት ቃል መግባታቸውንና ይህንኑ አማራጭ እንደሚቀበል ነግሮናል፡፡

 

 

 

Read 1419 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 12:48